1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪክ ድርጅቶች ሀገር አቀፍ የሰላም ጥሪ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016

ጥሪውን ያደረጉት የሲቪክ ድርጅቶች ሰላም ባልሰፈነበትና የተስተዋሉ ቀውሶች ተገቢ መፍትሔ ባላገኙበት ወደ አዲሱ ዓመት የሚደረገው ሽግግር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ለመከላከልና ወንጀሎችን ለመቀነስ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4kOEA
Infografik Karte Äthiopien EN

አሥር የሲቪክ ድርጅቶች ሀገር አቀፍ የሰላም ጥሪ

ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ባቀረቡት ጥሪ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲከበሩ እና ፆታዊ ጥቃቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ለሰላም ጥሪው ምክንያት የሆኑ ገፊ ምክንያቶች

በ2016 ዓ.ም ብቻ በመላው ኢትዮጵያ ከ1,792 በላይ ግጭት መመዝገባቸውን፣ በዚህም ምክንያት ከ6,164 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የጠቀሱት እነዚህ የሲቪክ ድርጅቶች ይህም በሀገሪቱ በየወሩ በአማካይ 560 ሰዎች የተገደሉበት ዓመት እንደነበር አመልክተዋል።

ክስተቶቹ የዘፈቀደ ግድያዎችን እና እሥር፣ የሰላማዊ ሰዎች አካል መጉደልን፣ ፆታዊ ጥቃትንእንደበቀል እና ጥቃት መሣሪያ መጠቀምን፣ መፈናቀልን፣ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት መውደም እና የሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ መቅረትን፣ የመንቀሳቀስ ነፃነታቸውን ማጣትን፣ አፈናና የአስገድዶ መሰወር መንሰራፋትን ብሎም ቀውስን የተከተለ የኑሮ ውድነት እና ጫና የዓመቱ አሳሳቢ ሁነቶች ነበሩ በማለት ዘርዝረዋል። 

እነዚህ ቀውሶች በተለይም በአማራ እንዲሁም በኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች ተባብሰው ስለመስተዋላቸው ያመለከቱት ድርጅቶቹ፣ ለ10 ወራት ተፈፃሚ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አሉታዊ እንድምታ ማሳረፉን ገልፀዋል።
ጥሪውን ካቀረቡት ድርጅቶች መካከል የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ሴታዊት የሚገኙበት ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልም አንዱ ነው። 

ሰላም ይቅደም፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት ይስፈን 

ጥሪውን ያደረጉት የሲቪክ ድርጅቶች ሰላም ባልሰፈነበትና የተስተዋሉ ቀውሶች ተገቢ መፍትሔ ባላገኙበት ወደ አዲሱ ዓመት የሚደረገው ሽግግር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ለመከላከልና ወንጀሎችን ለመቀነስ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል። ስለሆነም ግጭቶች በሰላማዊ መንገዶች እንዲፈቱ እንዲሁም ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፈ የጠየቁት የደቦ ፍርድ በመበራከቱ፣ አፈና እና አስገድዶ መሰወር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አዳጋች በመሆኑ ነው ብለዋል። በሀገሪቱ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተስፋፍቷል ያሉትን ፆታዊ ጥቃት ለመቀነስ ይረዳ ዘንድም የፆታ ጥቃት መከላከያ ብሔራዊ ፖሊሲ እንዲፀድቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የሲቪክ ምኅዳሩ ይጠበቅ

ከዚህ በፊት መሰልየሰላም ጥሪዎችን መሻሻል የታየባቸው በጎ ጅምሮች መኖራቸውን ሆኖም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት እንቅፋት ሆኗል ያሉት የፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ለዘፈቀደ እሥር፣ ወከባ እና እንግልት፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የመሸርሸር አዝማሚያ መኖሩንም ድርጅቶቹ ገልጸዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር