1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመኖሪያ ቤት ኪራይ አዋጅ እና አንድምታው

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ. ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ። መንግሥት አዋጁ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት በሚል ማርቀቁን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4eMEn
Stadtansicht Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

የመኖሪያ ቤት ኪራይ አዋጅ እና አንድምታው

የመኖሪያ ቤት ክራይን የተመለከተ አዋጅ ፀደቀ

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ. ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ።

መንግሥት አዋጁ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት በሚል ማርቀቁን አስታውቋል።

በአዋጁ መሠረት ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ተከራይ እስከ ሁለት ዓመት የመከራየት መብት የተሰጠው ሲሆን ፣ የመኖሪያ ቤት አከራዮች ይቋቋማሉ በተባሉ "ተቆጣጣሪ አካላት" በአመት አንድ ጊዜ በሚሰጡት የኪራይ ተመን ዋጋው የሚመራ እና የዘፈቀደ የክራይ ዋጋ ጭማሪን የሚያስቀር ነው ተብሏል።

ይህ አዋጅ ከፀደቀበት እለት ጀምሮ በነጋሪት ጋዜጣ መታተምን ሳይጠብቅ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ተነግሯል።

የአዋጁ አስፈላጊነት ምንድን ነው ?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ እስከ 9:30 የተወያዩበት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ለምን እንዳስፈለገ በምክር ቤቱ የመምግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቡልጅጌ አብራርተዋል።የቤት ክራይ ዋጋ ጭማሪ ክልከላ

"ግልጽነት፣ ተጠያቂነት ፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት" ነው ብለዋል።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው አዋጁ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ በደላሎች የሚመራውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሥርዓት ማስያዝ የዚህ ሕግ አላማ መሆኑን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው አዋጁ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ በደላሎች የሚመራውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሥርዓት ማስያዝ የዚህ ሕግ አላማ መሆኑን አብራርተዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

ዝርዝር የአዋጁ ድንጋጌዎች

አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ሆኖ በ3 ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ይህ አዋጅ የአዋጁን አፈፃፀም ለመቆጣጠር በሚቋቋም ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል በአመት አንድ ጊዜ አከራዮች አሁን የሚያከራዩበትን የገንዘብ መጠን መነሻ አድርጎ በሚያወጣው ተመን ቤት ማከራየትን የሚመራ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት በአከራዮች የነበረን የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ያስቀራል ተብሏል።

የአዋጁ አንደኛው አንኳር የተባለው ጉዳይ አንድ የመኖሪያ ቤት ተከራይ ቢያንስ ለ ሁለት አመታት በተከራየው ቤት ውስጥ መኖር እንዲችል አስቀድሞ ከአከራዩ ጋር የሚይዘው ውል ይፈቅድለታል። አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ መታተምን ሳይጠብቅ ከፀደቀበት እለት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን አከራይና ተከራይ ከዚህ በፊት የተዋዋሉበት ውል ቢቻል በአንድ ወር ፣ ቢበዛ በሦስት ወር ውስጥ መመዝገብ እንዳለበትም ተደንግጓል። የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ችግር

አዋጁ "የተከራይን ሰቀቀን እና ጭንቀት ይፈታል" የሚል እምነት እንደተጣለበት የገለፁት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ ሕጉ አስተዳደራዊ መሆኑን ገልፀው ፣ በአፈፃፀም ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩ የሚኖረው ቅጣትና ተጠያቂነትም አስተዳደራዊ እንጂ የወንጀል እንደማይሆን ገልፀዋል። የመንግሥት ቤቶች ሆነው ለመኖሪያ ቤት ኪራይ የሚዉሉት ከዚህ አዋጅ ተፈፃሚነት ወሰን ውጪ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ለምን እንዳላስፈለገ ያብራሩት ጌድዮን "የአዋጁን አላማ ማሳካት ስለማይቻል፣ ይህ ውሳኔ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ በእጥፍ ሊጨምር ስለሚችል እና ከቤት ውጣልኝ የሚል ንትርክ ሊከሰት ስለሚችል" ያንን ለመከላከል ነው ብለዋል።

አዋጁ የክልል ዋና ዋና ከተሞችንም እንደሚመለከት ተገልጿል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ሆኖ በ3 ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ይህ አዋጅ የአዋጁን አፈፃፀም ለመቆጣጠር በሚቋቋም ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል በአመት አንድ ጊዜ አከራዮች አሁን የሚያከራዩበትን የገንዘብ መጠን መነሻ አድርጎ በሚያወጣው ተመን ቤት ማከራየትን የሚመራ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት በአከራዮች የነበረን የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ያስቀራል ተብሏል።ምስል Ethiopian Press Agency

ውሳኔውን ደግፈው አስተያየት ከሰጡ ሁለት የምክር ቤት አባላት አንደኛው የሕጉን ተገቢነት ገልፀው፣ ነገር ግን በአተገባበሩ ላይ "ጥንቃቄ" እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ከአውሮጳ ጀርመን፣ ከኤስያ ቻይና፣ ከአፍሪካ ኬንያ ሕጉን ለማውጣት ልምድ ተወስዶበታል የተባለለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ አንዱን ጎድቶ ሌላውን የመጥቀም አላማ የለውም ተብሎለታል።

"መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማስፋት ስላልቻለ ወደ ቁጥጥር ሄደ" የሚል አዝማሚያ መኖሩን የገለፁት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ መንግሥት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከዚህ በፊት የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስጨረስ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እስከ 5.7 ቢሊየን ብር መመደቡን፣ የ20/ 80 መርሃግብርን እንደሚያግዝ እና ከግል ባለሃብቶች ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልፀዋል። የመኖርያ ቤት እጦትና የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት

አክለውም አዲስ አበባ ውስጥ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከገቢያቸው እስከ 70 በመቶውን አልፎ አልፎም ሙሉ ገቢያቸውን ለቤት ኪራይ እንደሚያውሉ ገልፀዋል። 

የቤት ኪራይ ችግር ስፋት

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳይደረግ በየጊዜው በከተማ መስተዳድሩ ክልከላ ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ግን መሰል የመንግሥት ውሳኔዎች የግለሰቦችን የግል ንብረትን የመጠቀም መብት የሚጋፋ  መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት ሌላ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ የሚገልፁት ሰዎች ብዙ ናቸው።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ