የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ጥሪ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2016የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ጥሪ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሒደት "አካታች እና ግልጽ እንዲሆን" የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከካርድ ጋር ተወያየ።
የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመረው የምክክር ሂደት ከጅምሩ "በተለያዩ ቡድኖች የአካታችነትና የግልጸኝነት ችግሮች እተነሱበት" ቢቆዩም ኮሚሽኑ ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራርያ ሳይሰጥ እና ዕርምት ሳይወስድ ወደ ቀጣይ የዝግጅት ምዕራፎች እተሸጋገረ ይገኛል ብሏል።
በዚህ ምክንያት "ምክክሩ የታለመለትን ዓላማ ላያሳካ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሳድሮብናል" ያለው ካርድ፤ ኮሚሽኑ ችግሮቹን ሊቀርፍበት የሚችልበትን መንገድ በይፋ እንዲያሳውቅ ይፋዊ የፊርማ ማሰባሰብ ሒደት ጀምሯል።
ይህንን የፊርማ ማሰባሰብ ሒደት ተከትሎ ካርድ በኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት በተደረገለት ጥሪ መሠረት ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ መወያየቱን አስታውቋል።//
ካርድ የጀመረው ፊርማ የማሰባሰብ ተነሳሽነት ዓላማ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያለፈው ሒደትና የምክክሩ ውጤት "በዘላቂነት ያመጣል የተባለለትን ሰላም፣ እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ በመንግሥትና በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያልውን ግንኙነት ለማደስ ይችላል ብለን አናምንም" ያለው ሀገር በቀሉ የሲቪክ ድርጅት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)፣ ኮሚሽኑ እየቀረቡለት ላሉት ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ "እስካሁን የተጫወተውን ሚና እናደንቃለን" ያለው ካርድ ኢትዮጵያውያን ያሉበት የግጭት ዐውድ "የኮሚሽኑን ሥራ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደደቀነበት" እንደሚረዳም አስታውቋል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሐሳብ ልዩነት ያላቸው አካላትን አካታችነትን እና የአካሔድ ግልጽነትን በተመለከተ ብዙ ቅሬታዎች እየተነሱ እንደሚገኙ ገልጿል።
ካርድ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያላቸው ጥያቄዎች ሳይፈቱ ከቀጠለ "ቀጣይ ዝግጅቶችን እና ዋናውን የምክክር መድረክ ማዘጋጀት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የሚያስከትላቸው ለውጦች የብዙኃን ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግ ይችላል የሚል ከፍተኛ ሥጋት" እንዳለውም አመልክቷል። በድርጅቱ የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ የሆኑትን አቶ መንግሥቱ አሰፋን ካርድ ስለጀመረው ፊርማ የማሰባሰብ ተነሳሽነት ዓላማ ጠይቀናቸዋል።
ካርድ እንደሚለው ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጅ አወጣጥ ሒደት ጀምሮ ተቋማዊ አደረጃጀቱን የሚመለከቱ የቅድመ መቋቋም ጉድለቶች፣ ከግጭቶች እና የግጭት ተዋናዮች ተሳትፎ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ማለትም እየቀጡሉ ካሉ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ታጣቂ ቡድኖቹ በሰላማዊ መንገድ የሀገራዊ ምክክሩ ላይ ለማካተት በኮሚሽኑ "በይፋ የተነደፈ ዕቅድ አለመኖሩ" ምክክሩ ግቡን እንዳይመታ ያደርገዋል የሚል ሥጋት እንዳለበት ገልጿል።
በሌላ በኩል ምክክሩን ከተለያዩ አካላት ተፅዕኖ ነጻ ማድረግን በተመለከተ፣ የምክክር ሒደቱ "ከመንግሥት ተፅዕኖ ራሱን የሚከልልበት አሠራር ባለመዘርጋቱ ወይም የዘረጋውን አሠራር ለባለድርሻ አካላት ግልጽ ባለማድረጉ" ሒደቱ ከጅምሩ ጀምሬ "ሲከተሉት የመጡ መሠረታዊ የተዓማኒነት፣ የአካታችነትና የግልጽነት ጥያቄዎች እስከመጨረሻው አብረውት እየተጓዙ በመሆኑ ምላሽ ይፈልጋሉ" ብሏል።
በምክክሩ እንድንሳተፍ አልተደረንም የሚሉ አካላት ቅሬታ እንዲሁም የአንዳንድ አካላት ያልተመጣጠነ ያለው ተሳትፎ እና ተፅዕኖ መኖር ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውንም ይሄው ድርጅት ገልጿል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን ካርድ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከድርጅቱ ጋር መወያየቱን ግልጿል። የድርጅቱ የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ አቶ መንግሥቱ አሰፋ ስለ ውይይቱ ተከታዩን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሒደት
ኮሚሽኑ ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ወደ አገራዊ ምክክሩ እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል። ሆኖም ግን የተሳካ አይመስልም። ይህም በምክክር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ ይነገራል።
ካርድ የተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አሁንም የፊርማ ማሰባሰብ ጥረቱን ቀጥሏል። ከተጽእኖ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን የሚገልፀው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በአዲስ አበባ ያጠናቀቀ ሲሆን ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ይህንኑ ተግባር እያከናወነ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ