1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ጥምረት

ቅዳሜ፣ መስከረም 23 2013

አራት የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በባሕር ዳር ጥምረት መሰረቱ፣ በጥምረቱ የወልቃይት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አልተካተተም፣ ጥምረቱ ሰላማዊ ትግል በማድረግ የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ የበለጠ ተደማጭ ይሆናል ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/3jNxN
Äthiopien I Coalition of Identity and Boundaries Committee
ምስል A. Mekonnen/DW

የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ጥምረት

አራት የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በባሕር ዳር ጥምረት መሰረቱ፣ በጥምረቱ የወልቃይት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አልተካተተም፣ ጥምረቱ ሰላማዊ ትግል በማድረግ የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ የበለጠ ተደማጭ ይሆናል ተብሏል፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ “የአማራ ክልል ተወላጆችና ነባር ግዛቶች ወደ ሌሎች ክልሎች ተካልለዋል” በሚል በተለያዩ አካባቢዎች ቅሬታ የሚያሰሙ የህብረተሰቡ ተወካዮች አሉ፡፡

“በተናጠል ያካሄድነው ትግል ብዙም ውጤት አላመጣም” በሚል ጥያቄ ከነበራቸው የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴዎች መካከል አራቱ ዛሬ በባሕር ዳር ጥምረት መስርተዋል፡፡

የጥምረቱ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ኃለሚካኤል አረአያ በጥምረቱ የራያ፣ የደራ፣ የመተከልና የጠለምት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት መካተታቸውን ተናግረዋል፡፡

አንድነቱ የበለጠ ጉልበት እንደሚሰጥና በመንግስት ላይ ጫና እንደሚያደርግ፣ መረጃዎችንም ለመሰብሰብ ያስችላል ብለዋል፡፡

Äthiopien I Coalition of Identity and Boundaries Committee
መስራቾች ስምምነት ሲፈራረሙምስል A. Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ከሚገኙ 5 የማንነትና የወሰን ጥያቄ ካላቸው ኮሚቴዎች መካከል የወልቃይት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አልተገኘም ምክንያቱን አቶ ኃይለሞካኤል ሲያብራሩ፡፡

በቦታው የነበሩት የራያ ተወላጁና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብዓዊ መብት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ በሰጡት አስተያየት በጋራ መታገሉ የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ ያግዛል ፡፡

የወልቃይት አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴም በጥምረቱ ቢካተት የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ዶ/ር ሲሳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጥምረቱ ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ኃይለ ሚካኤል እንደሚሉት የአማራ ማንነት ጥያቄ ያለው ህዝብ ቁጥር እስከ 15 ሚሊዮን ይደርሳል፡

የጥምረቱ ጽ/ቤት በጊዜያዊነት ባሕር ዳር ላይ የሚከፈት ሲሆን ጥምረቱ ከፖለቲካ ድርጅትነት ርቆ በሲቪክ ድርጅትነት እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

 ዓለምነው መኮንን