1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራያ አላማጣና አካባቢው ተፈናቃዮች ይዞታ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2016

የራያ አላማጣ ተፈናቃዮች ብዙዎቹ በወቅቱ ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አቅራቢያ በአንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠልለው የቆዩ ቢሆንም ከቀናት በኋላ እንዲወጡ መደረጉን በዋጃ ከተማ በአንድ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ ገልጠዋል፣ ወደ አዲሱ መጠለያ የደረሱት ጥቂት መሆናቸውን የሚናገሩት እኚህ ተፈናቃይ ሌሎቹ በየቦታው ተበትነዋል ነው ያሉት፡፡

https://p.dw.com/p/4fJKp
 የተፈናቃዮች መጠለያ በጃራ
የተፈናቃዮች መጠለያ በጃራምስል Alamata City Youth League

የራያ አላማጣና አካባቢው ተፈናቃዮች ይዞታ

ባለፉት ሳምንታት ከራያ አላማጣና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በቆቦ ከተማ አቅራቢያ በአንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች ከቦታው እንዲለቅቁ መደረጋቸውን ተፈናቃዮች ተናገሩ፣ የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ ተመልሰዋል ቢሉም፣ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ተፈናቃዮች  ተበትነዋል ይላሉ፣ የራያ ባላና ወፍላ ተፈናቃዮች ደግሞ እርዳታ አላገኘንም ብለዋል፡፡ሰሞኑን በተቀሰቀሰው የአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ብዙዎቹ ወደ አጎራባች ወረዳዎች መፈናቀላቸውን ብዙሐን መገናኛ ዘግበዋል፣ ዓለም  አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም አረጋግጠዋል፡፡ከራያ አላማጣና ሌሎች ወረዳዎች ብዙ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው

የራያ አላማጣ ተፈናቃዮች ብዙዎቹ በወቅቱ ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አቅራቢያ በአንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠልለው የቆዩ ቢሆንም ከቀናት በኋላ እንዲወጡ መደረጉን በዋጃ ከተማ በአንድ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ ገልጠዋል፣ ወደ አዲሱ መጠለያ የደረሱት ጥቂት መሆናቸውን የሚናገሩት እኚህ ተፈናቃይ ሌሎቹ በየቦታው ተበትነዋል ነው ያሉት፡፡“ ስጋት ያለበት ብዙ ነው፣ ትምህርት ቤት ነው እንደገና መጥተን የተጠለልን 8 እና 9 ሺህ እንሆናለን፣ ብር ያለው ሰው በቆቦም  በሌሎች ከተሞችም ሄዷል፣ አላማጣ ተመልሶ የሄደም አለ፡፡” ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በእርግጥ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ ከተማ የተመለሱ ቢሆንም ባለው ወከባና ስጋት ተመልሰው ወደየቦታው ሄደዋል ብለዋል፡፡“ልጃችሁ የብልፅግና ደጋፊ ነው፣ በማንነት ዙሪያ ታጋይ የሆነውን፣ በማንነት ጥያቄ ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ነው በማለት ወላጆቻቸውን እያሰቃዩ፣ ቤተሰብን እሰቃዩ ስለሆነ፣ ተመልሶ የሄደው ብቻ አይደለም  ተጨማሪ ተፈናቃይ ነው እየመጣ ያለው፣ አሁን የተወሰነ ተፈናቃ ዋጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አለ፣ ከዚያ ውጪ ያለው ግን ተበትኖ የሚሰበስበው አጠቶ በቆቦ፣ በወልዲያ፣ በደሴ ከተሞችና በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ተበትኖ ነው ያለው፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡የአማራ ክልል መንግሥት «ህወሓት ጦርነት ከፍቶብኛል» አለ

የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ባለፈው ሳምንት 7 ሺህ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች እርዳታ ተስጥቷል ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮች ለምን ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ አስፈለገ ተብለው የተጠየቁት አቶ ኃይሉ፣ 4 ምክንቶችን አስቀምጠዋል፣ ተፈናቃዮች ተበትነዋል የሚለውን ስሞታም አይቀበሉም፣ በቁጥር ባይገልፁትም አብዛኛው ተፈናቃይ ወደ ቦታው ተመልሷል ባይ ናቸው

 የተፈናቃዮች መጠለያ በጃራ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት
የተፈናቃዮች መጠለያ በጃራ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ምስል Alamata City Youth League

“...ህዝቡ ወደ ቦታው እንዲመለስ ስራ ሰርተናል አሁንም ህዝቡም እንዲመለስ አድርገናል፣ በቆቦና ሌሎች ከተሞች ላይ ሆኖ የተፈናቃይ መጠለያ ተሰርቶ እዛው መጠለያ ውስጥ እንዲኖር አንፈልግም፡፡” ብለዋል፡፡ አቶ ኃይሉ ለዚህ 4 ምክንቶችን አስቀምተዋል። አንድ   ወረርሽኝ ሊከስት እንደሚችል ጠቁመዋል፣ ሁለት      ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፣ ሦስት   የፖለቲካ ሴራ ሊሰራ ይችላል ብለዋል፣ አራተኛ   ህዝቡ ፖለቲካዊ ትግል  ማድረግ ያለበት በአለበት ከተማ መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡ ከወደ አላማጣ የመጣው ተፈናቃይ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ መደረጉን የሚናገሩት ከንቲባው በዋጃና በቆቦ ከተሞች ውስጥ ያሉት ተፈናቃዮችም በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አላማጣ እንደሚመለሱ ነው አቶ ኃይሉ የተናገሩት። በትግራይና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን ስለመፍታት የምሁራን አስተያየትቆቦ ውስጥ የነበረው የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ መፍረሱን የገለጡት ኃላፊው ከሁሉም በላይ “ነፃነታችን እንፈልገዋልን” ብለዋል፡፡

የራያ ባላ፣ የወፍላና ከረም ተፈናቃዮች ደግሞ ያለ እርዳታና መጠለያ በችግር ላይ እንደሆኑ አንድ ተፈናቃይ አስረድተዋል፡፡

“...ኮረም፣ ወፍላ ዛታም ሰብአዊ ድጋፍ እስካሁነን አልተገኘም፣ ህዝቡ በየበረንዳው፣ በየቤተክርስቲያኑ፣ በየ መስጊዱ ነው ያለው ማንም የጠየቀን የለም፡፡”ጉዳዮን አስመልክተን ከሰሜን ወሎ ዞንና ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች  ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ቢሮ  (UN-OCHA) በአካባቢው ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡

አለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ