የምርጫ ቦርድ እና የሲፌፓ እሰጥ አገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2016የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓን አስመልከቶ ያወጣው መግለጫ በዋናነት ከኦዲት ሪፖርት አለመቅረብና በሥም ማጥፋት ቅሬታ ላይ ያተኮረ ነው ፡፡ ቦርዱ በዚሁ መግለጫው “ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓ የመሰረዝ ዕጣ ፋንታ ሊገጥመው ይችላል “ ብሏል ፡፡ ፓርቲው ሊሠረዝ ይችላል ያለው በድጋፍ መልክ ለወሰደው1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር እስከአሁን የሂሳብ ሪፖርት ባለማቅረቡ መሆኑንም አስታውቋለ፡፡ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች በቦርዱ ላይ የሥም ማጥፋት መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ሲልም ቦርዱ አስጠንቅቋል፡፡
የአመራሮቹ አለመግባባትና የቦርዱ መግለጫ
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ የቀድሞው ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ ከሀገር መውጣታቸውን ተከትሎ ከተተኪ አመራሮች ህጋዊነት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በፓርቲው ውስጥ ለተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት መሆኑ ነው የሚነገረው ፡፡ አስቀድሞም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ የምርጫ ቦርድ በፓርቲው ህገ ደንብ መሠረት ከአገር የወጡትን ሊቀመንበር ቦታ ተክተው እንዲሠሩ እንደወሰነላቸው ይናገራሉ ፡፡ በአንጻሩ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ገነነ ሀሰና ደግሞ አቶ ጴጥሮስን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ቀደም ሲል በሥነሥረዓት ጥሰት ከሃላፊነት የታገዱ መሆናቸውን በመጥቀስ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አግባብ አይደለም ይላሉ ፡፡
በዚህ ውዝግብ መኻል መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው የመሠረዝ ዕጣ ፋንታ ሊገጥመው እንደሚችል አስታውቋል ፡፡ ቦርዱ “ ፓርቲው ሊሠረዝ ይችላል “ ያለው በ2015 ዓም በድጋፍ መልክ ለወሰደው 1 ነጥብ 1 ሚሊዬን ብር እስከአሁን የሂሳብ ሪፖርት ባለማቅረቡ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ቦርዱ በተጨማሪም “ አንዳንድ “ ሲል የጠራቸው የፓርቲው አመራሮች በቦርዱ ላይ የሥም ማጥፋት መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
መግለጫው በአመራሮቹ ዕይታ
ዶቼ ቬለ በሲፌፓ ዙሪያ በወጣው መግለጫ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ የብሄራዊ ምርጫ ቦርዱ የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም ፡፡ ከኦዲት ሪፖርት አለመቅርብና ከሥም ማጥፋት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ገነነ ሀሰና የቦርዱን ወቀሳ አልተቀበሉትም ፡፡
ይልቁንም ቦርዱ በፓርቲው ላይ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ በማሳለፍ ፓርቲውን አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል በማለት የተናገሩት አቶ ገነነ “ በድጋፍ የወሰድነውን ሂሳብ በማወራረድ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለብን እናውቃለን ፡፡ የሂሳብ ሪፖርቱን መሥራት ያልቻልነው ግን ቢሮው በአንድ ግለሰብ ቁጥጥር ሥር በመሆኑ የአስፈጻሚውም ሆነ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ወደ ቢሮ ገብተው ሊሠሩ አልቻሉም ፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን ጉዳይ እልባት እንዲሰጠን ብንጠይቅም ሊሰማን አልቻለም ፡፡ ቦርዱ ሥም ማጥፋት በሚል የቀረበውም ትክክል አይደለም ፡፡ በህጋዊ የማህበራዊ ድህረ ገጻችን ላይ የጉዳዩን ሂደት ከማሳወቅ ውጭ ሌላ ያቀረብነው ነገር የለም “ ብለዋል ፡፡
የቀረበው ጥሪ
ፓርቲውን ከአገር የወጡትን ሊቀመንበር ተክተው እንዲሠሩ የምርጫ ቦርድ እንደወሰናለቸው የሚናገሩት አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ ግን የአቶ ገነነ ሀሰናን ሀሳብ አይቀበሉትም ፡፡ እንዳውም አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ ተጠያቂው እነሱ ናቸው ይላሉ አቶ ጴጥሮስ ፡፡ እነኝህ [ አመራሮች ] ወደ ቢሮ እንዲመጡ ህዳር 12 2016 ዓ.ም ደብዳቤ ጽፈናል ፣ በስልክም ጥሪ አድርገናል ፣ ምርጫ ቦርድም ጥረት አድርጓል ፡፡ ነገር ግን ውይይት ለማድረግም ሆነ ለመምጣት አልፈለጉም ፡፡ ይልቁንም እኛንም ሆነ የምርጫ ቦርዱን መክሰስን መርጠዋል ፡፡ አሁንም የሂሳብ ኦዲት ባለማስደረግ ፓርቲውን እያፈረሱ ያሉት እነሱ ናቸው ፡፡ ነገ እውነቱ እየጠራ ይመጣል ፡፡ በህዘብ የሚጠየቁ እነሱ ይሆናሉ “ ብለዋል ፡፡
አሁን ላይ ህጋዊ የፓርቲው አመራር እሳቸው መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጴጥሮስ “ ከፓርቲው ጽህፈት ቤት ይዘው የወጡት ማህተምና አርማ አግባብ ባለሆነ መንገድ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ፡፡ የተለያዩ ተቋማትም ሆነ የሚዲያ አካላት መገናኘት ያለባቸው ህጋዊ ዕውቅና ከተሠጠው አካል ጋር ብቻ ሊሆን ይገባል “ ብለዋል ፡፡
በሲዳማ ክልል አማራጭ ተፎካካሪ ፓርቲ ለመሆን በ2014 ዓ.ም የተመሠረተው የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት ከ30 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ከፓርቲው ድህረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር