1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስ

የሬዲዮ ቴክኖሎጅ ግኝት እና ታሪክ

ረቡዕ፣ የካቲት 2 2014

ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሬዲዮ ግኝትና ምርምር አሁን የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ሊቃውንት ለብዙ ዓመታት ደክመውበታል።ያ በመሆኑ የሬዲዮ ቴክኖሎጂ የብዙ ምርምር ጥረትና ውጤት እንጂ ያንድ ሰው ድንገተኛ ፈጠራ አይደለም። ሆኖም አንድ አንዶቹ ሊቃውንት ከሌሎች በተለየ መልኩ ጉልህ አስተዋጾ ስላደረጉ በታሪክ ተጠቃሽ ናቸው።

https://p.dw.com/p/46kXq
የሬዲዮ ምስል
ሬዲዮ ከቀደምት የመገናኛ ብዙሃን አንዱ ነው።ምስል፦ Maurice Tricatelle/Zoonar/picture alliance

ግኝቱ የበርካታ ሊቃውንት የልፋት ውጤት ነው


በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ሳይንስ ለሰው ልጆች ካበረከታቸው የዓለማችን ታላላቅ ግኝቶች የሬዲዮ ቴክኖሎጅ አንዱ እና ዋነኛው ነው።ሬዲዮ ዛሬ በየትኛውም ቦታ መረጃ ለማግኘት የሚያገለግለን ቴክኖሎጅ ከመሆኑ ከ130 ዓመት ገደማ በፊት  የጥቅል የሃሳቦች እና የንድፈ-ሀሳቦች ሳይንስ ብቻ ነበር።
ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሬዲዮ ግኝትና ምርምር አሁን የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ሊቃውንት ለብዙ ዓመታት ደክመውበታል።ያ በመሆኑ የሬዲዮ ቴክኖሎጂ የብዙ ምርምር ጥረትና  ውጤት እንጂ ያንድ ሰው ድንገተኛ ፈጠራ አይደለም።በግኝቱ የጀርመን የጣሊያን የካናዳ የአሜሪካ ወዘተ ሊቃውንት የየበኩላቸውን አበርክተዋል።ሆኖም አንድ አንዶቹ ሊቃውንት ከሌሎች በተለየ መልኩ ጉልህ አስተዋጾ ስላደረጉ በታሪክ ተጠቃሽ ናቸው።
ከነዚህ ውስጥ በጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ ሃይንሪሽ ሄርዝ፣ቶማስ ኤድሰን፣ ኒኮላ ቴስላ እና ጉሊያሞ ማርኮኒ፣እንዲሁም ሬጅላንድ ፌሲደን ዋናዋናዎቹ ናቸው። የሬድዮ ሞገዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቁት እና የተጠኑት በጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ ሃይንሪሽ  ሩዶልፍ  ሄርዝ በጎርጎሪያኑ በ1886 ሲሆን፤ በዚህ ሄርዝ ፈጠራ ላይ በመመስረት ኒኮላ ቴስላ የተባለ  አሜሪካዊ በ1892 ዓ/ም መልዕክትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ያለ ሽቦ እንዴት ማስተላለፍ እንደሚቻል በሂሳብ ቀመር አሳይቷል።ከዚያ በኋላ የአንዱን ስራ አንዱ በማሻሻል  ጉሊየሞ ማርኮኒ የተባለ የ20 ዓመት ጣሊያናዊ ወጣት በ1895 ዓ/ም  በወላጆቹ ሰገነት ላይ ባደረገው ሙከራ ያለ ሽቦ መልዕክትን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ሩቅ ቦታ የሚያስተላልፍ ስርዓት በተጨባጭ በመገንባት 2.4 ኪሎ ሜትር ያህል እንዲደርስ በማድረግ “ገመድ አልባ ቴሌግራፍ” ብሎ የሰየመውን የመጀመሪያውን ተግባራዊ የሬዲዮ ማስተላለፊያና መቀበያ ፈለሰፈ።የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሶሎሞን በላይ እንደሚሉት ይህ ግኝት ለሳይንስ እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የዓለማችን የስልጣኔ ምልክት ተደርጎ ይታያል።

Guglielmo Marconi sendet als erster telegraphische Signale über den Atlantik
ምስል፦ AP

 ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ እስከ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ  ኒውተንን የመሳሰሉ ሊቃውንት በሬዲዮ ሞገድ ላይ ፍንጭ የሚሰጥ ምርምር  ሲያደርጉ ቢቆይዩም የጀርመናዊ  ሄንርሽ ሄርዝና የጣሊያናዊው የጉሊያሞ ማርኮኒን ያህል ውጤታማ አልነበረም።ያ በመሆኑ በ19ነኛው ክፍለ ዘመን  የተፈለሰፈው የሬዲዮ  ግኝት የፊዚክስ አብዮት መነሻ ነው ይሉታል።ዶክተር ሶሎሞን።
ማርኮኒ በ 1896 በእንግሊዝ ለመጀመሪያው ሽቦ አልባ ቴሌግራፍ የፈጠራ ባለቤትነት መብት  በማግኘት አሁን ድረስ ስሙ ተጠቃሽ ነው።በእንግሊዝ የመጀመሪያውን የራዲዮ ማሰራጫ በመክፈት እንዲሁም የራዲዮ ማምረቻ ፋብሪካ በማቋቋም ስሙ ከሬዲዮ ፈጠራ ጋር እንዲቆራኝ ሆኗል።በ 1909 ዓ/ም የሬዲዮ ማስተላለፊያ  ወይም «ትራንስሚተር»ስልት  ከፈጠሩት ከጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ ከፕሮፌሰር ካርል  ፈርዲናንድ ብራውን ጋር በገመድ አልባ ቴሌግራፊ እድገት ላይ ላደረጉት አስተዋፅኦ  ማርኮኒ በፊዚክስ የኖቤል ሽልማትን ተጋርቷል።  የሬዲዮ ሞገድ ፈጣሪው  ሌላው ጀርመናዊ የፊዚክስ ሊቅ  ሄንሪሽ ሄርዝ  ደግሞ «ሜጋና ኪሎ ሄርዝ »እያልን የምንጠራው የሬዲዮ ሞገድ በስሙ  እንዲሰየም ሆኗል። የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር  ሶሎሞንም ለሀሳቡ ፈጣሪ ለሄንሪሽ  ሄርዝ  የተለዬ አድናቆት አላቸው።

Heinrich Rudolf Hertz

በዋናነት የራዲዮ  ቴሌግራፊ ዘዴ በወቅቱ የተገነባው  ከመርከብ ወደ ባህር ዳርቻ እና ከመርከብ ወደ መርከብ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲሆን፤ ይህም በወቅቱ በሁለት ቦታዎች መካከል ቀላል ግንኙነት እንዲኖር አስችሏል።ታሪካዊቷ የታይታኒክ መርከብ በሰመጠች ጊዜ ይህ የማሪኮኒ ቴክኖሎጅ አብሮ እንደበር መረጃዎች ያሳያሉ።“ገመድ አልባ ቴሌግራፍ” ሆኖ የጀመረው  የሬዲዮ ቴክኖሎጅ ሙዚቃ እና መዝናኛ ከማቅረቡ በፊት ለአውሮፕላን አብራሪዎች ፣ለመርከብ ካፒቴኖች፣ ለመኪና ሹፌሮች፣ ለሕግ አስከባሪዎች፣ ለድንገተኛ አደጋ አገልግሎትና ለሌሎችም የግንኙነት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። 
በ1890ዎቹ  የፊዚክስ ሊቃውንት የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ሞገዶችን ለማጥናት በተጠቀሙባቸው  ስልቶች  ላይ በመመሥረት ጉሊያሞ ማርኮኒ የረዥም ርቀት የራዲዮ ግንኙነት ለማድረግ የመጀመሪያውን መሣሪያ ከሰራ በኋላ፤ በጎርጎሮሳውያኑ ታህሳስ 23 ቀን 1900 ካናዳዊው ፈጣሪ ሬጂናልድ  ፌሴደን በኤሌክትሮ ማግኔቲክ ሞገድ ከአንድ ማይል (1.6 ኪሎ ሜትር) ርቀት ላይ በተሳካ ሁኔታ በገመድ አልባ ስልክ ድምፅ ልኳል።ከስድስት ዓመታት በኋላ በ1906 የገና ዋዜማ በአሜሪካ  በሽቦ አልባ ስርጭት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለህዝብ በማስተላለፍ  የመጀመሪያው ሰው ሆነ።
በጎርጎሪያኑ በ 1910 እነዚህ የተለያዩ ሽቦ አልባ ስርዓቶች "ሬዲዮ" እየተባሉ መጠራት የጀመሩ ሲሆን፤  KDKA የተባለው  የመጀመሪያው የንግድ ሬዲዮ በአሜሪካ በፒትስበርግ ከተማ በ1920 ዓ/ም ስርጭት እንዲጀምር ተደርጓል።ስርጭቱ የጀመረው የምርጫ ቀን  ስለነበረም ሰዎች ፕሬዝዳንታዊ ፉክክር ውጤት በጋዜጣ ላይ ከማንበባቸው በፊት በሬዲዮ በመስማታቸው የራዲዮ ሃያልነት እንዲታይ ሆኗል።በዚህ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት በማግኘቱም በ1930ዎቹ፣ በዩናይትድ ስቴትስ  አሜሪካ እና በአውሮፓ 60 በመቶ የሚሆነው ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ሬዲዮ ነበረው።

Old radio set, video still Altes Radiogerät Radioempfänger
ምስል፦ AP

በ1933 ዓ/ም የአሜሪካዊው ኤድዊን ኤች.  አርምስትሮንግ በኤፍ አም ሬዲዮ ፈጠራ ባለቤትነት ያገኘ ሲሆን፤ በ1939 የመጀመሪያውን ሙሉ የኤፍ ኤም ጣቢያ ገንብቶ  በማሳቹሴት 400 ጫማ ከሚረዝም ማማ ላይ የሙከራ ስርጭት አድርጓል።ራዲዮ ከመፈጠሩ በፊት፣ በአለም ላይ ምን እንደሚካሄድ የሚፈትሽ ጎግል አልነበረም። በየምሽቱ ዜና  የሚያሰራጩ ቴሌቪዥኖችም እንዲሁ። ያ በመሆኑ እያንዳንዱ ሀገርና ህዝብ የተገለለ ነበር።የሬድዮ መምጣት ግን የዓለም ህዝቦች እንዲተሳሰሩ አድርጓል።በዚህ የተነሳ በዓለም ዙሪያ በርካቶች በየቀኑ በሬዲዮ ዙሪያ በመሰባሰብ ከጓደኞቻቸው እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ሆነው ዜና መጠበቅ የተለመደ ነበር።ዶክተር ሶሎሞን እንደሚሉት ሬዲዮ ለሳይንስ እድገትም መሰረት ጥሏል።
ሬዲዮ  ለሰው ልጆች እድገትና መሻሻል፣  ለችግሮች መፍትሄ ለመሻት፣ ህይወትን ለመታደግ፣የዕለት ተዕለት ኑሮን የተቃና ለማድረግ የሚያስችሉ መረጃዎችን ይሰጣል። ዓለምን ለማገናኘት፣ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪ ልማት፣ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍም  ሬዲዮን የሚስተካከለው አልነበረም።ለዚህም ነው የሬዲዮ ፈጠራ ዓለምን የቀየረ ፈጠራ ነው የሚባለው።

ይህ ዓለምን  የለወጠው የሬዲዮ ፅንሰ-ሐሳብ ምንም እንኳን ግንኙነቱ የመጀመሪያው ሬዲዮ ከተፈጠረበት ጊዜ በጣም የተለየ ቢሆንም የሬዲዮ ስርጭት  ድንበር ተሻግሮ የመድረስ አቅም ያለው በመሆኑ፤የበይነመረብ መዳረሻ ሲዘጋ ፣ የስልክ እና የመብራት መቋረጥ ቢያጋጥም መረጃ ለማግኘት ሬዲዮ አሁንም ተመራጭ ነው። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ በተመለከተ  የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ዛሬም ድረስ  ራዲዮ  በዓለማችን ወሳኝ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።ራዲዮ ለአጠቃቀም ቀላል ፤ዋጋውም ርካሽ በመሆኑ በቀላሉ ተደራሽ በመሆን  የማህበረሰቡን መረጃ የማግኘት ዕድል ጨምሯል።በተለይ በታዳጊ ሀገራት። 

Radiohörer in Afrika
ምስል፦ Nicholas Kajoba/Xinhua/imago images

በሌላ በኩል የራዲዮ ቴክኖሎጂ ከባትሪ የለሽ ራዲዮ/ሪስታል ራዲዮ/ ወደ ዲጅታል ከዚያም  ወደ ሳተላይት ራዲዮ ተሸጋግሯል። የቴክኖሎጂ ለውጦች በሬዲዮ ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ  ቢሆንም፤ እንደማንኛውም ኢንደስትሪ ሬዲዮም ወደ ዲጂታል አብዮት  በተመሳሳይ አቅጣጫ መሄድ  ጀምሯል።ሌሎች የቴክኖሎጅ አማራጮችን በመጠቀም የመደመጥ እድሎቻቸውን በማስፋት የሬዲዮ ጣቢያዎች እድገታቸው አብሮ ቀጥሏል።
በአጠቃላይ ሬዲዮ  ሀብታም፣ ድሃ፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ ወጣት፣ አዋቂ ሳይል ወይም የዕድሜ ፣ የጾታ እና የ ዘር ልዩነት ሳይገድበው  ለሁሉም ተደራሽ መሆን ይችላል። ይህ ለሰው ልጆች የሚሰጠው ጥቅም ተመዝኖም የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ከርጎሪያኑ 2011 ዓ/ም ጀምሮ  በየ ዓመቱ  በዓለም አቀፍ ደረጃ የሬዲዮ ቀን እንዲከበር አድርጓል።ዘንድሮ በጎርጎሪያኑ የካቲት 13 ቀን የፊታችን እሁድ ለ11ኛ ጊዜ ተከብሮ ይውላል።
 ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እንደተወደደ የዘለቀው ሬዲዮ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ ጠቀሜታው እና ተፈላጊነቱ  አሁንም ድረስ ቀጥሏል። የዶቼ ቬለ ራዲዮም ከጀርመን ቦን ከተማ  መረጃዎችን ወደ እናንተ ማድረሱን እንዲሁ ይቀጥላል።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ