1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ሁኔታ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

«በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ለከተሰቱት የፀጥታ ችግሮችና የነዋሪዎች ጥቃት መንግሥት ጽንፈኛ ሲል የሚጠራቸው የሸኔና የፋኖ እጅ አለበት» አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር፡፡ የሰሞኑ የማረቆ አካባቢ ጥቃት የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ በጉዳዩ አሉበት ተብለው የተጠረጠሩ እየታሠሩ እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4kAyE
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስል Central Ethiopia Regional state Communications office

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ሁኔታ

“ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ለከተሰቱት የፀጥታ ችግሮችና የነዋሪዎች ጥቃት መንግሥት ጽንፈኛ ሲል የሚጠራቸው የሸኔ እና የፋኖ እጅ አለበት “ አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው ፡፡ በክልሉ የበርካቶች ህይወት በጠፋበት የሰሞኑ የማረቆ አካባቢ ጥቃት ጋር በተያያዘም የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ በጉዳዩ አሉበት ተብለው የተጠረጠሩ እየታሠሩ እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አላቸው በተባሉት በሁለቱ የሸኔ እና የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች በኩል ግን እስከአሁን የተሠጠ  ማረጋጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ሁኔታ

ምሥረታውን ከዓመት በፊት ያደረገው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአንጻራዊነት ሰላማዊ ከሚባሉት ክልሎች አንዱ ነው ፡፡ከቅርብ ወራቶች ወዲህ ግን በክልሉ ማረቆ ልዩ ወረዳ፣በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶና ምሥራቅ መስቃን ወረዳዎች በነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃትና እገታ እየበረታ መምጣቱ ነው የሚነገረው ፡፡  ባለፈው ሳምንት ብቻ በክልሉ ማረቆ ልዩ ወረዳ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ  ወረዳ ደግሞ አምስት የቤተክርሲቲያን አገልጋዮች ታፍነው ተወስደዋል ፡፡

የእንደራሴዎቹ ውይይት

ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ውይይት ያደረጉት የክልልና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች  ለሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የተለየ ትኩረት የሰጡ ይመስላል ፡፡ የክልሉን አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታ አስመልከቶ ከእንደራሴ ምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ የተነሳላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በአካባቢው ለተከሰቱት የፀጥታ ችግሮችና የነዋሪዎች ጥቃት መንግሥት ጽንፈኛ ሲል የሚጠራቸው የሸኔ እና የፋኖ እጅ እንዳለበት ነው የተናገሩት ፡፡

“ ማዕከላዊ ኢትዮጵያን የሁሉ ነገር ማጠራቀሚያ ለማድረግ የሚፈልግ ሀይል አለ “ ያሉት ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው “ የሸኔ ሀይል ከሌላ ቦታ ሲባረር እዚህ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ነውለመስፈር እየሞከረ ያለው ፡፡ ይሄን እየተከላከልን ነው ያለነው ፡፡ ከአበሽጌ ወረዳ ጋር ተያይዞ ዳርጌ አካባቢ ወደ እዚህ ለመግባት የሞከረ የፋኖ ሀይል አለ ፡፡ የፋኖ ሀይል  ዳርጌም  ወልቂጤም ላይ ህዋስ አለው ፡፡  ሸኔም እንደዛው ፡፡ የተፈለገው ነገር አርሶአደሩንና የመንግሥት ሠራተኛውን ከሥራው ነቅሎ ማዳካም ነው የተፈለገው ፡፡ ይሄ እኛ እስካለን አይሳካም “ ብለዋል  ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አላቸው በተባሉት በሁለቱ የሸኔ እና የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች በኩል ግን እስከአሁን የተሠጠ  ማረጋጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም ፡፡

የማረቆ ጥቃትና የእሥር እርምጃዎች

በክልሉ የበርካቶች ህይወት በጠፋበት የሰሞኑ የማረቆ አካባቢ ጥቃት ጋር በተያያዘም የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮች እየታሠሩ እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡ እስከአሁን ምን ያህል ተጠርጣሪዎች እንደታሰሩ በቁጥር ከመግለጽ የተቆጠቡት ርዕሰ መስተዳድሩ “ በአካባቢው የተከሰተው ችግር በመሠረታዊነት የማረቆና የመስቃን አይደለም ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት እርስ በእርስ ተጋብተው  የኖሩና ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው ፡፡  በአስተዳደር ወሰን ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን በቀጣዩ 2017 ዓም ትኩረት ሰጥተን የምንፈታ ይሆናል ፡፡ በዚህ መኸል የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የግጭቱ ዋንኛ ተዋናይ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በማሰር  በህግ የመጠየቅ ሥራ ተጀምሯል “ ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስል Hadeya zone communication affairs

ዘላቂ መፍትሄ  

አቶ ዳያሞ ዳሌ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያና ቀደምሲል በተወካዮች ምክር ቤት በአባልነት ያገለገሉ ናቸው ፡፡ በርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽ ዙሪያ ዶቼ ቬለ የግል አስተያየታቸውን የጠየቃቸው አቶ ዳያሞ ደንበር ዘለል የፀጥታ ሥጋትን መከላከል የሚቻለው በአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጀ በሚደረጉ ጥረቶች መሆን ይገባዋል ብለዋል ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች የአካባቢው ፖለቲከኞች ሚና ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ ዳያሞ የአስተዳደር ወሰንን እንደድንበር  መቁጠር የችግሩ መንሥኤ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል ፡፡ በቀጣይ በብሄር ማንነት ላይ የተሠማሩ የአስተዳደር ወሰኖች በመፈተሽና በማጥናት ዘላቂ ሰላም ሊያመጡ በሚችሉ አማራጮች መተካት እንደሚያሥፈልግም የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው ጠቁመዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ