1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
መገናኛ ብዙኃንኢትዮጵያ

«ራዲዮ የብርቅ እቃ ነው»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ የካቲት 8 2016

ለቻይና ወጣቶች ራዲዮ ያለው ትርጓሜ እየቀነሰ ነው። በሀገሪቱ ከ2000 በላይ የራዲዮ ጣቢያዎች ቢኖሩም ወጣቶች መረጃ የሚፈልጉት የኦንላይን መገናኛ ብዙኃን ላይ ነው። ለኢትዮጵያውያን ወጣቶችስ ራዲዮ ምን ያህል ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ነው?

https://p.dw.com/p/4cStG
ራዲዮ የያዘ ሰው
ራዲዮ አሁንም በሰፊው ጥቅም ላይ ከዋሉት የመገናኛ ብዙሃን ዓይነቶች አንዱ ነውምስል Tsvangirayi Mukwazhi/AP Photo/picture alliance

ራዲዮ በወጣቱ ዘንድ ያለው ተሰሚነት ምን ይመስላል?

መረጃ በራዲዮ ሲሰራጭ ከ100 ዓመት በላይ ሆኖታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በ 1928 የተጀመረው የራዲዮ ፕሮግራም ስርጭት 88 ዓመታት አስቆጥሯል። ባለፈው ማክሰኞ ለ13ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለውን የዓለም የራድዮ ቀን  በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎርጎሮሲያኑን የካቲት 13 ቀን ታስቦ እንዲውል የወሰነው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ነው። ዛሬ የራዲዮ ሚና ምን ይመስላል?

የዓለማችን ክፍል  ዋነኛው የመረጃ ምንጭ ነው?

 እንደ ተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) ከሆነ ቴክኖሎጂው በፍጥነት በሚለዋወጥበት በአሁኑ ጊዜ እንኳን  ሬዲዮ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አስተማማኝ እና በሰፊው ጥቅም ላይ ከዋሉት የመገናኛ ብዙሃን ዓይነቶች አንዱ ሆኖ የሁለተኛውን ክፍለ ዘመን አገልግሎት ጀምሯል።

ወጣቶች ምን ይላሉ?

አስተያየታቸውን ለዶይቸ ቬለ ያካፈሉ አፍሪቃውያን ወጣቶች ራዲዮን ሲገልፁ ፦  "የእለት ተእለት እንቅስቃሴዬን ሳከናውን ራዲዮ አብሮኝ አለ።» ፣ "በአብዛኛው ቴሌቪዥን በማያገኙ የገጠር አካባቢዎች ሬዲዮ ብዙ ጥቅሞች አሉት " ፣ "የፈለኩት ቦታ ይዤው መሄድ እችላለሁ። " ፣ " በትንሽ ገንዘብ ሬዲዮ ገዝቶ መረጃ ማግኘት ይቻላል። " ይላሉ።

ይሁንና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚገኝበት አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ዘንድ ራዲዮ የመስማት ልማዱ እየተቀዛቀዘ ያለ ይመስላል። አስተያየታቸውን በፁሁፍ ካካፈሉን ወጣቶች መካከል፣ 
ወንድም ኑረዲን « እኔ ዜናዎችን የማገኘው በኢንተርኔት ነው ምክንያቱም በፈለኩ ሰአት የፈለኩትን ዜና ስለማገኝ ሬድዬ ከቤታችን ከጠፈች ሰነበተ» ይላል ሀዋሳ ባባ « ራዲዮ
እየቀረ ነው። ምናልባት ብዙ የኢንተርኔት አገልግሎት በማያገኙ ገጠር አካባቢዎች የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች የመደመጥ ዕድል አላቸው። እንደ መዝናኛም ስለሚያገለግሉ።» ባይ ነው። ሳሚ
ራዲዮ ምሰማው የስፖርት ዜና ካለ ነው። እሱም አርሰናል ሲያሸንፍ ብቻ ። ሌላው ደሞ የበአል ዋዜማ እና የበአሉ ቀን የበአል ዘፈኖች ስለሚመቹኝ ብቻ ነው ሬዲዮ የምሰማው ።» ብሎናል። 
ላለፉት አራት አመታት በሸገር ሬዲዮ እና በሐራምቤ ሬዲዮ በዜና አምባቢነት እና በፕሮግራም አዘጋጅነት እየሰራ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዮሴፍ ዳሪዮስ ራዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሚና እንዲህ ሲል ይገልፃል። « ራዲዮ ተከትለውት ከመጡ ቴክኖሎጂዎች አንፃር ሊጥሉት የሚጥሉ ነገሮች በዝተው ነበር። ቴሌቪዥን ፣ኢንተርኔት ስልክ...እነዚህን ነገሮች በሙሉ ተሻግሮ ራዲዮ እዚህ ደርሷል። አሁንም እንደቀደመው ጊዜ አድማጭ አለ ለማለት ባያስደፍርም ተመርጠው የሚሰሙ ፕሮግራሞች እንዳሉ ርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል» ይላል።

በገጠር አካባቢ የራዲዮ ተሰሚነት

ሁለት ወንዶች ቁጭ ብለው ራዲዮ ሲያዳምጡ
በእድሜ ከፍ ያሉ አፍሪቃውያን ዘንድ ራዲዮ መከታተል አሁንም የተዘወተረ ነውምስል Pascal Deloche/Godong/picture alliance

በሸዋ ሮቢት አካባቢ ንዋሪ የሆነ እና ስሙን ባይገልፅ የመረጠው ወጣት ደግሞ በገጠሩ አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች ሁለት ከፍሎ ነው የሚያየው « ከተማ ቀመስ የሆኑ ገጠራማ አካባቢዎቻችን ራዲዮም ቴሌቪዥንም ይከፍታሉ። በእድሜ ከፍለን ስናየው በእድሜ ከፍ ያሉት ራዲዮ መከታተል ያዘወትራሉ። ወጣቱ ግን ኢንተርኔት ሲኖር እዛ ላይ ያተኩራል። መብራት የሌለባቸው አካባቢዎች ከተማ ሲመጡ ስልካቸውን ቻርጅ እያደረጉ ወይም በፀሀይ ብርኃን እየሞሉ ራዲዮ የማዳመጥ ነገር አለ» ይላል። በግሉ ቴሌቪዥን እና መረጃ በኢንተርኔት ለማግኘት እንደሚያዘወትር ገልፆልናል።

አድያም ነግድ «ስራዬ ብየ ለመረጃ ወይም ለመዝናኛ ከአዳመጥኩ 10 ዓመት አና ከዚያ በላይ ይሆነኛል።» ብሎናል። ፋንታሁን « ራድዮን ማዳመጥ ከተዉኩ 4 ዓመት ሆኖኛል። ምክንያቱም በኦንላይን እና በኢንተርኔት ስለምከታተል ነዉ ይላል። ባንቲ« አብዛኛው የራዲዮ ሚዲያ ገለልተኛ ስላልሆኑ ማዳመጥ አቁሚያለሁ ምክንያቱም የመንግስት ልሳን ናቸው ። ካሳዬ ተስፋዬ
«ራዲዮ ማዳመጥ ካቆምኩ ቆየሁ ምክንያቱ ደግሞ የመንግስትን ደካማ ጎን አይዘግቡም»

መቅደላዊት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናት።  «እውነቱን ለመናገር ሬዲዮ አልከታተልም» ትላለች።  የእሷስ ምክንያት ምን ይሆን? «  ጠዋት ስራ ላይ ነው የምውለው ከዛ ተመልሼ ራዲዮ የምሰማበት ጊዜ የለኝም» ትላለች። መረጃ የምትፈልገው የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ነው። ሌሎች ወጣቶችም በቀላሉ እና በፈለጉበት ሰዓት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መረጃ ስለሚያገኙ« ወደእዛ የሚሳቡ ይመስለኛል» ባይ ናት።
ቻይና ውስጥ ከ2000 በላይ የራዲዮ ጣቢያዎች ቢኖርም 98 በመቶ የሚሆነው ወጣት መረጃ የሚፈልገው ከቲክቶክ ጋር ተመሳሳይ የሆነው የቻይና መተግበሪያ  ዶይን ወይም በፖድካስት መልክ የሚቀርቡ መረጃዎችን ኢንተርኔት ላይ በመፈለግ ነው።  

ጊኒ ቢሳው ራዲዮ የሚያዳምጥ ነጋዴ
ጊኒ ቢሳው ራዲዮ የሚያዳምጥ ነጋዴ እጎአ 2012 ዓ ምምስል Andre Kosters/dpa/picture alliance

«ራዲዮ የብርቅ እቃ ነው»

 ጋዜጠኛ ዮሴፍ እንደሚለው የራዲዮ ተሰሚነት አሁንም ሊቀጥል የቻለው ከቴክኖሎጂው ጋር የመጡ አማራጮችን ማካተት ስለተቻለ ነው። « በዩቲውብ ፣ ቲክቶች እና ፌስቡክ የሚተላለፍበት ሁኔታ አለ። አንዳንዴም በስልክ ላይ የሚተላለፍበት አማራጭ ስላለ አሁንም ድረስ የራሱ አድማጮች እንዲኖሩት አድርጎታል» ይላል። ራዲዮ አሁንም በተለይ በገጠራማው አካባቢ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚናገረው ዮሴፍ « አሁንም ድረስ ራዲዮ አለ ማለት እውነት ነው ማለት ነው። ዩቲውብ እና ቲክቶክን ግን የመጠራጠር ሁኔታ አለ። ገጠር ደሳሳ የምትባል ጎጆ ውስጥ ራድዮ አሁንም የብርቅ እቃ ነው።» ከምንም በላይ ደግሞ « በአይነ ስውራን ዘንድ ራዲዮ ያለው ተቀባይነት ጨምራል» ይላል። ጋዜጠኛ ዮሴፍ ዳሪዮስ።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ