የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ ለተደረሰው ግጭት የማቆም ሥምምነት ቁልፍ ሚና ነበራቸው ለተባሉ ወገኖች ያለፈው ዕሁድ ሚያዚያ15 ቀን 2015 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ የምሥጋና እና የእውቅና መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
«ጦርነት ይብቃ - ሰላምን እናፅና» በተሰኘው በዚህ መርሐ-ግብር በውጊያው ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የፌደራል መንግሥት ብሎም የህወሓት የሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ የአፍሪቃ ኅብረት ፣አደራዳሪዎች እና ታዛቢዎች ተሸልመዋል።
ይህንን ተከትሎ ሀይማኖት ተክሉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «በመሀል ቤት የእነሱን የወንበር ሽሚያ ለማስጠበቅ በከፈቱት ጦርነት ጭዳ የሆነው ህዝብ ተረሳ፡፡ሾላ በድፍኑ ነገር፡፡ በቀጣይ ግን ለእንደዚህ አይነት የወንበር ሽሚያ የሚሞት ይኖር ይሆን?»ሲሉ ጠይቀዋል።በላይ ገረመው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ «ለሰው ፖለቲካ መሞት ልምዳችን ነው።»በማለት ለአስተያየቱ መልሰዋል። ብሬ የንሂም በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ሲመስለኝ ይህ ሁሉ መሽሞንሞን ከተጠያቂነት ለመዳን ነው "አይሳካላቹህም"»የሚል ነው።«እንደ ጊዜ መስታዋት የለም ሁሉን ያሳየናል።»ይላል አርሴ ማንቼ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት።
እውነታው ይኸውነው ደግሞ «ድሮምኮ ህዝቡ ነው እንጅ ያጣላችሁ እናንተ ምስኪን ናችሁ¡¡¡»የሚል ምፀት አስፍረዋል።
«በወንጄል ይጠየቃሉ ስንል ጭራሽ ሽልማት»ያሉት ደግሞ ሄዊ ነኝ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። ቡልቻ ዳፊስ በበኩላቸው «ሰላም የማይወድ ሰይጣን ብቻ ነው። አቁሙ ወደ ፊት አርቃችሁ ተመልከቱ። ከትላንቱ ፍጅት እና ዉድመት እንጂ ምን ያተርፈነው ነገር አለ? ሰላም ሰላም ለሀገራችን!!»በማለት ፅፈዋል።
ጫልቱ ወለጋ «ለሁሉም ነገር ጥድፊያ ግን የጤና አይመስለኝም።»ሲሉ፤ ተፈፀመ ተፈፀመ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «እዉነት ነዉ ያለቀዉ የሰዉ ህይወትና ንብረት እንጅ ወንበራቸዉ አልተነካ»ይላል። ኪዳኔ ወልደአረጋይ ደግሞ «ሠላም ለሠው ልጆች ሠላም ለ ኢትዮጵያ አረ ጦርነት በቃን ሠለቸኝ አቦ የተንከራተትነው ይበቃናል።»ብለዋል።
ሁሉም ያልፋል በሚል ስም የሰፈረው ረዘም ያለ አስተያየት ደግሞ «አቶ ጌታቸው ረዳም ጠቅላይ ሚንስትሩም የሰላም ሰባኪ ሀነው አመሹ ጥሩ ነው።አየሩንም ምድሩንም የግጭት ወሬ በተቆጣጠራት ሀገር ይህንን መስማት ደስ ይላል። ግን ይህንን ለመናገር ሁለት ዓመት መዋጋት ነበረብን።ሺዎች መሞት ነበረባቸው።ያ ሁሉ ንብረት መውደም ነበረበት?የድሃ ልጅስ? ደሃ እናትስ ልጇን ያጣችው? ወንጀለኞችስ ለፍርድ አይቀርቡም? እያሉ በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቃቸው ቀጥለዋል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙዎችን ያነጋገረው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ ሸኔ» ብሎ በተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጀው እና እራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር »ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ድርድር ልጀምር ነው ማለቱ ነው። «ግጭት ይቁም ሰላምን እናፅና» በተሰኘው መርሐ-ግብር መንግስት "ኦነግ ሸኔ" ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል። መንግስት ስለድርድሩ በገለፀ ማግስት ታዲያ ፤ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ/ም ታጣቂ ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ድርድር እንደሚጀምር አረጋግጧል።ይህ እርምጃ ሰላም ለማውረድ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብሎታል፡፡ይሁን እንጅ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ከነዚህም መካከል «ኦነግ ሸኔ» የሚለውን ስያሜ እንደማይቀበለው የሚጠቅሰው ይገኝበታል።ያም ሆኖ ድርድሩ በታንዛኒ መጀመሩን የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታዉቋል።
ይህንን ተከትሎ ሰርኬ ሀይሌ የተባሉ አስተያየት «ሰጪ እንዲያ ከሆነ ነገሩ መንግስት ከሌለ ነገር ጋር ሊደራደር ነዋ !ጎበዝ የምንሰማው እና የገጠመን ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው።» በማለት ግርምታቸውን ገልፀዋል።
ቴዲ ማርሸት «መርህ አልቫ ግንኙነት።»ሲሉ፤መሀመድ አሊ ደግሞ «የአባት እና ልጅ ድርድር ነው»ብለዋል። ሚኪ ፀጋዬ «ከራስ ጋር ንግግር» ሲሉ፤አብዱ የሱፍ በበኩላቸው «እውነት ያድርገው ሰላም መውረዱ ጥሩ ነው በተለይ መሬት ላይ ለሚሰቃየው ምስኪን ህዝብ።»ብለዋል።ሀሰን ከድር «እና መንግስት ማነህ ብሎ ነው እየተደራደረ ያለው።በወለጋ የደረሰው ሞት እና መፈናቀልስ ባለቤቱ ማነው?።»ሲሉ ጠይቀዋል።አስተዋይ አለሙ ደግሞ በበኩላቸው «ብዕር የጨበጠ ጋዜጠኛን እያሰሩ ፤የታጠቀ እና የገደለን ደግሞ ለድርድር ማቅረብ።»ብለዋል።
ነጋ ሮበሌ «ሰላም የሁሉ ነገር ምንጭ ነው!! መስማማት እጅግ በጣም ወሳኝና ሕዝብም የሚደግፈው ነው:» ብለዋል። ተክሉ አያሌው ደግሞ «መንግስት ከህዝብ ጋርስ መቼ ነው የሚታረቀው»ብለዋል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የሀነው ጉዳይ በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የባለስልጣናት ቡድን መቀሌ መግባቱ ነበር። በትናንትናዉ ዕለት ሚያዝያ 19፣ 2015 ዓ/ም መቀሌ ከገባው የልዑካን ቡድን በሁለቱ ዓመት ጦርነት ቀጥተኛ ተጎጅ የነበሩት የአማራ እና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የተለያዩ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ተካተዋል። ለባለስልጣናቱ መቀሌ ሲደርሱም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ አቀባበል አድርገዋል።
ካላዩ መኮንን«ሰላምን የመሰለ ነገር የለም።» ሲሉ።አረጋዊ ንጉስ በበኩላቸው «ጥሩ ነው ግን ክረምት እየገባ ነው። የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቦታቸው ከተመለሱ ነው ሰላም የሚመጣው። እንጂ ህዝብ እየተቸገረ ዝም ማለት ሰላሙ የት ኣለ።»
አድና ሲሳይ ግን የባለስልጣናቱ ነገር የተዋጠላቸው አይመስሉም «ከአንገት ነው ከአንጀት» ብለዋል።
«ከፖለቲከኞቹ ይልቅ ምናለ የተጎዳውን ህዝብ መጀመሪያ ብሶቱን ብታዳምጡት።»ያሉት ጆኒ ማን የተባሉ አስተያየት ሰጭ ናቸው።
«የእናንተን ወንበር ለማፅናት ያለቀው ህዝብስ?» ወጣት ሆይ ለነገ ትምህርት ውሰድ።ለማንም ፖለቲከኛ እንዳትሞት።»ብለዋል ልጅ አሌክስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ።
ነስር ዓሊ «አንድነት እና ሰላም ሐይል ነው አላህ ልባችሁን ያረጋጋው»ብለዋል። አዛለች አዛሉ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ለታይታ ካልሆነ ሰላም ጥሩ ነው።ነገር ግን ዘላቂ ሰላም ከዘላቂ ፍትህ ነው የሚመጣው።»ይላል።
ክፍሎም ፍፁም« ይሄን ማየት ድንቅ ነው።ደስ ይላል።ወደህዝብ ሲወርድ ደግሞ ውብ ይሆናል።ሰላም ለሀገራችን»ብለዋል።
«ፈገግ ብለው ሲተቃቀፉ ግን ወጣት ያስጨረሱ ሳይሆን ለወጣቱ የስራ እድል የፈጠሩ ነው የሚመስሉት።እንደ ፖለቲካ ያለ ቆሻሻ ነገር የለም።»ያሉት አክሊሉ ማናዬ ናቸው።
በሱዳኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ሄሜቲ በመባል በሚታወቁት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መሪ ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳግሎ መካከል በተፈጠረው ግጭት ሱዳን በጦርነት እየታመሰች ነው። ይህንን ተከትሎ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ እና ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሱዳናውያን ስደተኞች ከሀገር ውስጥ ጉዳዮች በተጨማሪ የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
ሰሚራ ሰኢድ «ሱዳን ሆይ ከኢትዮጵያ መከራ ተማሪ»ብለዋል።አሸብር ሀይለማሪያም ደግሞ «የሱዳን ተፈናቃዮች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው።ጣጣው ለእኛም ጭምር ነው።የዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ጦሱ ለሀገራችን እየተረፈ ነው።»ብለዋል።
ሰላም ታደሰ ደግሞ «የሚያሳዝኑት ሱዳን ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።ምናለበት እንደሌሎቹ ሀገራት መንግስት ዜጎቹን ቢያስወጣ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ብሩክ ሀይሉ «እኔን የገረመኝ በአረብ አብዮት ከስልጣን የወረዱት አልበሽር በግርግር ማምለጣቸው ነው።»ሲሉ፤ ከቤ አራዳው ደግሞ «የሱዳን ህዝብ ግን ይህ አይገባውም ነበር።ያ ሁሉ ትግል ውሃ በላው።»ብለዋል።
«የአፍሪቃ ባለስልጣናት ግን መቼ ነው ህዝብን ከወንበራቸው የሚያስቀድሙት።»ያሉት ደግሞ ኪያ ኪያ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ናቸው።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ