1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሞት ፍርድን የሚጠባበቁት ኢትዮጵያዉያን በሳዑዲ እስር ቤት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2018

ሳዑዲ አረቢያ ሕገወጥ ያለቻቸዉን ወደ 14,855 የዉጭ ዜጎች ከሀገሯ አስወጣች። ከተጠረዙት መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን መሆናቸዉ ታዉቋል። በአሁኑ ወቅት ከ 65 እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በተለይም ጫትን በማጓጓዝ ተከሰው የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን ድርጅቱ አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/5DUpH
Symbolbild Gefängnis Kuba
ምስል፦ p79/ZUMA/picture alliance

የሞት ፍርድን የሚጠባበቁት ኢትዮጵያዉያን በሳዉዲ እስር ቤት

የሞት ፍርድን የሚጠባበቁትን ጨምሮ ሰነድ አልባዎቹ ኢትዮጵያዉያን በሳዉዲ

ሳዑዲ አረቢያ ሕገወጥ ያለቻቸዉን ወደ  14,855 የዉጭ ዜጎች ከሀገሯ አስወጣች። ወደ  11,300 የሚሆኑትን ደግሞ በቁጥጥር ስር ማዋሏን የሀገሪቱ  ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታዉቋል። በቁጥጥር ሥር ከዋሉት እና ወደ ሀገር ቤት ከተጠረዙት መካከል 54 በመቶ  የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን መሆናቸዉ ታዉቋል። እጽ በማዘዋወር እና በሌሎች ወንጀሎች ተከሰዉ በሳዉዲ እስር ቤቶች የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉም ተዘግቧል። በቅርቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሳዉዲ አረብያ እስር ቤት የሚገኙ እና የሞት ቅጣት ለሚጠብቃቸዉ ኢትዮጵያዉያን መፍትሄ እንዲፈለግ ሲል ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፉ ይታወቃል።   

ከ 65 እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርድን እየተጠባበቁ ነዉ

 ሳዑዲ አረቢያ ካባረቻቸዉ እና እስር ቤት ካጎረቻቸዉ ሕገ-ወጥ ካለቻቸዉ ነዋሪዎች መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን መሆናቸዉን የሳዉዲ አረብያ ጋዜጣ ባለፈዉ ሰሞን ዘግቧል።  በሳዉዲ አረብያ ያለ መኖርያ ፈቃድ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ላይ አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ሁኔታ እየተከሰተ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ያመለክታል።  በአሁኑ ወቅት ከ 65 እስከ 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በተለይም ጫትን በማጓጓዝ ተከሰውየሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን ድርጅቱ አስታዉቋል። በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መብት በማስከበር፣ የወገኖችን ስቃይ በመዘገብ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ የሚታወቀዉ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ፤ እንደሚለዉ ወደ ሳዉዲ የሚሄደዉም የሚባረረዉም፤ ብሎም የሞት ፍርዱን የሚጠባበቀዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ብዙ ነዉ።

ፎቶ ከማኅደር ፤ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሳዉዲ የመን ድንበር
ፎቶ ከማኅደር ፤ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሳዉዲ የመን ድንበር ምስል፦ Khaled Abdullah/REUTERS

«ወደ ሳዉዲ የሚሄደዉ እና የሚመለሰዉ ሰዉ እንዲሁም የሚመለሰዉም ሰዉ ቁጥር በጣም ከፍተኛ  ነዉ። የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት በሳዉዲ እስር ቤት የሚገኙ አንገታቸዉን የሚቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ 200 በላይ ናቸዉ መፍትሄ ይፈለግ ሲል ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደብዳቤ ጽፋል።» አዎ ከሳምንት በፊት በሳዉዲ አረብያ ይፋ እንደሆነዉ፤ ከ 14 ሺህ በላይ ሕገወጥ ነዋሪዎች፤ በሳዉዲ አረብያ ተይዘዋል፤ ከ 13 ሺህ በላይ ደግሞ በቁጥጥር ስር ዉለዋል። ከእነዚህ መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ ተብሏል።  

መጭዉም ሆነ ከሳዉዲ ተጠራዡ እጅግ ብዙ ነዉ

ፎቶ ከማኅደር፤ ህገወጥ ስደተኞች በሳዉዲ
ፎቶ ከማኅደር፤ ህገወጥ ስደተኞች በሳዉዲ ምስል፦ picture-alliance/dpa/Str

 « 14 ሺህ የተባለዉ፤ ምናልባትም የአንድ ሳምንት ፤ የሁለት ሳምንት ሊሆን ይችላል እንጂ፤ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሰዉ ነዉ በአንድ ወር ዉስጥ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከዉ። ነገር ግን እስር ቤት ያሉት ኢትዮጵያዉያንቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ድንበር ጥሰዉ ሳዉዲ አረብያ የሚገቡ ኢትዮጵያዉያኖች ቁጥር በቀን እስከ 3000 ሺህ ይገባሉ ተብሎ እየተገመተ ነዉ ያለዉ። የታሳሪዎችም ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነዉ።» ጋዜጠኛ ነብዩ ሳዉዲ እስር ቤት ያሉት ምናልባትም የሞት ቅጣታቸዉን የሚጠባበቁ መረጃ አድርሰዉሃል ፤ እና ምንድን ነዉ የሚሉት?

« በሳዉዲአረብያ የኢትዮጵያዉያኑን ጉዳይ እከታተል ነበር መረጃዎችም ይደርሱኛል። ከእስር ቤትም ቀጥታ የሚደዉሉልኝ አሉ። የመንግሥት ያለህ እያሉ ይማፀናሉ  በጠባብ ክፍል እስከ 300 – 400 ሰዉ ታጉሮ ነዉ የታሰረዉ የእስር ቤት አያያዙ በጣም መጥፎ ነዉ። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ጉዳይ እንዴት ነዉ ማስቆም የሚችለዉ ?

«መንግሥት ምንም ማድረግ አይችልም። ምናልባት በዲፕሎማሲ ከሞከረ ነዉ ሃገሪቱ ግን እፅ ሲያዘዋዉሩ ጫት ሲያዘዋዉሩ የተገኙ፤ ይታሰራሉ አንገታቸዉን ይቀላሉ የሚል አዋጅ አዉጥቶ አጽድቋል።»  ድህነትን፤ በተለያዩ ክልሎች የሚታየዉን ጦርነትን ሸሽተዉ ሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር ወደ 750,000 ይገመታል። አብዛኞቹ  ኢትዮጵያውያን በግንባታ፣ በግብርና እና በቤት ውስጥ አገልግሎት ይተዳደራሉ። ከነዚህ መካከል በጣም ጥቂቶች የሥራ ፈቃድ ያላቸዉ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ሰነድ አልባ ናቸዉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ