1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የምርጫ ቦርድ እና የሲፌፓ ውዝግብ

ዓርብ፣ የካቲት 15 2016

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል» ሲል የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓ ገለጸ ፡፡ የፓርቲውን ቅሬታ አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቀውና በኢሜል ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ ውሳኔው የተሰጠው የቀረቡ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4ckpx
ፎቶ ከማኅደር፤ የሲፌፓ ዋና ጽሕፈት ቤት
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ በሲዳማ ክልል መንግሥት ላይ የሰላ ትችት እያቀረቡ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በመሆን ይታወቃል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሲፌፓ ዋና ጽሕፈት ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

የምርጫ ቦርድ እና የሲፌፓ ውዝግብ

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል» ሲልየሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓ ገለጸ ፡፡ ቦርዱ ከሥልጣኑ ውጭ በፓርቲው የውስጥ አሠራር ላይ በተደጋጋሚ ጣልቃ እየገባ ይገኛል ያለው ፓርቲው በሥነ ሥረዓት ኮሚቴ የተላለፉ ውሳኔዎችን በመሻር፣ በማሻሻልና በመለወጥ «አደገኛ» ያለውን አካሄድ እየተከተለ ነው ሲልም ነቅፏል። የፓርቲውን ቅሬታ አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቀውና በኢሜል ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ ውሳኔው የተሰጠው የቀረቡ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው ብሏል።

ሲፌፓ የቦርዱን ውሳኔ ለምን ነቀፈ ? 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው የውስጥ አሠራር ላይ ጣልቃ በመግባት ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ እያሳለፈ እንደሚገኝ የጠቀሱት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገነነ ሀሰና «ፓርቲውን  ለማዳካም ሲሠሩ ተደርሶባቸው የሥነሥረዓት እርምጃ በተወሰደባቸው ስምንት የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላይ ቦርዱ ያሳለፈው ውሳኔ የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ የሚጻረር ነው። ፓርቲው በራሱ የሥነ ሥረዓት ደንብ መሠረት ያሳለፈውን ውሳኔ ቦርዱ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ በመሄድ ውሳኔውን ለመቀልበስ ሞክሯል። የቦርዱ ውሳኔ ተገቢነት የሌለውና ይልቁንም የፓርቲውን ህልውና የሚፈታተን ነው።  ይህን ቅሬታችንንም ለቦርዱ አቅርበናል» ብለዋል።

ቃለ ጉባዔው 

የፓርቲውን ቅሬታ አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቀውና በኢሜል ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ውሳኔው የተሰጠው የቀረቡ ማስጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው ብሏል። የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ ስምንት አመራሮች የፓርቲውን ጽህፈት ቤት ቁልፍ ሰብረው በመግባት የተለያዩ ንብረቶችን ዘርፈዋል በሚል የተላለፈባቸውን የሥነ ሥረዓት እርምጃ ቦርዱ መመርመሩን አስታውቋል። ይሁን እንጂ ፓርቲው እርምጃውን ሲወስድ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴውን አግባብነት ያላቸውን ሕጎች ተከትሎ ስለማቋቋሙ የሚያረጋግጥ ቃለ ጉባኤ እንዲያቀርብ በቦርዱ ተጠይቆ ባለማቅረቡ ቦርዱ በአመራሮቹ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉን በሰጠው የጹሁፍ ምላሽ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማምስል Ethiopian National Election Board

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የተቋቋመበትን ቃለ ጉባዔ አላቀረበም በሚል የሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገነነ ሀሰና «ይህ የፖለቲካ ሤራ ነው። ሕገ ወጡ አካል የፓርቲውን ጽህፈት ቤት ሰብሮ ገብቶ ቁልፍ በቀየረበት ሁኔታ እንዴት ሠነዱን ማግኘት እንችላልን? ሁኔታውን በሙሉ ለቦርዱ ነግረናል። ነገር ግን ሊረዱን አልቻሉም» ነው ያሉት።

እርምጃው የተወሰደባቸው አመራሮች አስተያየት 

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሥነ ሥርዓት እርምጃ ተወስዶባቸዋል ከተባሉት አንዱ አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ መግለጫ የሚያወጣውና ለቦርዱ የአቤቱታ ደብዳቤ ያስገባው ቡድን ሕጋዊ አመራር አይደለም ይላሉ። የፓርቲው ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ ከወራት በፊት ከአገር ወጥተው በመሄዳቸው በፓርቲው ደንቡ መሰረት ፓርቲውን በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነት እየመሩ አንደሚገኙ አቶ ጴጥሮስ ተናግረዋል። ጽህፈት ቤት ሰብረው ገብተዋል የተባለውን ክስ « ሀሰት» ያሉት አቶ ጴጥሮስ «እኔን ጨምሮ በሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላይ የተወሰደው እርምጃ ከሕገ ደንብ ውጭ የተወሰነ ነው በሚል ቦርዱ ውድቅ አድርጎታል። ለወደፊቱም ቡድኑ የፓርቲውን ማህተም ተጠቅሞ ለመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ለቦርዱ የመጻፍ መብትም የለውም። የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ነኝ ብሎ ምንም አይነት መግለጫ ማውጣት አይችልም» ብለዋል። የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ በሲዳማ ክልል መንግሥት ላይ የሰላ ትችት እያቀረቡ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በመሆን ይታወቃል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ