የሱዳን መንግስት በድሮን ጥቃት ኢትዮጵያን ከሰሰ
በጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን መንግስት ከኢትዮጵያ ግዛት የተነሳ ድንበር ተሻጋሪ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽሞብኛል ሲል ከሰሰ። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን "ግልጽ ወረራ" ሲል ኮንኖታል። በጎረቤት ሀገራት በኩል የሚደረግ የውጭ ጣልቃ ገብነት ጦርነቱን እያባባሰው ነው ሲልም አስጠንቅቋል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ባለፉት ሁለት ወራት በሱዳን የተለያዩ ስፍራዎች የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች መነሻቸው "የኢትዮጵያ ግዛት" መሆኑ ይታወቅልኝ ብሏል። ሚኒስቴሩ ለዚህ "የጠብ አጫሪነት " ላለው ድርጊት አዲስ አበባን ያስጠነቀቀ ቢሆንም፣ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመና ያደረሰውን ጉዳት ግን በዝርዝር አለመገለጹን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።የግብፅ አምባሳደር ኢሃብ አዋድ በበኩላቸው፣ ስሟ ያልተጠቀሰ የሱዳን ጎረቤት ሀገር ታጣቂዎችን የምታሰለጥንበትና የምታስታጥቅበት ካምፕ መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ብለዋል።ያም ሆኖ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመሩት የብሔራዊ ጦሩ በጎረቤት ሃገራት ላይ ጣቷን የምትቀስረውን ግብጽን ጨምሮ ከሳዑዲ አረቢያ እና የቱርክ ድጋፍ እንደሚያገኙ ዘገባው አመልክቷል።ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያ እጇን አስገብታለች ተብላ በይፋ ስትወቀስ ይህ የመጀመሪያው ነው።ኢትዮጵያ ለቀረበባት ይፋዊ ክስ መልስ ስለመስጠቷ ዘገባው ያለው ነገር የለም። ከሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።
የፑቲን የመካከለኛው ምስራቅ ሽምግልና
ፑቲን በነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የአረብ ስጋቶችን ለኢራን እንደሚያደርሱ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ገለፁ።የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ጠዋት እንተናገሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በክልሉ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የአረብ መሪዎችን ስጋት ለኢራን ያሳውቃሉ።ፑቲን ሰኞ ዕለት ከአራት የአረብ አገራት መሪዎች ጋር የስልክ ጥሪዎችን አድርገዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ፣ ሞስኮ ከቴህራን ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እና አጋርነት በመጠቀም በክልሉ ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ እንደምትሞክር ቃል ገብተዋል።«ትናንት ከሞላ ጎደል ከሁሉም ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ያተኮረው ፑቲን ኢራን በመሠረተ ልማት ላይ ስለምታደርሰው ጥቃት ያላቸውን ጥልቅ ስጋት በኢራን ላሉ የሥራ ባልደረቦቻችን በማሳወቅ ነው።ይህም ከኢራን አመራር ጋር የምናደርገውን ውይይት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ነበር።»ብለዋል።ኢራን በባህረ ሰላጤ አገሮች የኃይል መሠረተ ልማት እና በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ጥቃቶች በሰጠችው ምላሽ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።እንደ ሮይተርስ ዘገባ ፑቲን የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒይ መገደል ተከትሎ በሳምንቱ መጨረሻ ለፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በጻፉት ማስታወሻ ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ኢራን ቅዳሜ ዕለት ጥቃት ከተጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ክሪምሊን ከከፍተኛ የኢራን አመራሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ይፋ አላደረገችም። ፑቲን ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋርም አልተነጋገሩም፣ያሉት ፔስኮቭ በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት ውይይት ለማድረግ ምንም አይነት እቅድ እንደሌለ ገልፀዋል።
በሊባኖስ ቢያንስ 30,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል ተባለ
በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በሊባኖስ ቢያንስ 30,000 ተፈናቅለዋል ሲል፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ።በመካከለኛው ምስራቅ በተባባሰው ግጭት በሊባኖስ ቢያንስ 30,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ዛሬ ማክሰኞ አስታውቋል።የፈረንሳዩ የዜና ምንጭ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከጀኔቫ እንደዘገበው እስራኤል ለነዋሪዎች እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ ከሰጠች በኋላ፣ በተለይም በቤሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች እና በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ላይ የአየር ድብደባ ማድረጓን ቀጥላለች።እንደዘገባው እስራኤል ከ53 በላይ በሆኑ የሊባኖስ መንደሮችን እና በሦስቱም የሊባኖስ ክፍሎች ከፍተኛ የአየር ድብደባዎችን አድርጋለች።ይህንን ተከትሎ በደቡባዊ ሊባኖስ በቤካ እና በቤሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ባባር ባሎች ተናግረዋል።
«እስከ ትላንት ድረስ፣ ግምታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ወደ 30,000 የሚጠጉ ሰዎች በጋራ መጠለያዎች ውስጥ ተስተናግደው ተመዝግበዋል፣ ብዙዎቹ በመንገዶች ዳር በመኪኖቻቸው ውስጥ ተኝተዋል ወይም ደቡብ ቤሩትን ለመልቀቅ በትራፊክ መጨናነቅ ተይዘው መንገዶች ላይ ይገኛሉ።» ሲሉ ገልፀዋል።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ በበኩላቸው ሂዝቦላህ ወደ እስራኤል በርካታ ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ተከትሎ በመጣው የእስራኤል ከባድ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በሊባኖስ የተባባሰው ጦርነት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።"ሁለቱም ወገኖች የጥቃቱን መባባስ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ወደተስማሙበት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመለሱ አጥብቀን እናሳስባለን።" ብለዋል።የእስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች እና በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ የደረሰ ጉዳት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል መኖሩንም ዘገባው አመልክቷል።
በቴህራን የቀጠሉት አዳዲስ ጥቃቶች
አራተኛው ቀኑን በያዘው ግጭት በቴህራን አዳዲስስ ጥቃቶች መቀጠላቸው ተዘገበ።የኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት እንደገና ከባድ የቦምብ ድብደባ ደርሶባታል ሲል የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።የአካባቢው ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ወደ 12 የሚጠጉ ሚሳኤሎች በፓርዲስ ዳርቻ ተወርውሯል።ከዋና ከተማዋ ውጭ ባለው የአልቦርዝ ተራራ ክልል ላይ የፍንዳታ እና ጭስ ምስሎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተጋርተዋል።የትኞቹ ኢላማዎች እንደተመቱ ወይም ጥቃቶቹን ማን እንደጀመረ ግልጽ ባይሆንም የእስራኤል ጦር በኤክስ ገፁ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ "በቴህራን እና ቤሩት በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ጥቃት እያካሄደ ነው" ብሏል።ከዋና ከተማዋ ውጭ በካራጅ ከተማ እና በአገሪቱ መሃል በምትገኘው ኢስፋሃንም ፍንዳታዎች መታየታቸው ተዘግቧል።በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ቅዳሜ ዕለት የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ መገደል ተከትሎ፤ ኢራን ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በርካታ የባህረ ሰላጤ አገሮችን የመታች ሲሆን፤እስራኤልም በኢራን የሚደገፈውን የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድን ለመምታት በቤሩት እና ቴህራን ላይ አዲስ ጥቃት ጀምራለች። በኢራን ጥቃት በሳውዲ ዋና ከተማ ሪያድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም በድሮን ጥቃት ደርሶበታል።የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የአፀፋ ምላሽ 'እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።ጥቃቱን ተከትሎ አሜሪካ የባህረ ሰላጤ አገሮችን ውስጥ ካሉ 6 ኤምባሲዎቿ ለአስቸኳይ ስራ ከሚፈለጉት በቀር በርካታ ሰራተኞችን አስወጥታለች።
የጀርመን ፖሊስ የመንገደኞች ማስጠንቀቂያ
የጀርመን ፖሊስ በኢራን ጦርነት የተስተጓጎሉ መንገደኞች በረራዎችን እንደገና ማስያዝ እንችላለን ከሚሉ አጭበርባሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠነቀቀ።ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው በጀርመን ደቡባዊ የባቫሪያ ግዛት አንዲት ሴት ትክክለኛ የበረራ ቦታ ማስያዣ ነው ብላ ለገመተችው መስመር 2,500 ዩሮ ክፍያ ፈፅማ ከተጭበረበረች በኋላ ነው።የባቫሪያ ግዛት የወንጀል ፖሊስ ቢሮ (BLKA) ተጓዦች የአስቸኳይ ጊዜ የስልክ ቁጥሮችን ከአየር መንገዶች ይፋዊ ድረ-ገጽ ብቻ እንዲያገኙ እና ክፍያ በሚጠይቁ እና ባልታወቁ የጉዞ መረጃ ቁጥሮች እንዳይታለሉ አሳስቧል።ፖሊስ የቦታ ማስያዣ ለውጦች መደረግ ያለባቸው በአየር መንገዶች ይፋዊ የደንበኛ አገልግሎት ብቻ መሆኑን ገልጾ ፤ በማጭበርበር የተጠረጠሩ ሰዎችን ለባለስልጣናት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።የጀርመን የጉዞ ማህበር እንደገለጸው የአሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ባደረሱት ጥቃት በተባባሰው ግጭት እስከ 30,000 የሚደርሱ የጀርመን መንገደኞች በመካከለኛው ምስራቅ መጉላላት ገጥሟቸዋል።
30,000 የጀርመን መንገደኞች በመካከለኛው ምስራቅ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጀርመን የቱሪዝም ቡድን (TUI )ለተቸገሩ ደንበኞች የመመለሻ በረራዎችን ሊጀምር መሆኑን ገልጿል።የጀርመን የቱሪዝም ቡድን TUI በአሁኑ ግጭት በመካከለኛው ምስራቅ ለተቸገሩ ደንበኞች በረራዎችን ከማክሰኞ ጀምሮ እንደሚያቀርብ ዋና ስራ አስፈፃሚው ሴባስቲያን ኤቤል ተናግረዋል።ኤቤል ከኤቲሃድ፣ ኤምሬትስ እና ኳታር አየር መንገድ ጋር እየሰራ መሆኑን እና ማክሰኞ ከእነዚያ ኩባንያዎች ጋር የመጀመሪያዎቹን በረራዎች ያካሂዳል ተብሎ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።ሀላፊው አያይዘውም ወደ ጀርመን ለመብረር ከተቸገሩ 30,000 የሚሆኑ መንገደኞች መካከል 10,000 የሚሆኑት የጀርመን የቱሪዝም ቡድን TUI ደንበኞች እንደሆኑ ተናግረዋል።ኤቤል የተመላሽ መንገደኞቹ ፍጥነት በፀጥታ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል፣ ይህም ለመተንበይ አስቸጋሪ በመሆኑ ሂደቱ ብዙ ቀናት ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈፀሙት ጥቃት እየሰፋ የመጣው ግጭት በመካከለኛው ምስራቅ የአየር ክልል እንዲዘጋ ምክንያት ሆኗል፣ መርከቦችም በወደብ ላይ ተስተጓጉለው እንደቀሩ ተናግረዋል።
ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ