1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራባውያን መድሃኒት እና የአፍሪቃውያን እልቂት

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2016

በጎርጎርሳውያኑ 1870 ዎቹ እና 80 ዎቹ ውስጥ ለሞቃታማ አካባቢዎች የሕክምና ምርምር ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ጊዜ ነበር። ጊዜው ደግሞ የአውሮጳ ሃገራት መላው አፍሪቃን ለመቀራመት የሚሯሯጡበት ወቅትም ነበር።

https://p.dw.com/p/4dcxi
Teaser Shadows of german colonialism AMH
ምስል DW

በጎርጎርሳውያኑ 1870 ዎቹ እና 80 ዎቹ ውስጥ ለሞቃታማ አካባቢዎች የሕክምና ምርምር ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ጊዜ ነበር። ጊዜው ደግሞ የአውሮጳ ሃገራት መላው አፍሪቃን ለመቀራመት የሚሯሯጡበት ወቅትም ነበር።  እናም ቡርዣዎቹ አፍሪቃ ውስጥ እግራቸውን እስከመጨረሻ የማቆየት ፍላጎት ባይኖራቸው እንኳ በዚያ ምድር የሚኖሩት ግን  መትረፍ እንዳለባቸው አለማሰባቸው በአጋጣሚ አልነበረም። አፍሪቃ ውስጥ በተለይ በማዕከላዊ የአህጉሪቱ ክፍል ተገኝተህ ከሆነ ከተረፉቱ ወገን ነህ ማለት ነው።  ከዚህ ራቅ ወደሚለው የቀደመው ጊዜ መለስ ስንል ፤ ገና በቅኝ ግዛት ስር ከወደቁ ብዙም ባልቆዩት በካሜሩን እና ቶጎ የሚገኙ ነጮችን የትኩሳት በሽታ ያገኛቸው ከባህር ዳርቻ አካባቢዎች ርቀው በማዕከላዊ አካባቢዎች ለመስፈር ጥረት ባደረጉበት ወቅት ነበር። በወቅቱ በሽታው ብርቱ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት የጀርመን የቅኝ ግዛት ፖሊሲ እስኪወጣለትም ደርሷል። 

« በ19ኛው ክፍለዘመን በአፍሪቃ በተለይ በምስራቅ አፍሪቃ የነጮች መቃብር በመባል ይታወቅ ነበር። በወቅቱ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በሽታ ለእልቂታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል።»

  ፊሊሞን ምቶይ በምስራቅ አፍሪቃ የጤና ታሪክ ተመራማሪ እና ተንታኝ ናቸው ።

 

«ጀርመኖቹ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ በተለይ ወደ ታንዛንያ ከመምጣታቸው በፊት የሀገሬው ነዋሪ እራሱ በፈጠረው አካባቢ በራሱ እና  በበሽታው መካከል ያለውን የስነምህዳር ሚዛን ለማመጣጠን ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለት ነበር።

በሽታውን እንዴት እንደሚለዩ እና እንዴት መቀነስ እንዳለባቸው ያውቃሉ ። ግን ደግሞ በሽታን የሚያሰራጭ ቢሆን እንኳ የስነምህዳር አካባቢን መረበሽ አይፈልጉም ። »

 « ጀርመኖቹ ግን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ደኑን አወደሙት ። ይህ ደግሞ እንደ ንዳድ እና ቸነፈር አይነት አስከፊ በሽታዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል።»

አፍሪቃውያኑ ከአውሮጵውያኑ ጋር በተገናኙ ቁጥር ለአዳዲስ በሽታዎች ይጋለጡ ጀመር ። በእርግጥ ነው እንደ ወባ ያሉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች ቀድሞውኑ የነበሩ ናቸው ። ነገር ግን አውሮጳውያኑ እንደ ፈንጣጣ ካሉ ቀደም ሲል የለመዷቸው  በሽታዎችን የመቋቋም አቅም የነበራቸው ጥቂት አፍሪቃውያን ብቻ ነበሩ ። እናም አውሮጳውያን ሀኪሞች እንዴት አድርገው አዲስ መድሃኒት መስራት እንደሚችሉ ማሰብ ነበረባቸው ። ነገር ግን ታማሚዎች ለምን ያህል ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ ? በጣም ጥቂት ጊዜ ።

 በ1880ዎቹ ውጤታማ የፈንጣጣ በሽታ ክትባት አውሮጳ ውስጥ ይገኝ ነበር። ነገር ግን የቅኝ ግዛት ሐኪሞች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው አልያም ውጤታማ ያልነበሩ ክትባቶች እንዲሰጡ ያደርጉ ነበር። ሀኪሞቹ በየአካባቢው ለሚታዩ በሽታዎች በእጃቸው ባለው ነገር ለማከም ከመሞከር ያለፈ ጥረት አያደርጉም ነበር። የቅኝ ግዛቶችም የምዕራባውያንን ክትባቶች የመቀበል ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ተንታኝ ቶዬም ፎጋንግ የጀርመን የቅኝ ግዢ ሐኪሞች በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ የጀመረውን የቶጎ ላንድ የፈንጣጣ ወረርሽኝ  እንዴት እንደተቆጣጠሩት ይናገራሉ።

ክትባቶች የመጀመሪያዎቹ የበሽታ መከላከያ መርሃ ግብር ነበሩ ፤ በተጨማሪም ሌሎች በሽታ የመከላከያ መርሃ ግብሮችም ተዘርግተዋል 

የባህል መድሃኒት አዋቂዎች እና ባህላዊ  ተንከባካቢዎች ክትባቶቹን  ለባህላችን መጥፎ ነው  ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ነገር ግን የስረአቱ ወታደሮች የክትባት ዘመቻዎችን በሙሉ አቅማቸው ያስፈጽማሉ።

እናም እንዲህ አይነት አስገዳጅ ክትባት እየተሰጠም  በሎሜ ክልል ብቻ፣ በየመንደሮቹ የሚኖሩ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በፈንጣጣ በሽታ ሞተዋል ። በጎርጎርሳውያኑ 1911 የቅኝ ግዛት ሐኪሞቹ ቆም ብለው ሁኔታው  በማጤን የክትባት ሂደቱን ለመቀየር እስከመገደድም ደርሰዋል። በዚህም በ1914 የፈንጣጣ ወረርሽኝ ስጋት በእጅጉ ለመቀነስ አስችሏል። ነገር ግን  ፎጋንግ እንደሚሉት አስቀድሞ የደረሰው የበሽታው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር በአካባቢው ሌላ አጠቃላይ ችግር አስከትሏል።