የሰዓሊዋ አዲስ አይነት የጥበብ ሥራዎች  | ባህል | DW | 09.12.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የሰዓሊዋ አዲስ አይነት የጥበብ ሥራዎች 

ሁልጊዜ አዲስ ነገርን ለመፍጠር፤ ለመስራት ጉጉት እንዳላት የምትናገረዉ ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ፤ አሁን ደግሞ በጨርቅ ላይ የሚሰሩ የሃበሻ ባህልን የሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ የቤት ማስጌጫዎችን ማለትም የጠረቤዛ ልብስ፤ የሶፋ ትራስ ልብስ፤ የአልጋ ልብስ፤ የትራስጌ መብራት፤ የቡናና የሻይ ሲኒዎችን በአዲስ ጥበብ ይዛ ብቅ ብላለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:26

በኢንስተግራምና በፊስ ቡክ «HaimiArt» ላይ እገኛለሁ

«በተለይ ሴቶች እህቶቻችን፤ በቤት ዉስጥ በሥራ የተጠመድን፤ ልጅ በማሳደግ ጊዜ ያጣን፤ በርግጥም ራሳችን ብናዳምጥ፤ ብዙ ተሰጥኦ በዉስጣችን እናገኛለን እና ራሳችንን እናዳምጥ»

ስትል የምትናገረዉ «ሃይሚ አርት» በመባል የምትታወቀዉ ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ ናት። ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ በጀርመን መኖር ከጀመረች፤ ከ 20 ዓመታት በላይ ሆኗታል። ሰዓሊ ሃይማኖት የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች የሚያንፀባርቁ ስዕሎችዋን ይዛ ብቅ ካለች ከ 15 ዓመት በላይ ሆኖዋታል። ስዕሎችዋን የምትሰራዉ ቀን ተቀጥራ በምትሰራበት ከሙኒኩ የንግድ ኤግዚቢሽን የአስተዳደር ስራዋን አጠናቃ ወደ ቤትዋ ስትመለሰ ለሊት ለሊት ነበር።

ስዕልዋን ስትስል እስከ እኩለ ለሊት ድረስ እንደምታመሽ ተናግራለች። የስዕል ተሰጥኦ እንዳላት ያወቀችዉም ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር። ሁልጊዜ አዲስ ነገርን ለመፍጠር፤ ለመስራት ጉጉት እንዳላት የምትናገረዉ ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ፤ አሁን ደግሞ በጨርቅ ላይ የሚሰሩ የሃበሻ ባህልን የሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ የቤት ማሳመርያ እና ማስጌጫዎችን ማለትም የጠረቤዛ ልብሶች፤ የሶፋ እና የትራስ ልብሶች፤ የአልጋ ልብስ፤ የትራስጌ መብራት፤ የቡና እና የሻይ ሲኒዎች ላይ ስዕሎችዋን እያተመች በአዲስ ሞያ፤ በአዲስ ጥበብ ብቅ ብላለች። ሃይማኖት ከስዕል ስራዋ በተጨማሪ ይህን ሥራ የጀመረችዉ ከ 10 ዓመት በላይ በአስተዳደር ሞያ በባየር ሙኒክ ከተማ ተቀጥራ ከምትሰራበት ከንግድ ትርኢት ማዕከል በኮሮና ምክንያት በመዘጋቱ እና ስራዋን በመልቀቅዋ ነዉ።

ሰዓሊ ሃይማኖት መለሰ በጀርመን እና በምዕራቡ ዓለም «ሃይሚ አርት» በሚል ነዉ የምትታወቀዉ። የአበሻ ባህላዊ አይነት ስዕሎችን በመሳልዋ እዉቅናን አግኝታለች። አሁን ደግሞ በጨርቅ ላይ በስፊት መልክ፤ በህትመት መልክ በአዲስ ጥበብ መጥተሻል። እንዴት ነዉ አንዴም ሰዓሊ ደሞ አሁን የስፌት ባለሞያ መሆን የቻልሽዉ ስንል ጠይቀናታል።  
ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ በጀርመን ልዉጥ የተባለዉ የኮሮና ወረርሽኝ አራተኛ ዙር እንዳዛመት ስጋት በማሳደሩ ከቤትዋ ሳትወጣ ስእሎችዋንም ሆነ በጨርቅ ላይ የጀመረችዉን ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች እንደምትሰራ አጫዉታናለች። በጀርመን በኮሮና የዝዉዉር ሕግ መጥበቅን ተከትሎ ብዙዎች ስራቸዉን እያጡ መሆናቸዉንm ተናግራለች። 


ኮለኝ ከተማ በሚገኝ አንድ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ከጎርጎረሳዉያኑ ከ1957 ዓ,ም እስከ 1961 ዓ.ም የስዕል እዉቀቱን በከፍተኛ ትምህርት ያዳበረዉ ሁለገቡ ጥበበኛ፤ ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደሰታ ከትምህርት ማዕከሉ በከፍተኛ ዉጤት ማጠናቀቁ ይነገርለታል። በአሁኑ ወቅት የሰዓሊና ገጣሚ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ፈለግ ይዘዉ በጀርመን የሥነ- ጥበብ ሥራዎቻቸዉን እያስተዋወቁ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ጥቂቶች አይደሉም።  «ሃይሚ አርት» በመባል የምትታወቀዉ ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለ አንዷ ናት። ሰዓሊ ሃይማኖት መሰለን ይበል በርቺ በማለት ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 


አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

Audios and videos on the topic