1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባዎችን የሚመለከቱ ሕግጋት

ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለተጎጅዎች ማካካሻ እንዲሰጥ የሚረዳ እና የጅምላ ወንጀሎችን ለመመርመር የሚያግዝ የሕግ ሠነዶችን ማዘጋጀታቸውን የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ገለፀ።

https://p.dw.com/p/4lh0H
የፍትህ ተምሳሌት
የፍትህ ተምሳሌት ፎቶ ከማኅደርምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

 ሀገር በቀል የሆነው ይህ የሲቪክ ድርጅት ሕጎቹን የማውጣት ሥልጣን የመንግሥት ቢሆንም የማውጣት ሂደቱ ምን መምሰል አለበት የሚለውን በሚረዳ መልኩ መዘጋጀታቸውን እና ለውይይትም መቅረባቸውን አስታውቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ተከትሎ ሰለባዎች የሚካሱበት እና አጥፊዎች የሚጠየቁበት የፍሬ ነገርም ሆነ የሥነ-ሥርዓት ሕግ እና ተቋም አለመኖር ለሕጎቹ መዘጋጀት ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል። ሕጎቹ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስለመሆኑም ተነግሯል።

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጠበቃ አምሃ መኮንን እንዳሉት ሥር በሰደደ ድህነት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት በዐሉታ እየተነሳች ያለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አስተሳሰብን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ለሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ማሽቆልቆል አንድ ምክንያት ሆኗል። 

ኢትዮጵያ እያስተናገደቻቸው ያሉትኃይል የቀላቀሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች የሚያስከትሉት የመብት ጥሰት ጥልቀት «ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን በቡድን ደረጃም አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የመገፋት እና የመገለል ቅሬታን እንደፈጠሩ ይገመታል» ብለዋል። ይህ ለመብት ጥሰት አዙሪት መዳረጉን የገለፁት ኃላፊው የጥሰት ሰለባዎች እንዲያገግሙ እና እንዲጠበቁ የሚያግዙ እንዲሁም የጅምላ ግድያን ለመመርመር የሚረዱ ሕግጋትን ድርጅታቸው በባለሙያዎች ማሰናዳቱን ገልፀዋል።

«በሀገራችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጅዎችን በተመልከተ ሙሉ በሙሉ ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ፣ እንዲጠገኑና ዳግመኛም ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጥበቃ የሚያደርግላቸው እና መብታቸውን የሚያስከብሩበት ይህ ነው የሚባል የፍሬ ነገርም ሆነ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ወይም ተቋም የለም»።

Äthiopien Addis Abeba 2024 | Amha Mekonnen, Geschäftsführer von 'Lawyers for Human Rights'
የሕግ ባለሙያ አማሃ መኮንንምስል Solomon Muchie/DW

በድርጅቱ የተዘጋጁት የሕግ ሠነዶች መንግሥት የሕግ እና የፖለቲካ ግዴታ በገባበት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉ ናቸው ተብሏል። ሠነዶቹን ያዘጋጁት ባለሙያ ዶክተር ማርሸት ታደሰ የማካከሻ ሀሳብን የያዘውን ሠነድ አላማ ሲገልፁ ሀገር የዜጎቹን ደህንነት ከመጠበቅ ግዴታ እንፃር አያይዘውታል።

«ማንም ይፈጽመው ማን ለተፈፀሙ በደሎች ሀገሩ ኃላፊነት አለበት የሚል መልዕክት ያለው ነው»። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ራኬብ መሰለ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለማውጣት የተያዘውን ቁርጠኝነት በበጎ ጠቅሰው ሆኖም ይህ በአተገባበሩ ላይም ሊኖር የተገባ ነው ብለዋል። «እንደዚህ ዓይነት ሰፊ ችግሮችን ለማስቆም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል»። 

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ያዘጋጃቸውና ለውይይት የቀረቡት ሰነዶች በሂደት ታትመው ለመንግሥት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አፈፃፀም ሥራ እንደ ግብዓት ያገለግላሉ ተብሏል። ይሁንና ወደ ፊት ሕግ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ በፊት ለተፈፀሙ ፍትሕ ለሚጠየቅባቸው ጉዳዮችም ምላሽ እንዲሰጡ የሚያግዙ እንዲሆኑ ይጠበቃል ተብሏል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ