1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ ዕውቅናና ሽልማት

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

ውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) ለማኀበረሰባቸውና ለሃገራቸው ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ላላቸው ስመ ጥር ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት አበረከተ። በስነ ምግባር የታነፁና በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ተማሪዎችም ሽልማት ማግኘታቸውም ተገልጿል ።

https://p.dw.com/p/4SLRl
Infografik Karte Äthiopien AM

ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎችም ገንዘብ ተሸልመዋል

ውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) ለማኀበረሰባቸውና ለሃገራቸው ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ላላቸው ስመ ጥር ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት አበረከተ። በስነ ምግባር የታነፁና በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ተማሪዎችም ሽልማት ማግኘታቸውም ተገልጿል ።  ዘጋቢያችን ታሪኩ ኃይሉ ከአትላንታ ጆርጂያ ቀጣዩን ዘገባ አጠናቅሯል ።

ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) ስነ ምግባራቸው ለቀና፣በሙያቸው ማኀበረሰባቸውንና ሃገራቸውን ለሚያገለግሉ ስመ ጥር ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት መስጠት ከጀመረ 30 ዓመት ሆነው። ሲድ ኢትዮጵያ 30 ዓመት በዓሉን ያከበረበትን የዘንድሮው ሽልማትና የዕውቅና ዝግጅት፣ «በኀያሉ ግዩራን»ወይም «ዳያስፖራ» በሚል ርዕስ ማካሄዱን፣ የድርጅቱ መስራችና ሊቀ መንበር አቶ አክሊሉ ደምሴ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።
 
«ግዩራን» ከግእዝ ወጥቶ ወደ ዐማርኛ የተወረሰ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ዲያስፖራ ማለት ነው። «ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ 30 ዓመቱን ነው ያከበረው ዘንድሮ። ዓላማው ወጣቶችን የኢትዮጵያ ልጆች ወይም ኢሚግራንት ሆነው የመጡትም እዚህም ሃገር የተወለዱትም አሜሪካን ሃገር ማለት ነው። ሌላም ሃገር ሊሆን ይችላል። እንዲነቃቁና ያላቸውን ባሉበት ሃገር ያላቸውን ዕድል ተጠቅመው፣ጥሩ ቦታ እንዲደርሱ ለማበረታታትና እነርሱም ከመኻከላችን ሌላ ዐዋቂ ኢትዮጵያውያኖች ወደ የደረሱን ማፋጨትና አነርሱም ለብዙ ጊዜ በስራ አገልግሎታቸው፣ በትምርታቸው ያሳዩትን እነርሱን እንደ ምሳሌ በማቅረብ ወደፊት ደግሞ እነሱ የሚጠበቅባቸውን የኮሚኒቲ ሰርቪስ እንዲያዩ ዐዋቂዎችን አጠገባቸው አድርገን 12 ክፍል የጨረሱትን አጠገባቸው አድርገን እናከብራቸዋለን።»

ሜሪላንድ ውስጥ በተካኼደው ስነ ስርዓት ላይ በትምህርት፣በንግድ፣በቴክኖሎጂ፣በኪነጥበብ፣በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ ለማህበረሰባቸውና ለሃገራቸው አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማምጣት ታላቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል የተባሉ እውቅ ግለሰቦች የላቀ ዕውቅናና ሽልማት እንደተሰጣቸው አቶ አክሊሉ ገልጸዋል።

«ዘንድሮ ዘጠኝ ሰዎችና ሁለት ድርጅቶች ሸልመናል። ደግሞ 10 የሚሆኑ በጣም ጎበዝ ተማሪዎች ከአራት ነጥብ ሁለት በላይ ያገኙ ዐስር ልጆች ሸልመናል። እያንዳንዱ ሁለት ሺህ ዶላር ስኮላርሺፕ ሰጥተናል።»

ለዕውቅና ከበቁት ስመ ጥር ግለሰቦች መኻከል፣ የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪል ካውንስል ሰብሳቢ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ፣ የአዲስ ተስፋ ማገገሚያ ማእከል መስራች ዶክተር ሊሻን ካሳ፣የኅዳሴ ግድብ አሰመልክቶ በተሟጋችነቱ የሚታወቀው ዑዝታዝ ጀማል፣ ደብረ በብርሃን የሚገኘው የኀይሌ ሜነስ አካዳሚ መሥራች ወይዘሮ ርብቃ ጌታቸው ኀይሌ፣የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ፣የኢትዮጵያና የጀርመን የፖለቲካ ጉዳዮች ዐዋቂና ደራሲ ልዑል አስፋወሰን አሥራተ ይገኙባቸዋል። 

የማኅበራዊ ፍትሕ ታጋይ እንደሆኑ የተነገረላቸው፣ የዴንቨር ነዋሪው ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ስለተሰጣቸው ዕውቅና ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ የሚከተለውን ብለዋል።

«እንግዲህ፣ያው በዚሁ በእንቅስቃሴ ዓለም ገና ተማሪ ቤት ጀምሮ የነበርኹበት ነገር ነው፤ 50 ዓመት የተሳተፍኹበት ስለ እግዚአብሔርና ስለሃገር ጉዳይ አሁን በቅርቡም ባለፉት ስምንት ዓመታት እዚሁ የአሜሪካ ኮንግረስናስቴት ዲፓርትመንት ውስጥ የለፋንበት ያገኘነው ውጤት የሌላውም እሱን ነው የላኩልኝ። በእሱ ነው እንግዲህ ዕውቅና የሰጡት።»

በድርጅት የተሸለሙት፣የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ/ኤፓክ/እና የሐበሻ ህጻናት ክለብ ናቸው። 

ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ/ሲድ/በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ የትውልደ ኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ድርጅት እንደሆነ ይነገርለታል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ