የመሬት መሸራተት አደጋ፤ የዓለም ባንክ ብርድ ለኢትዮጵያ እና የሐማስ መሪ መገደል
ዓርብ፣ ሐምሌ 26 2016የበርካቶችን ሕይወት ድንገት ከቀጠፈው የጎፋው የመሬት መንሸራተት አደጋ ማግስት በሲዳማም ሌላ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቷል ። የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማጽደቁ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ድጋፍ እና ተቃውሞ ገጥሞታል ። የሐማስ ከፍተኛ መሪ ኢራን ውስጥ የመገደላቸው ዜናም በመላው ዓለም የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን ከፍተኛ ትኩረት ስቧል ። በሦስቱም ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን አሰባስበናል ።
የዓለም ባንክ የተራዘመ ብድር እና የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በዚሁ ሳምንት ያጸደቀው የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ፖሊሲ ከወዲሁ ማነጋገር ጀምሯል ። ውሳኔው ኢትዮጵያ ውስጥ የብር የመግዛት አቅምን በብርቱ ማዳከሙ ወዲያው ነው የተስተዋለው ። የብር የመግዛት አቅም መዳከም ጉዳይ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) መርሐ-ግብር ውስጥ የተካተተ ነው ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ከዓለም ባንክ የተገኘውን የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍና ብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበለትን አዋጅ በዚሁ ሳምንት አጽድቋል ። አዋጁ በምክር ቤቱ ሲጸድቅም የቀረበው የተቃውሞ ድምፅ አንድ ብቻ መሆኑ ተዘግቧል ።
ሐፍቶም ኢትዮጵያዊ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «የአንድ ተቃውሞ ብቻ አይደለም፤ የኔም አለበት ። ምንም እንኳን የፓርላማ አባል ባልሆንም» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል ። «ኢትዮጵያውያንን የሚጠቅመው አንዳችም ነገር የለም ። በኢትዮጵያውያን ላይ የተደረገ እግረ-ሙቅ ነው» ሲሉ በእንግሊዥኛ የጻፉት ደግሞ ጆሞ ጆ ጆሜስ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ።
ዐቢይ መርሻ የተባሉ የቴሌግራም ተከታያችን ደግሞ፦ «መንግሰት ለሕዝብ ማሰብ ካቆመ ቆየ ። ሕዝቡን ንቆታል ። ሕዝቡም ፈሪ ሆኗል ። ኑሮ ሲከብደው መፍትሄ ያደረገው ቁርስ፣ ምሳ--- መተዉን ነው ። በሌሎች ሀገሮች የምናየው ከዚህ ይለያል ። በእውነቱ ምን ነካን፡ ወዴትሰ እየሔድ ነው?» ሲሉ አጠይቀዋል ።
ዘመዴነህ ንጋቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ስለ ጸደቀው ብድር ማክሰኞ ዕለት በትዊተር ገጻቸው በእንግሊዝኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ፦ «ታላቅ ስኬት» ብለዋል ። እንዲህ ያለ ከፍተኛ ገንዘብም «መዋዕለ ንዋይ ፍሰቱን በእጅጉ ያሳልጣል» ሲሉም አክለዋል ። «ትቀልዳለህ? የትኛው መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ነው በጦርነት እና በቀውስ ወደምትናጥ ሀገር መምጣት የሚፈልገው ?» ሲሉ የሚጠይቁት ሜስ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ። «ወሬ ብቻ» ሲሉም ጽሑፋቸውን ያጠቃልላሉ ። «በመንግሥት የተያዙ ኩባንያዎች ሳይቀር ወደ ግል መዞር ያሻቸዋል» ይህ ደግሞ የምስጋናው በርሄ የትዊተር መልእክት ነው ።
«ኧር መንግስት ምን አስቦ ነው?» ይጠይቃሉ ናሆም፦ በቴሌግራም ። «ትንሽ ምክንያት የሚፈልግ ሕዝብ ለራሱ ኡኡኡኡ» ሲሉም ብሶታቸውን ገልጠዋል ። አብዱልአዚህ ዓሊ ሐሰን በበኩላቸው በቴሌግራም መልእክታቸው፦ «አብይ አህመድ እንደ መፍትሔ የወሰደው የኢኮኖሚ ችግር ብድር ግን የእዳ ጫናው ዛሬም ቀጣይ ትውልድ መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ደርሷል» ሲሉ ብሶታቸውን አንጸባርቀዋል ።
አሰቃቂው የጎፋ እና የሲዳማ የመሬት መንሸራተት
በደቡባዊው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ በሕይወት ላይ እያስከተለ የሚገኘው አደጋ ተደጋግሟል ። እሁድ ሐምሌ 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም እና በማግስቱ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካቶችን አስደንግጧል፤ በጣምም አሳዝኗል ። በመሬት መንሸራተቱ አደጋ እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 23 ድረስ በፍለጋው የ243 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል ። በክብር እንዲያርፉ መደረጋቸውም ተዘግቧል ። ይህ የባለፈው የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው የጎፋው ዞን አደጋ ሐዘን ሳያገግም በሲዳማ ክልልም ተመሳሳይ አደጋ ተከስቷል ። በሲዳማ የመሬት መንሸራተት የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል ።
«እጅግ በጣም ያሳዝናል! መፅናናት ለሁሉም ቤተሰቦች እና ዘመድ አዝማድ» አዘዘ ጦሩ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት ነው ። በርካቶች በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አደጋው ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተው ሐዘናቸውን ገልጠዋል ። ዓለማየሁ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ደጉን የአገሬን ሰው ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋ ፈጀቻው ። ሚዳያ ለማያገኙት በሞርተርና በመድፍ ለሚጨፈጨፉት ወገኖቼም ነብስ ይማርልን» ብለዋል ።
ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ እና ባለቤታቸው በጎፋ የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰበት ሥፍራ በመገኘት ሐዘናቸውን መግለጣቸውን የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል ። «በሺህዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በግፍ ሲጨፈጨፉ ዐቢይ አንድም ጊዜ ሐዘኑን ገልጦ ዐያውቅም» ሲሉ ድርጊቱን የማስመሰል ሲሉ የተቹት ኢትዮጵያ ራይዚንግ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው ።
«ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሀገር በአደጋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ተቋም አለመኖሩ በጣም ገርሞኛል» ሲሉ ፌስቡክ ላይ የጻፉት ዓለማየሁ ዘጸአት ናቸው ። «በሐዘን በተሰበረ ስነልቦና እና ጉልበት ይህን ያህል ጥረት የፈጣሪ ብርታት ካልተጨመረ የሚቻል አልነበረም» ሲሉም አክለዋል ። «ያለፈውን ትተን ሕዝበ ሆይ ከሚመጣው ፈተና አውጣን እንበለው» የግርማ ኤሊያስ አጠር ያለ አስተያየት ነው ። ዝምታ የጎዳኝ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ፈጣሪን ይጠይቃሉ? «ወይ ፈጣሪ ስንት አሸባሪ እያለ ለምን ምስኪኖችን? እባክህ በቃ በለን ፍርድህን አታዛባ» ሲሉ ። በዚሁ አስተያየት ወደ ቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ እንሻገር ።
የሐማስ ከፍተኛ መሪ እስማኤል ሐኒዬህ ኢራን ውስጥ መገደል
የሐማስ ከፍተኛ መሪ እስማኤል ሐኒዬህ ኢራን ውስጥ ተገደሉ የመባሉ ድንገተኛ ዜና በመላው ዓለም የበርካቶች መነጋገሪያ የሆነው ወዲያው ነበር ። የሐማስ ፖለቲካል ጽ/ቤት መሪ የነበሩት እስማኤል ሐኒዬህ ኢራን ውስጥ ከአየር በተሰነዘረ ጥቃት ስለመገደላቸው ይፋ ያደረገው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ነበር ። ምንም እንኳን እስማኤል ሐኒዬህን በመስከረም 26ቱ የሐማስ ጥቃት ጋ በተገናኘ እሥራኤል ለመግደል በተደጋጋሚ ብትዝትም ለግድያው ግን ወዲያው ኃላፊነት የወሰደ አካል አልነበረም ። ሐማስ፦ እስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ነው ።
«እኔ የየትኛውም ፖለቲከኛ የሀማስም የእስራኤልም ደጋፊም ነቃፊም አይደለሁም» ሲሉ አስተያየታቸውን በፌስቡክ የሚያንደረድሩት ገብረመድኅን ተስፉ ናቸው ። «በሁለቱም በኩል ያለ ንጹህ ሕዝብ ሰለባ ግን በጣም ያመኛል ያሳዝናል» ሲሉም አክለዋል ። «እራሷ ኢራን ላለምግደሏ ምን ማስረጃ አለ?» ጥያቄው የኢብን ዑመር ነው ። በፌስቡክ ። «ወይ ዘንድሮ» ይላሉ ማሜ በላይ በአጭሩ ። ፀጋዬ ወላድይም እዛው ፌስብክ ላይ በአጭሩ ቀጣዩን ብለዋል ። «ሰላም ለዓለም ሕዝቦች በሙሉ»
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ