1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሮተርዳም ማራቶን ኔዘርላንድስ ውስጥ ድል ተቀዳጅተዋል ። በቤጂንግ የግማሽ ማራቶን የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶችን ቻይናዊው ሯጭ ቀድሞ እንዲገባ ሩጫው ሆን ተብሎ ዝግ ማለቱ መነጋገሪያ ሆኗል ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ታሪክ ከ120 ዓመት በኋላ ባዬርን ሌቨርኩሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ጽፏል ።

https://p.dw.com/p/4eoSk
የጀርመን ቡንደስሊጋ የደጋጋፊዎች ድባብ
የጀርመን ቡንደስሊጋ የደጋጋፊዎች ድባብ ። ፎቶ ከማኅደርምስል INA FASSBENDER/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሮተርዳም ማራቶን ኔዘርላንድስ ውስጥ ድል ተቀዳጅተዋል ። በቤጂንግ የግማሽ ማራቶን የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶችን ቻይናዊው ሯጭ ቀድሞ እንዲገባ ሩጫው ሆን ተብሎ ዝግ ማለቱ መነጋገሪያ ሆኗል ። ቻይናዊው ሲያሸንፍ በተንቀሳቃሽ ምስል ያዩ አንዳንድ ተመልካቾች «አሳፋሪ ውጤት» ብለዋል ። በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተጀምሯል ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ታሪክ ከ120 ዓመት በኋላ ባዬርን ሌቨርኩሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ጽፏል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን አምስት ጨዋታዎች እየቀረው በ5 ለ0 ለዋንጫ ድል መብቃቱ ያስፈነጠዛቸው ደጋፊዎች ወደ ስታዲየሙ ተምመው ገብተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እና አርሰናል በገዛ ሜዳቸው ተሸንፈው የዋንጫ ግስጋሴያቸውን ገትተዋል ። ሽንፈታቸው ሉቶን ታወንን ድባቅ ለመታው ማንቸስተር ሲቲ መልካም አጋጣሚ ሆኗል ።

አትሌቲክስ

ኔዘርላንድስ ውስጥ በተከናወነው የሮተርዳም ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸቴ በከሬ 1ኛ በመውጣት ለድል በቃች ። አሸቴ ያሸነፈችው (2:19:30) በመሮጥ ነው ። በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ (2:04:50) 2ኛ ደረጃ አግኝቷል ። በዚህ ውድድር ያሸነፈው የኔዘርላንዱ ሯጭ ትውልደ ሶማሌያዊው አብዲ ናጊዬ (2:04:45)ነው ።  ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ለገሠ (2:05:16)የሦስኛ ደረጃ አግኝቷል ።  በሴቶች ተመሳሳይ የሮተርዳም ማራቶን ፉክክር ኬንያውያት አትሌቶች ቪዮላ ኪብዎት (2:20:57) እና ሴሊ ቼፕዬጎ ካፕቲች (2:22:46)አሸቴን ተከትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የመጋቢት 30 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አሳፋሪው የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ክስተት

ትናንት ቻይና ውስጥ በተከናወነው የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ፍጻሜ ወቅት እጅግ ግራ አጋቢ ክስተት ተስተውሏል ። በውድድሩ ኬንያውያን እና ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ፍጥነታቸውን ቀንሰው ቻይናዊው ሯጭ ወደ ፊት እንዲያልፍ በእጃቸው ሲያመለክቱ ታይተዋል ።  ይህን ድርጊት የሚያሳየው ቪዲዮ በቻይና የማኅበራዊ መገናኛ አውታር «ዌይቦ» በስፋት ተሰራጭቷል ። አፍሪቃውያኑ አትሌቶች ሆን ብለው ቻይናዊው እንዲያሸንፍ አስችለዋልም ተብሏል ።

በቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ቻይናዊው አትሌት ሔ ጂይ ውድድሩን ያጠናቀቀው (1:03:44) በመሮጥ ነው ። ከኢትዮጵያዊው አትሌት ደጀኔ ኃይሉ ቢቂላ እንዲሁም ከኬንያውያኑ ሮበርት ኬተር እና ዊሊ ምኛኛትም በ1 ሰከንድ ቀድሞ አንደኛ ወጥቷል ። አራቱ አትሌቶች ከ21 ኪሎ ሜርት በላይ በጋራ እጅብ ብለው ሲሮጡ እንደነበር ተዘግቧል ።

አንድ ከቤጂንግ ስፖርት ጽ/ቤት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሰው፦ «ምርመራ እያደረግን ነው» ብለዋል ። የምርመራ ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ተናግረዋል ። የውድድሩ አዘጋጆች የቤጂንግ ስፖርት ውድድሮች አስተዳደር እና ዓለም አቀፍ የልውውጥ ማእከልም ምርመራ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል ።

በቻይና የማኅበራዊ መገናኛ አውታር «ዌይቦ» ላይ አፍሪቃውያኑ አትሌቶች ዝግ ካሉ በኋላ ቻይናዊው ሲያሸንፍ በተንቀሳቃሽ ምስል ያዩ አንዳንድ ተመልካቾች «አሳፋሪ ውጤት» ብለዋል ። ወትሮ በርካታ የድል ውጤቶችን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ላይ ለተመልካቾች ይፋ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስለቻይናው አሳፋሪ ክስተት በገጹ ላይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የጻፈው ነገር የለም ። 

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ፦ ዘንድሮ ውብ ጨዋታዎችን በማሳየት እና በርካታ ግቦች እንዳይቆጠርባቸው በማድረግ የባዬርን ሌቨርኩሰን ተጨዋቾች በብርቱ ታግለዋል ። የትግላቸው ፍሬም በቡንደስሊጋው «ተፎካካሪ» ብቻ በሚል የሚቀለድባቸውን አስቀርቶ ከተፎካካሪነትም አሸናፊ መሆናቸውን አስመስክረዋል ። ለዚህ ድንቅ ድል ደግሞ የቀድሞ የሊቨርፑል ተጨዋች የ42 ዓመቱ ስፔናዊው አሰልጣኝ ሻቢ አሎንሶ በዋናነት ስሙ ይነሳል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ታሪክ ተጽፏል ። የዚህ ድንቅ ታሪክ ዋነኛ ጸሐፊ ደግሞ ስፔናዊው አሰልጣኝ ሻቢ አሎንሶ ነው ።

ባዬር ሌቨርኩሰን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የማይሆን የመሰለውን ዕውን አድርጓል ። እሁድ ዕለት ። ባዬር ሌቨርኩሰን ማሸነፉ አለያም አንድ ቀን ቀድም ብሎ የባዬር ሙይንሽን መሸነፍ የዘመናት ታሪክ የሚቀይር ክስተት መሆኑ የማያጠራጥር ነበር ። ቅዳሜ ዕለት ባዬር ሙይንሽን ኮሎኝን 2 ለ0 በማሸነፉ የባዬር ሌቨርኩሰን አምስት ጨዋታ እየቀረው ዋንጫ ማንሳት የሚወሰነው በነጋታው እሁድ ነበር ። ትናንት የሻቪ አሎንሶ ልጆች እንደተርብ እየተወረወሩ ታሪክ ጽፈዋል ። ተጋጣሚያቸው ቬርደር ብሬመንን 5 ለ0 አደባይተው ዋንጫውን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከእጃቸው አስገብተዋል ።

አሰልጣኝ ሻቢ አሎንሶ ባዬርን ሌቨርኩሰን በዘንድሮ ውድድር ለረዥም ጊዜያት እንዳይሸነፍ አስችሏል ። በእግር ኳስ ቡድኑ የ120 ዓመታት ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የቡንደስ ሊጋ ድል የባዬር ሌቨርኩሰን ደጋፊዎችን አስፈንጥዟል ። አሰልጣኝ ሻቢ አሎንሶም እንደዛው ።

«ያገኘነው ድል ትርጉም ለማወቅ እና ለማጣጣም ምናልባት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናል በቡንደስሊጋው አሸናፊ መሆን በራሱ ከባድ ነው ግን ደግሞ በዚያ አይነት አጨዋወታችን ማሸነፋችን ልዩ ነው ያን ማጣጣም አለብን ለእኛ እጅግ ለየት ያለ ዓመት ስለሆነም ልንገመግመው ይገባል ደስታችን ገና የምናጣጥምበት ቅጽበት ነው አሁን »

የባዬር ሌቨርኩሰን የእግር ኳስ ዳይሬክተር ሲሞን ሮልፍስ በበኩላቸው ለቡድናቸው ታላቅ ስኬት የቡድን ሥራ ወሳኝ እንደነበር ጠቅሰዋል ። የመጋቢት 23 ቀን 2016 የስፖርት መሰናዶ

«የቡድኑ መንፈስ እና በአጠቃላይ የልጆቹ ብቃት ልዩ ነው እጅግ በጣም የሚያኮራ። »

ለባዬር ሌቨርኩሰን አስደማሚ ድል አምስት አፍሪቃዊ ተጨዋቾች ሚናቸው ላቅ ያለ ነበር ። ናይጄሪያዊያኑ አጥቂ ቪክቶር ቦኒፌስ እና አማካዩ ናታን ቴላ፤ የሞሮኮው አጥቂ አሚኔ አድሊ፤ የአይቮሪ ኮስት ተከላካይ ኦዲሎን ኮሱዎኑ እና የቡርኪና ፋሶው ሌላኛው ተከላካይ ኤድሞንድ ታፕሶባ በባዬር ሌቨርኩሰን የ120 ዓመት ጉዞ ላይ አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል ።

የባዬር ሌቨርኩሰን ተጨዋቾች አሰልጣኝ ሻቪ አሎንሶ ላይ በትልልቅ ብርጭዎች የተሞላ ቢራ ሲደፉበት
የባዬር ሌቨርኩሰን ተጨዋቾች አሰልጣኝ ሻቪ አሎንሶ ላይ በትልልቅ ብርጭዎች የተሞላ ቢራ ሲደፉበት ። በቡንደስሊጋው ዋንጫ የማጝነት ድል ይህ የተለመደ ነው ምስል TH/Kirchner-Media/IMAGO

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እንደ አርሰናል እና ሊቨርፑል ደጋፊዎች የተበሳጨ የለም ። በ70 ነጥቡ በሁለቱ ቡድኖች በአንድ ነጥብ ተበልጦ ሦስተኛ የነበርው ማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ደግሞ ቦርቀዋል ። ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን ለማንሳት በሚደረገው የሦስቱ ቡድኖች ፉክክር ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት በለስ ቀንቶታል ። ተጋጣሚው ሉቶን ታወንን 5 ለ1 ድባቅ መትቷል ። በዚህ ጨዋታ ኧርሊንግ ኦላንድ 1 ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር ዘንድሮም የኮከብ ግብ አግቢነቱን ስፍራ አስጠብቆ ለመዝለቅ የቆረጠ ይመስላል ።

ኮከብ ግብ አስቆጣሪ

20 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ኧርሊንግ ኦላንድ በኮከብ ግብ አግቢነት መሪነቱን አስጠብቋል ። ትናንት በነበረው የአርሰናል እና አስቶን ቪላ ግጥሚያ አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም ተሸንፏል ። በዚህ ግጥሚያ ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው ኦሊ ዋትኪንስ ከኧርሊንግ ኦላንድ በአንድ ግብ ብቻ ነው የሚበለጠው ። 17 ግቦችን በማስቆጠር ሦስት ተጨዋቾች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የኒውካስሉ አሌክሳንደር ይሳቅ፤ የበርመሱ ዶሚኒክ ሶላንኬ እንዲሁም የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሣላኅ 17 ግቦች አላቸው ። የመጋቢት 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሊቨርፑል እንደ አርሰናል ሁሉ ትናንት በገዛ ሜዳው አንፊልድ ውስጥ በክሪስታል ፓላስ የ1 ለ0 ሽንፈትን አስተናግዶ ደጋፊዎቹን ኩም አድርጓል ። በሳምንቱ መጨረሻ ውጤቶች መሠረትም፦ ማንቸስተር ሲቲ የፕሬሚየር ሊጉን በ73 ነጥብ ይመራል ። አርሰናል እና ሊቨርፑል በ71 ነጥብ ግን ደግሞ በግብ ክፍያ ልዩነት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው ። አርሰናልን ጉድ ያደረገው አስቶን ቪላ በአራተኛ ደረጃ 63 ነጥብ ይዞ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱ ለጊዜው አስረግጧል ። የዋንጫ ባለቤቱም ሆነ የሻምፒዮንስ ሊግ አራት ተሳታፊዎች ማንነት ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ይለያል ። ዛሬ ማታ ቸልሲ ከኤቨርተን ጋ ይጋጠማል ። 44 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ይኛል ።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ይኖራል ።  ነገ ባርሴሎና ከፓሪ ሳን ጃርሞ፤ እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋ ይጋጠማሉ ። ረቡዕ ደግሞ ባዬርን ሙይንሽን ከአርሰናል እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ከሪያል ማድሪድ ጋ ይጫወታሉ ። አሸናፊዎች ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያልፋሉ ።  በአውሮጳ ሊግ ደግሞ፦ ሐሙስ አታላንታና ሊቨርፑል፤ ዌስትሀምና ባዬር ሌቨርኩሰን፤ ሮማ ከሚላን እንዲሁም ማርሴይ ከቤኔፊካ ጋ የመልስ ጨዋታ ያደርጋሉ ። 

በአውሮጳ ሊግ ሐሙስ አታላንታና ሊቨርፑል በተጫወቱበት ወቅት
በአውሮጳ ሊግ ሐሙስ አታላንታና ሊቨርፑል፤ ዌስትሀምና ባዬር ሌቨርኩሰን፤ ሮማ ከሚላን እንዲሁም ማርሴይ ከቤኔፊካ ጋ የመልስ ጨዋታ ያደርጋሉ ። ምስል Molly Darlington/REUTERS

የተጨዋቾች እና የአሰልጣኞች ዝውውር

በጀርመን የባዬርን ሙይንሽን እና የቮልፍስቡርግ እንዲሁም የሞናኮ የቀድሞ አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች ምናልባትም ተሰናባቹ ዬርገን ክሎፕን ሊተኩ ይችላል ሲል ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል ። በተያያዘ ሊቨርፑል እንግሊዛዊው የክንፍ ተጨዋች ማርኩስ ኤድዋርድስን በ30 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያስመጣ እንደሆነም ተዘግቧል ። የ25 ዓመቱ ማርኩስ የሚጫወተው ለፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝቦን ነው ። የፈረንሣዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ ማርኩስ ራሽፎርድን ለመውሰድ ፍላጎት እንደሌለ በመግለጡ በማንቸስተር ዩናይትድ ይቆያል ሲል ሰን ጋዜጣ ዘግቧል ። ቸልሲ ኔዘርላንዳዊው አማካይ ቶይን ኩፕማይነርስን ለማስመጣት አታላንታ ሊቨርፑልን ባሸነፈበት ጨዋታ ገምጋሚዎችን ልኮ እንደነበር ደግሞ ስፖርትሜዲያሴት በጣሊያንኛ አትቷል ። ባዬርን ሙይንሽን ተሰናባቹ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁልን ለመተካት ፍላጎቱ ካለው ሲል ዚነዲን ዚዳንን ማናገሩም ተዘግቧል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ