የማረቆና የመስቃን ወረዳ ተፈናቃዮች የእርዳታ ጥሪ
ሰኞ፣ ኅዳር 17 2011
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ባለፈዉ ሳምንት በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች በተቀሰቀ ግጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች መንግስት በተገቢዉ ሁኔታ እርዳታ እያቀረበልን አይደለም ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ።የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ እርዳታዉን ወደ ቦታዉ ለማድረስ እያጓጓዝኩ ነዉ ብሏል።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነት ላይ ያተኮሩ ግጭቶችና መፈናቀሎች ከሚታይባቸዉ ቦታዎች የደቡብ ክልል አንዱ ነዉ።በክልሉ ከዚህ ቀደም በወላይታና ሲዳማ ብሄረሰብ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት ሞት ፣የአካል ጉዳትና የመፈናቀል አደጋ ደርሷል። በቅርቡም በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭትም ወደ 24 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸዉንና ከ 165 ሰወች በላይ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸዉን ተዘግቧል።ከዚህ በተጨማሪም ከጉዳቱ ለመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ያም ሆኖ ግን ተፈናቅለዉ ባሉበት የመጠለያ ስፍራ የአካባቢዉ ህብረተሰብ ከሚያደርግላቸዉ ድጋፍ ዉጭ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በመንግስት በኩል ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ይላሉ። ከማረቆ ወረዳ አሊቦር ቀበሌ ቤታቸዉ ተቃጥሎባቸዉ ከ5 ልጆቻቸዉ ጋር ከቀያቸዉ ተፈናቅለዉ በቡታ ጅራ ከተማ ስታዲየም ተጠልለዉ የሚገኙት አቶ ሻፊ ኑሪ ለDW ይህንኑ ያረጋግጣሉ።
በቡታጅራ ከተማ 05 ቀበሌ ተፈናቃዩችን የሚያስተባብሩት አቶ መሀመድ በበኩላቸዉ የአካባቢዉ ህብረተሰብ የዕለት ምግብ በማቅረብ ረገድ የተቻለዉን እያደረገ መሆኑን ገልፀዉ ነገር ግን ከመጠለያና ከንፅህና ጋር በተያየዘ ችግር እያጋጠመ መሆኑን አስረድተዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ DW ያነጋገራቸዉ የመስቃን ወረዳ የመንግስት ኮምኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ሬድዋን ከድር ፣የከተማዉ ነዋሪና አንዳንድ ባለሀብቶች ተጎጅዎቹን ለመርዳት ያደረጉት ድጋፍ አበረታች መሆኑን ገልፀዉ፤ በመንግስት በኩል ግን እስካሁን ምንም እርዳታ ባለመቅረቡ የተፈናቃዮቹ ቅሬታ ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጠለያ ጣቢያዎቹ በርካታ ህጻናት፣ አረጋዉያን ፣አራስ ሴቶችና የቤት እንስሳት ጭምር በአንድ ቦታ የሚገኙ በመሆናቸዉ ችግሩ የከፋ መሆኑንም አቶ ሬድዋን ጨምረዉ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ሬድዋን ተፈናቃዮቹን ወደ ቦታቸዉ ለመመለስ የተደረገ ጥረት ቢኖርም በአካባቢዉ አስተማማኝ ሰላም ባለመስፈኑ ሊሳካ እንዳልቻለ ገልፀዋል።መሆኑም ችግሩ ከወረዳዉ አቅም በላይ በመሆኑ መንግስት አፋጣን መፍትሄ እንዲሰጥ ለበላይ አካል ጥያቄ መቅረቡን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ተፈናቃዮቹን ለመርዳት እርዳታ በማጓጓዝ ላይ መሆኑን ገልጿል። የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ከሁለቱም ወረዳዎች ከ 30 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸዉን ገልፀዉ ለነዚሁ ሰዎች እርዳታ እየተጓጓዘ ነዉ ብለዋል።
ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ