የምርጫ አስፈፃሚ በታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደረገ | ኢትዮጵያ | DW | 26.06.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የምርጫ አስፈፃሚ በታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን "ምዕራብ አርሲ ዞን ሊበን አረሲ ወረዳ ለምርጫ ስራ ከወረዳው ተመድበው የነበሩ የወረዳው ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰኔ 9 ቀን ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው" መገኘታቸውን አስታውቋል። በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቀዳሚ ሪፖርት በአማራ ክልል የአብንና የኢዜማ አባላቶች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:12

ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቀዳሚ ሪፖርቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል

በኦሮሚያ ክልል የምርጫ አስፈፃሚ በታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደረገ። በክልሉ "ምዕራብ አርሲ ዞን ሊበን አረሲ ወረዳ ለምርጫ ስራ ከወረዳው ተመድበው የነበሩት የወረዳው ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው" መገኘታቸውን ኮሚሽኑ ዛሬ ቅዳሜ አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቀዳሚ ሪፖርቱን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። በአጠቃላይ 94 ባለሙያዎችን የያዙ 35 ቡድኖች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ምርጫው በተካሄደባቸው 7 ክልሎች በሚገኙ 99 ምርጫ ክልሎች እና 404 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ኮሚሽኑ እንዳለው በነቀምት ዲጋ ወረዳ በሬዳ ሶሮማ ቀበሌ ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ላይ የምርጫ ጣቢያ ሲጠብቁ የነበሩ 4 ሰዎች ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሦስቱ ቆስለዋል። በዚያው በኦሮሚያ ክልል በቡሌ ሆራ ዙሪያ ወረዳ ምርጫ ጣቢያ የዱግዳ ዳዋ ወረዳ ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የቀድሞ የሙረቲ ቀበሌ ሊቀመንበር ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን ም ይፋ አድርጓል።

Äthiopien l Menschenrechtskommission veröffentlicht ihren vorläufigen Wahlbericht

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቀዳሚ ሪፖርቱን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

 

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙት ባሶ ሊበን፣ ጎንቻ እና ደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ገሊላ ቀበሌዎች በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባላቶች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለኮሚሽኑ ሪፖርት አቅርበዋል። በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን፣ ጃርሶ ቀበሌ የሚኖር የኢዜማ ደጋፊ የቀበሌው 2 ሚሊሻዎች ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ድብደባ እንደተፈጸመበት ለኮሚሽኑ ሪፖርት ማቅረቡ ተገልጿል። 

በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሊዘነጉ አይገባም ያላቸውን አበይት አገራዊ አውዶች ጠቅሷል። "በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ከፍተኛ መፈናቀል ባስከተለበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች ራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋና ከግምት ውስጥ የሚገባ ተግዳሮት ነው" ብሏል። 

በኮሚሽኑ ግምገማ መሠረት "በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው ዕለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አልነበረም።"

በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ፣ ግድያና የአካል ጉዳት፣ እስርና እንግልት ያደረሱ ሰዎች ላይ ሁሉ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ ጥሪ አቅርበዋል። 

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር
እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic