1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እና የጎረቤት ሃገራት ሚና

እሑድ፣ መስከረም 22 2015

ሰላማዊ መፍትሔ ያጣው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ጨምሮ ሀገሪቱን ለሚያብጠው አለመረጋጋት በጦርነቱ በቀጥታ በመሳተፍም ሆነ ግጭቶች እንዲባባሱ የጎረቤት ሃገራት ሚና እንዳላቸው በስም እየተጠቀሰ ሲነገር ይሰማል። ድርድን በመደገፍ ለሰላም ንግግሩ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የገለጹ የጎረቤት ሃገራት እንዳሉ ስማቸው ይጠቀሳል።

https://p.dw.com/p/4HeWP
Karte Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre EN

በጦርነቱ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኑ የጎረቤት ሃገራት ሚና

ብርቱ ሰብአዊ እልቂት፣ ኤኮኖሚያዊ ውድመት እንዲሁም ማሕበራዊ ቀውስ ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መሸናነፍ ሳይኖረው ለግልግልም እንዳስቸገረ ቀጥሏል። ጦርነቱ ቆሞ የፌዴራል መንግስቱ እና የትግራይ ኃይሎች  ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ መንግስታት እና ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አልሰመረም።

የአፍሪቃ ህብረት ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ፣ የአውሮጳ ህብረት እና ሌሎች ሃገራት በተናጥል እና በጋራ ሲያደርጓቸው የነበሩ የሰላም ጥረቶች ተፋላሚ ወገኖች ተፈጻሚ ሊሆን በሚያስቸግር ቅድመ ሁኔታ አልያም ለሰላም ንግግሩ ከቃል ባለፈ ተግባራዊ ምላሽ ባለመስጠት ሳይሳካ ቀርቷል። የሰላም  ጥረቶች ላለመሳካታቸው በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የውጭ መንግስታት ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው።

የሰላም ሂደቱ ፍሬ ላለማፍራቱ በመንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ብርቱ አለመተማመን መስፈኑ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል  የሁለቱን ወገኖች ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ያነጋገሩት   በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ገልጸዋል ።

ህዳር 2013 ዓ/ም የተጀመረው ጦርነቱ አንዴ ጋብ አንዴ  ፋም  እያለ እነሆ ሶስተኛ ዙር ደም እያፋሰሰ ቀጥሏል።   ጦርነቱ  እንደገና ለመቀስቀሱ ተፋላሚ ወገኖች  በጠብ አጫሪነት አንዱ አንደኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ሰላማዊ መፍትሔ ያጣው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ጨምሮ ሀገሪቱን ለሚያብጠው አለመረጋጋት በጦርነቱ በቀጥታ በመሳተፍም  ሆነ ግጭቶች እንዲባባሱ የጎረቤት ሃገራት ሚና እንዳላቸው በስም እየተጠቀሰ ሲነገር ይሰማል። በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪቃ ህብረት ጥላ ስር በሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ድጋፍ የሚደረገውን የማደራደር ጥረት በተናጥል በመደገፍ ለሰላም ንግግሩ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የገለጹ የጎረቤት ሃገራት እንዳሉ ስማቸው ይጠቀሳል።

«በሰሜን ኢትዮጵያ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት ፤ የጎረቤት ሃገራት ሚና » የዛሬው የእንወያይ መሰናዷችን ርዕስ ነው።

ታምራት ዲንሳ