1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ወለጋና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች ሁኔታ

ዓርብ፣ ሰኔ 24 2014

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ዓለማየሁ በአርጆ ጉደቱ ከተማና ቶሌ ቀበሌ ለተጠለሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ መድረሱን ተናገሩ፡፡ ትናንት 7 ተሳቢ መኪና ርዳታ መላኩን ጠቁመዋል፡፡ በቶሌ ቀበሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ድጋፍ እንደ ደረሳቸው የተናገሩ ሲሆን ወደ ሌሎች ስፍራዎች የሸሹ ደግሞ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4DWis
Äthiopien  Metekel, Wonbera, Gondi Kebele
ምስል Negassa Desalegn/DW

ከምዕራብ ወለጋና ጊምቢ ለተፈናቀሉ የሚደረግ ሰብአዊ ዕርዳታ

ሰኔ 11/2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቦሎጅጋንፎይ ወይም (ሚዥጋ) ወረዳ "ሴኔ" ቀበሌ በደረሰው ጥቃት 12000 የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸውን "የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ" ወይም በቀድሞ ስሙ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ 

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት አለማየሁ በአርጆ ጉደቱ ከተማ እና ቶሌ ቀበሌ ለተጠለሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በትናትው ዕለት 7 የሚደርስ ተሳቢ መኪና ዕርዳታ መላኩን ጠቁሟል፡፡ በቶሌ ቀበሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ድጋፍ እንደ ደረሳቸው የተናገሩ ሲሆን ወደ ሌሎች ስፍራዎች የሸሹ ደግሞ ድጋፍ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡

በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌና እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቦሎጅጋንፎይ ወረዳ ሴኔ ቀበሌ የዛሬ 2 ሳምንት ገደማ  ደርሶ በነበረው ጥቃት ከ338 ሰዎች ህይወት ማለፉን መንግስት ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡ በሰው እና ንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናላቸውን የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የምእራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ  አመልክተዋል፡፡ የቡሳ ጎኖፋ ምዕራብ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ነጻነት አለማየሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈናቀሉ 4ሺ በላይ ዜጎች በምስራቅ ወለጋ ዞን አርጆ ጉደቱ የተጠለሉ ሲሆን ከ7ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ በቶሌ ቀበሌ እንደሚገኙ ለዶይቼቬለ ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች የኢትየዮጵ ቀይ መስቀል ማህበር እና የክልሉ መንግስት ሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያ ቁሳቀሶችን ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በትናትናው ዕለትም ሰብአዊ ድጋፍ  ወደ ቶሌ ቀበሌ ማድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሰኔ 11/ 2014 ዓ.ም በበቶሌ ቀበሌ በተከሰው ጥቃት አራት ልጆቻቸውን እንዳጡ የነገሩን ነዋሪ በስፋራው ምን የተረፈላቸው ንብረትም ሆነ ምርት እንደሌለ ጠቁሟል፡፡ በሌላ ቦታ ለሚገኙ ለተፈናቀሉ ዜጎች ብርድ ልብስን ጨምሮ የተወሰነ ስንዴና ዱቄት እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱ ወቅት በደረሳባቸው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል እንደሚገኙ  የነገሩን ሌላው ነዋሪ ደግሞ   የመጣ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ በደረሰው ጥቃት በርካቶች ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሸሹ ሲሆን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የመጡ በርካታ ሰዎች ከዘመድ ጋር ተጠግተው  እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ ባለፉት 14 ቀናት የደረሳቸው ድጋፍ ሆነ ያነጋገራቸው ሰው አለመኖሩንም ወደ ባምባሲ የሸሹ ነዋሪዎች ተናግሯል፡፡

በጊምቢና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ ላይ በሚገኙ ቶሌና ሴኔ ቀበሌዎች ውስጥ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም በደረሰው ጥቃት 338 ሰዎች ህይወት ማለፉን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራርያ አስረድተዋል፡፡ ከአሁን በፊት የጎላ የጸጥታ ችግር ይታይባቸው በነበሩ የአማራ፣ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከነበሩት የተወሳሰበ የጸጥታ ሁኔታ አኳያ የተሻለ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ