1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ቅኝት በትግራይ

ሰኞ፣ ግንቦት 14 2015

የትግራይ ኃይሎችን ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆን ትጥቅ የማስፈታት ሥራ መፈፀሙን በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ ተቆጣጣሪ ልዑክ ገለፀ።

https://p.dw.com/p/4Rfwt
Äthiopien AU-Überwachungsteam in Mekelle
ምስል Million Hailesilassie/DW

የሰላም ስምምነቱ ትግበራ

 

የትግራይ ኃይሎችን ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆን ትጥቅ የማስፈታት ሥራ መፈፀሙን በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ ተቆጣጣሪ ልዑክ ገለፀ። በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻፀምን በተመለከተ ለተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ አታሼዎች ማብራርያ የሰጠው የሕብረቱ የሰላም ስምምነት አፈጻፀም ተቆጣጣሪ ልዑክ በፌደራሉ መንግሥት በኩልም መፈጸም የሚገባቸው ተግባራት እየተከወኑ መሆኑን አንስቷል። 

ከስድስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለመታዘብ እና አሁናዊ የትግራይ ሁኔታን ለማየት 43 የተለያዩ ሃገራት ወታደራዊ አታሼዎች በመቐለ ጉብኝት ያደረጉት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ነበር። ወታደራዊ አታሼዎቹ በመቐለ ቆይታቸው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ልዑክ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በዚሁ መድረክ ለወታደራዊ አታሼዎች ማብራርያ የሰጡት በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ ልዑክ መሪ ሜጀር ጀነራል ስቴቨን ራዲና በሰላም ስምምነቱ መሠረት ትጥቅ የማስፈታቱ ተግባር ከ85 እስከ 90 በመቶ መፈፀሙን አስታውቀዋል። ጀነራሉ አክለውም ትጥቅ ከማስፈታት በተጨማሪ የቀድሞ ተዋጊዎችን የማቋቋም ሥራም እንደሚከወን አንስተዋል። 

Äthiopien | Straßenszene Mekele City
መቀሌ ከተማ ምስል Million Gebresilassie/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከመመለስ አንፃር የተናገሩት ሜጀር ጀነራል ስቴቨን ራዲና፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የስልክ እና ባንክ ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች መጀመራቸውን  በአወንታዊነት የሚጠቀስ ብለውታል። ጀነራሉ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነት ልዑኩ በቅርቡ በምዕራብ ትግራይ ጉብኝት እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የኤርትራ ኃይሎች አሁንም የሰላም ስምምነቱ እንቅፋት ሆነው መቀጠላቸውን በማንሳት፣ ሰብአዊ እርዳታ የማዳረስ ሥራ ከማደናቀፍ በተጨማሪ የአፍሪቃ ሕብረቱን ተቆጣጣሪ ቡድን እንቅስቃሴም እያስተጓጎሉ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራንም መሠራት እንደሚገባ ገልፀዋል። 

ሚሊየን ኃይለሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ