1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰዎች ደብዛ መጥፋትና የቤተሰብ ጭንቀት

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016

እምጥ ይግቡ ስምጥ የማይታወቅ ደብዛቸው ለቀናት፣ ለሳምንታት ብሎም ለወራት የሚጠፋ ሰዎችን ዜና መስማት የተለመደ እየመሰለ ነው። ይህ ክስተት ባለፈው ወር ለሥራ ከቤታቸው የወጡ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ላይ ጭምር መድረሱን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወንድማቸው ነግረውናል።

https://p.dw.com/p/4e6a8
Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Eshete Bekele/DW

የሰዎች ደብዛ መጥፋትና የቤተሰብ ጭንቀት

የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሀብታሙ በላይነህ የተባሉ ሰው የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ. ም ከቤታቸው እንደውጡ እስካሁን ደብዛቸው መጥፋቱን ቤተሰቦቻቸው ለዶቼ ቬለ ገለፁ።አዲስ አበባ ውስጥ ለሚመለከተው የፀጥታ አካል በደብዳቤ እና በቃል ማመልከታቸውን የገለፁት ወንድማቸው "መረጃ የለንም" የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው እና ወንድማቸው ሊታሰሩ የሚችሉበት የሚያውቁት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ አርብ የካቲት 8 ቀን 2016ዓ.ም ከቤት እንደወጡ እስካሁን የት እንደገቡ ያልታወቁት ኢንጂነር አማኑኤል መንገሻ የተባሉ ሰው ባለቤት ባለቤታቸው የት እንዳሉ ማወቅ እንደተቸገሩ ገልፀው "እስካሁን መፍትሔ አላገኘንም" ብለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች ከቤታቸው እንደወጡ ለሳምንታት ደብዛቸው ሲጠፋ፣ በኋላም በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር  መቆየቸው ሲገለጽ ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም በታጣቂዎች ተይዘው ቤዛ ሲጠየቅባቸው ማየት ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል።

ተደጋጋሚው የሰዎች መጥፋት 

እምጥ ይግቡ ስምጥ የማይታወቅ ደብዛቸው ለቀናት፣ ለሳምንታት ብሎም ለወራት የሚጠፋ ሰዎችን ዜና መስማት የተለመደ እየመሰለ ነው። ይህ ክስተት ባለፈው ወር ለሥራ ከቤታቸው የወጡ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት  አባል ላይ ጭምር መድረሱን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወንድማቸው ነግረውናል። ለስብሰባ ብለው ወጥተው በዚያው የጠፉት አቶ ሀብታሙ ሊታሰሩ የሚችሉበት የሚያውቁት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለም ወንድማቸው ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

በተመሳሳይ የካቲት 8 ቀን 2016ዓ.ም ከሚኖሩበት አዲስ አበባ የካ አባዶ ከቤት እንደወጡ ደብዛቸው የጠፋው ኢንጂነር አማኑኤል መንገሻ የተባሉ ሰው ከጠፉ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ አጋፔ ግዮን ገልፀውልናል።
ይህንን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች  ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪልን ጠይቀናቸዋል። በመሰል ክስተቶች ላይ ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ  ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች ከቤታቸው እንደወጡ ደብዛቸው ሲጠፋ፣ በኋላም በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር መቆየቸው ሲገለጽ ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም በታጣቂዎች ተይዘው ቤዛ ሲጠየቅባቸው ማየት ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል። ይህ በተለይ በፖለቲከኞች፣ በያገባናል ባዮች እና ጋዜጠኞች ላይ ተደጋግሟል።  
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ