1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2016

በአራት ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ቃርመናል። አስተያየቶቹ የረመዳንና ዐብይ ፆም መጀመሪያ ዕለት መገጣጣም፣በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግጭትና መፍትሔዉ፣ የፕሪቶሪያዉን ስምምነት በገመገመዉ ስብሰባና ከወራት በፊት የታሰሩት የአብን ከፍተኛ ባለሥልጣን ያለመከሰስ መብት መነሳቱን በሚያወሱት ዘገቦች ላይ የተሰጡ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/4diJh
Eid Al-Fitr Feier in Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በአራት ጉዳዮች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ቃርመናል።አስተያየቶቹ በረመዳንና ዐብይ ፆም መጀመሪያ ዕለት መገጣጣም፣በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግጭትና መፍትሔዉ፣ የፕሪቶሪያዉን ስምምነት በገመገመዉ ስብሰባና ከወራት በፊት የታሰሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከፍተኛ ባለሥልጣን የክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት መነሳቱን በሚያወሱት ዘገቦች ላይ የተሰጡ ናቸዉ። 
የዘንድሮዉ የረመዳንና የዐብይ አፅዋማት ባንድ ቀን (ባለፈዉ ሰኞ  መጋቢት 2) እኩል መጀመራቸዉ ለአንዳዶች አስገራሚ፣ ለብዙዎች በተለይ ለኢትዮጵያዉን መልካም አጋጣሚ ብጤ ሆኗል።የሁለቱም ኃይማኖቶች ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም እንደቀጠለ ነዉ።ጥላሁን ጌታቸዉ በፌስ ቡክ የመንፈስን ብርታት ያስረዳል።«በትክክል አምነንበት የምንፆም ከሆነ አይሪበንም አይጠማንምም።» ቀጠለም «ለተራበ ካበላህ ችግረኛን ከረዳህ፣ ሰላም፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን ካስተማርክ ወይም ካሰብክ አይርብህም አይጠማህም።» ጥላሁን ጌታቸዉ ነዉ ይህን ባዩ።
ቶሚ ዳዲ ደግሞ ብዙ አትብሉ ባይ ነዉ። «እኔ በጥዋት መብላት ኣልወድም። በፍሰግ ግዜ ከራበኝ በኋላ ነው የምበላው። እና ብዙ መብላት የጤና ችግር ያመጣል።» የሪያድ ማህበረሰብ ድምጽ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየች ሰጪ «ለሁለቱም መንፈሳዊ እምነት ተከታዩች እንኳን ለረመዳን ወር ፆም እና ለዐቢይ ፆም አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ።» ብሏል።እንኳን አደረሰሕ።
ሳዳም ሱሌይማን በፌስ ቡክ ሥለረመዳን ምንነት የሚያስረዳ በአቡ ሐይደር የተዘጋጀ በጣም ሰፊ መጣጥፍ ለጥፏል።አንብቡት።
አቲዬ ሸገር፣ በፌስ ቡክ፣-«ፈጣሪ ሃገራችንን አለማችንን ሰላም ያርግልን» እያለች ትፀልያለች።ምትኩ መለሰ ደግሞ የሁለቱን ኃይማኖቶች አፅዋማት አንድነትን ባጭሩ ያስረዳል-እሱም በፌስ ቡክ ነዉ «አንድ የሚያደርጋቸው ጾም ሲፈታ የሚያመጣውን ደስታ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ጋር ሆነ፣ በሃገር ደረጃ በዓላቱን ማክበር፣ መደሰት፣ መፋቀር ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ሲሆን--»እያለ ይቀጥላል ምትኩ በፌስቡክ።እኛ ይብቃን።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ግጭትና መፍትሔዉ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በሚገኙ ታጣቂ ኃይላትና በመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የሚደረገዉ ዉጊያና ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱ እየሰፋ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰዉ ጉዳትም እየከፋ ነዉ።በኦሮሚያ ክልል የሚደረገዉን ግጭት ለማስቆም የተፋላሚ ኅይላት ተወካዮች ሁለት ጊዜ ቢደራደሩም መስማማት አልቻሉም።የአማራ ክልሉን ዉጊያ ለማስቆም ግን እስካሁን በይፋ የተደረገ የድርድር ሙከራ የለም።ሁለቱን የኢትዮጵያ ትላልቅ ክልሎች የሚያወድመዉ ግጭት ያደረሰዉ ጥፋትና መፍትሔዉን የሚቃኝ ዉይይት ባለፈዉ እሁድ አሰራጭተን ነበር።
ራሞስ ታምራት በፌስ ቡክ «ብልፅግና ካልተወገደ አይቆምም» ይላል ባጭሩ። አብዱ ፊክር ከራሞስ ጋር ተመሳሳይ አስተያየት አለዉ «መንግሥት ሠላም ባለመፈለጉ ነው የምንሠቃየው። ጭር ሲል አይወድም» የአብዱ ፊክር አስተያየት ነዉ። ዋርታ ኡዚ እሱም በፌስ ቡክ « የፌደራል መንግስቱ ግብዝነት የፈጠረዉ ችግር ነዉ-ሐገራችንን የሚያምሳት።» ይላል።  
ፋሪያ አሕመድ ረዘም ግን ለየት ያለ አስተያየት አላት።በፌስ ቡክ ነዉ። «የሚገርመዉ ነገር ሁለቱ ክልሎች ጫካ ያሉት ቡድናት የአይዶሎጂ ልዩነት ከባድ መሆኑ ነዉ። የትግራይ ክልል ጦርነት መቆም በአማራ ክልል ጦርነተነት ለመጀመሩ ምክንያት ነዉ።ኦሮሚያ ላይ ህዝቡና መንግስት አይደማመጡም።መንግስት ህዝብ የሚሰማቸዉን ጎበዝ ሰዎችን አባርሮ አስበዉ ማስተዳደር የማይችሉ ሰዎችን ሾሞ ክልሉን ሰላም አሳጣዉ።ጫካ ያሉትም ህዝቡን የሚሰሙ አልሆኑም።» የፋሪያ አሕመድ አስተያየት ነዉ።

ፎቶ ማህደር፤ ታጣቂዎች በሰሜናዊ ኢትዮጵያ
ፎቶ ማህደር፤ ታጣቂዎች በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ምስል Mariel Müller/DW

የፕሪቶርያዉ ስምምነት ግምገማ
የኢትዮጵያ መንግስትና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባለስልጣናት ፕሪቶሪያ ላይ ያደረጉትን ስምምነት ሰሞኑን ተሰብስበዉ ሲገመግሙ ነዉ የሰነበቱት። ተሰብሳቢዎቹ የዛሬ 15 ወር የተፈራረሙት ስምምነት እስካሁን ገቢራዊ የሆኑና ያልሆኑ ክፍሎቹን ከነምክንያቶቹ  አንስተዉ መነጋገራቸዉ ተዘግቧል። በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበርነት የተደረገዉን ስብሰባ የአዉሮጳ ሕብረት፣የኢጋድና የዩናይትድ ስቴትስ ተወካዮች ሲታዘቡት ነበር።ስብሰባዉ ትናንት አብቅቷል።
አዳነ አስመላሽ፣ ስብሰባዉ እንደተጀመረ በX (የቀድሞዉ ትዊተር) በግሊዝኛ በጻፈዉ አስተያየት «የፕሪቶሪያዉ ስምምነት ለ14 ወራት የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሆኖ ዉጤት ባለማምጣቱ አሁን እንደገና አለም አቀፋዊ ሆነ።» የኔሁን ታዬ ባንፃሩ በፌስ ቡክ «አማራውን ያላሳተፈ ነገር መጨረሻው አያምርም። ሁለቱን ሕዝቦች ማቀራረብ፣ ማወያዬት ወደ ዕርቅ ማምጣት ከፖለቲካ ድርድሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆን ነበር።» ይላል።
እዉነት ይነገር ግን የየኔ ሁን  ታዬን አስተያየት የተቀበለዉ አይመስልም።እንዲያዉም ይጠይቃል። «ሕዝቦቹን ማን አራራቃቸውና? ራሳቸው ሕዝቦቹ ተቀራርበው መነጋገር ይችሉ የለ? የምን "የአስታራቂ ያለህ!" ነው?» 
ብሮኮ ያሲኖ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ አስተያየት ሰጪ፣ «በእኔ የግል እይታ የአፍሪቃ ህብረት ስምምነቱ በምን ደረጃ እየተጓዘ እንዳለና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በውይይት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ለመገምገም መቀመጡ መልካም ተግባር ነው።»
ጥላሁን ጌታቸዉ እሱም በፌስ ቡክ «ስምምነቱ:ጠቃሚ:ነዉ» ይላል ቀጠለም። «የሰዉ: ህይወት: በከንቱ መጥፋት:የንብረት ዉድመት ቀንሷል በሌሎች: ክልሎችም: እንደዚህ: አይነት: ስምምነት ቢፈጠር ጠቃሚ ነዉ።» ይላል።     

የፕሪቶርያዉ ስምምነት
የፕሪቶርያዉ ስምምነት ምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

የፓርላማ አባሉ ያለመከሰስ መብት መነሳት                          
ከመጨረሻዉ ርዕሳችን ላይ ደርሰናል።የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከፍተኛ ባለስልጣን ክርስቲያን ታደለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆናቸዉ ይዘዉት የነበረዉ ያለመከሰስ መብት ሥለመገፈፉ የተሰጡ አስተያየቶች ናቸዉ።አቶ ክርስቲያን የታሰሩት ባለፈዉ ነሐሴ 2015 ነበር።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ያለመከሰስ መብታቸዉን የተገፈፈዉ ግን ትናንት ነዉ። w
መልካሙ እያሱ ይጠይቃል።«እስከ አሁን ተቀምጦ ነበር እንዴ?» ብሎ።እሸቴ ካሴ ደግሞ የታሰረዉን ኃላፊነት ማን ይወስዳል?» ይላል ሁለት ጥያቄ? ትቤ ላቭ በፌስ ቡክ « አይዞን» ይላል ወይም ትላለች።«ጊዜ ይቀየራል።»
ናትናይም አዉራሪስ ይጠይቃል «ክስ ሳይመሠረትበት እንደት እስካሁን ታሰረ!?» እያለ በፌስ ቡክ።ገደፋዉ አበጀ እሱም በፌስ ቡክ «አስሮ ማጣራት» ይልና - «የተናገሩት ከሚጠፋ ---» አንጠልጥሎ ተወዉ። እኛም አበቃን።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ