የመብረቅ አደጋ በኢትዮጵያ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የመብረቅ አደጋ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከሰኔ እስከ መስከረም በሚቆየው ዝናባማ ወቅት በተለያዩ አከባቢዎች መብረቅ መጣሉ የተለመደ ነው፡፡ በመብረቅ ስለደረሱ ጉዳቶች መስማትም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በዚህ ዓመት በመብረቅ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በተለይ በአፋር ክልል ከወትሮው ከፍ ማለቱን የአካባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:00 ደቂቃ

በአፋር ክልል ብቻ 20 ሰው በመብረቅ ሞቷል

እዋ በአፋር ክልል ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷናት፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን ለሚገኙ አካባቢዎች የምትቀርበው ይህቺ ወረዳ በገላጣ ሜዳዎች የተሞላች ነች፡፡ የነሐሴ ወር ከገባ ያለማቋረጥ ከባድ ዝናብ እየዘነበባት የምትገኘው እዋ የዘንድሮው ክረምት ጉዳት ይዞባት መጥቷል፡፡ ስማቸው መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የወረዳው ነዋሪ በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት ያስረዳሉ፡፡

“እኛ አካባቢ አምስት ሰው የሚሆኑ ሞተዋል፡፡ ሞባይል እያነጋገሩ በድንገት በመብረቅ ተመትተው የተረፉ አሉ፡፡ እዋ ወረዳ ቦሎቶሞ፣ ቢሉ የሚባሉ ቀበሌዎች ነው መብረቅ ያረፈው፡፡ ቢሉ ቀበሌ አንድ ሰው አንድ ከብት ጋር ተመትቶ ሞተ፡፡ እዚህ ቦሎቶሞ ቀበሌ ደግሞ እንደዚሁ አንዲት ሴት ናት የሞተችው፡፡ ቶል አርባ አንዲት ሴት፣ ዱባ አንዲት ሴት፣ ሲያሎ ውስጥ አስረዲ የሚባል ጎጥ ላይ ባል እና ሚስት በመብረቅ ሞተዋል” ይላሉ ነዋሪ፡፡  

በአፋር ክልል የመብረቅ አደጋ የደረሰው በእዋ ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች ወረዳዎችም ባልተለመደ መልኩ ደጋግሞ በወረደ መብረቅ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አቶ ከድር አብደላ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ናቸው፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመብረቅ ምክንያት ስለደረሰው አደጋ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

“በየቀኑ መረጃዎች እንሰበስባለን፡፡ እነዚያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከመብረቅ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩትን አደጋዎች ጠቅለል አድርገን ስንደምረው ወደ 20 አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች እንደሞቱ እና 21 የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የሚያሳየው፡፡  በሰውም ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ እንስሳትም ስናይ ደግሞ ብዙ እንስሳቶች በዚያ በመብረቅ ጉዳት የደረሰባቸው መኖራቸውን ያመለክታሉ፡፡ እንደሚታወቀው የእኛ ማህበረሰብ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ከመሆኑ የተነሳ ሀብተ፣ ንብረቱ፣ ጥሪቱ እንስሳት ሆኖ እዚያም እንስሳቱም ላይ ጉዳት እንደደረሰም ጭምር ያሳያል” ይላሉ ኃላፊው፡፡

በአፋር ክረምቱ ከገባ ወዲህ እዋን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ከድር ይናገራሉ፡፡ የመብረቅ አደጋዎች በአፋር ክልል ብቻ የተወሰኑ ሳይሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱን መረጃዎች ይሳያሉ፡፡ በፌደራል የአደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን የተመዘገበው መረጃ ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ ነሐሴ 15 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ በመብረቅ የሞቱት ሰዎች ብዛት 29 መሆኑን ያመለክታል፡፡ በመረጃው ውስጥ በአፋር በመብረቅ የሞቱ ሰዎች ሁለት ብቻ ተብሎ መጠቀሱ የሟቾቹ ቁጥር ዝቅ እንዲል አድርጎታል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች 50 የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው መብረቅ በምን ምክንያት የሚከሰት ነው? ሳይንሳዊ አመጣጡን ያስረዱን ዘንድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑትን ዶክተር ድሪባ ቆሪቻ ጠይቀን ነበር፡፡ መብረቅ የሚፈጠረው በዝናባማ ወቅት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ድሪባ ምክንያቱም ለመብረቅ መፈጠር ምክንያት የሚሆኑት ክስተቶች በዚያን ጊዜ ስለሚኖሩ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

“ለመብረቅ መፈጠር መንስኤ የሚሆኑት ሁለት ዋና ዋና ክስተቶች  አሉ፡፡ እነሱም በከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የእርጥበት መጠን መኖር አለበት፡፡ በሁለለተኛ ደረጃ ደግሞ ከባቢ አየርን በሚገባ የሚያሞቅ ከጸሐይ የሚገኘው ኃይል ጠንካራ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው” ይላሉ ዶ/ር ድሪባ፡፡   

በጠዋት ወይም ቀትር ላይ ከፍተኛ የሆነ የጸሐይ ሙቀት በሚኖርበት ጊዜ በውሃ አካል፣ በተክሎች እና በአፈር ውስጥ የሚኖረው እርጥበት በትነት መልክ ወደ ከባቢ አየር እንደሚገባ የሚናገሩት ባለሙያው ይህ ትነት ወደ ሰማይ እየራቀ በሚሄድበት ጊዜ የሚፈጠረውን እንዲህ  ያብራራሉ፡፡ 

“ከዚያ በኋላ የውሃ ትነት ቀስ በቀስ ወደ ከፍታ በሚወጣበት ጊዜ በተወሰነ መልኩ እየቀዘቀዘ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ትንንሽ ትነት ያለው ውሃ ይያዝና ዳመና ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ጊዜ ከመሬት ገጽ ከ ዘጠኝ እስከ 12 ኪሎ ሜትር ከፍታ ያለው ቁልል ደመና የምንለው ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ በቁልል ዳመና ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የታመቀ፣ ሙቀት የያዘ ውሃ ስላለ ውሃው ወደ ከፍታ በሄደ እና እየቀዘቀዘ በሚሄድበት ጊዜ በረዶ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ያ በረዶ በንፋስ ኃይል በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በረዶ ከበረዶ፣ ዳመና ከዳመና፣ ሌሎች ጥቃቅን የማይታዩ የውሃ አካላት እርስ በእርስ ይጋጫሉ ማለት ነው፡፡ በሚጋጩበት ጊዜ ብልጭታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በሂደት ነው፡፡ 

ብልጭታው እየተፈጠረ በሚሄድበት ጊዜ በጣም ደመናው ክብደት ሲኖረው፣ መሸከም ሲያቅተው ከዳመናው በላይ ጫፉ ላይ ማለት ነው ትልቅ የበረዶ ክምችት ይኖራል፡፡ ዳመናው ወደ ታች እየገፉት ይሄዳሉ፡፡ እርስ በእርስ ሲጋጩ ይሄ ብልጭታ ሲፈጠር ከላይ ባለው ዳመና እና ከታች ባለው ዳመና የኤሌክትሪክ ቻርጅ ይፈጠራል፡፡ ከላይ ያለው ደመና ፖዘቲቭ ቻርጅ የሚባለው ነው የሚፈጥረው፡፡ የዳመናው ታችኛው ክፍል ደግሞ ኔጊቲቭ የሚባለውን የኤሌክትሪክ ቻርጅ ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ እነኚ ሁለቱ እንግዲህ  በአንድ በኩል ይሳሳባሉ፡፡ ተመሳሳይ ቻርጅ ያላቸው ደግሞ ፖዘቲቭ ከፖዘቲቭ ጋር ይጋፋል፡፡ ፖዘቲቭ እና ኔጌቴቩ እርስ በእርስ ይሳሳባል ማለት ነው፡፡ በሚሳሳብበት ጊዜ መሬት ገጽ ላይ ያሉ ቁስ አካላት (ህይወት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው) ፖዘቲቭ እና ኔጌቲቭ ቻርጅ ይኖራቸዋል፡፡ ዳመና ስር ወይም ግርጌ ላይ ያለው ኔጌቲቭ ቻርጅ መሬት ላይ ካለው ፖዘቲቭ ቻርጅ ጋር ይሳሳባሉ ማለት ነው፡፡ በሚሳሳቡ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ድምጽ እና ብልጭታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ መብረቅ ወይንም ከብልጭታ ጋር ተያይዞ የሚወርደው ኃይል ሊፈጠር የሚችለው” ሲሉ ስለ መብረቅ አፈጣጠር ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡

“መብረቅ ሰውን እንዴት ነው የሚገድለው?” ባለሙያው ምላሽ አላቸው፡፡ “በዳመና ውስጥ እንግዲህ ከፍተኛ የሆነ የታመቀ ኃይል አለ ብያለሁ፡፡ ስለዚህ ከዳመናው ታችኛው ክፍል የተጠራቀመው ኔጌቲቭ ቻርጅ እና መሬት ላይ ያለው ፖዘቲቭ ቻርጅ በሚሳሳብበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ኃይል ፍሰት ይኖራል ወይም ኤሌክትሪክ ይፈሳል፡፡ ምንድነው ተመራማሪዎች አጥንተው እስካሁን ድረስ የደረሱበት በአንድ ብልጭታ ውስጥ ያለው ሙቀት ወይም ኃይል ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማመንጨት ይችላል፡፡ አስር ሺህ ሜጋ ዋት ማለት እንግዲህ ማንኛውም ነገር ሊቋቋመው የማይችለው ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ  ይሄ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ያለው ኤሌክትሪክ ብዙውን ጊዜ ከመሬት ገጽ በላይ በከፍታ ያሉ እንደ ዛፍ፣ ሰው፣ ትንንሽ ቁጥቋጦዎች ወይም እንስሳት በሜዳ ላይ ካሉ፣ ቤት፣ ህንጻ በመሳሰሉት አማካኝነት ከዳመናው የታችኛው ክፍል ወደ መሬት ይፈሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳት የሚያስከትለው ምንድነው? ሙቀቱ በእነኚህ ቁስ አካላት በሚያልፍበት ጊዜ የመሰነጣጠቅ፣ የማቃጠል ፣ የማውደም እና የማቅለጥ ክስተት ያስከትላል” ሲሉ ጉዳቱ በምን መልክ እንደሚከሰት ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሚቴዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለረጅም ዓመታት የሰሩትን ዶ/ር ድሪባን የመብረቅ አደጋ እንዲህ እንዳሁኑ ዓመት መበርከቱ የተለመደ እንደው ጠይቄያቸው ነበር፡፡ “አደጋውስ ለምን በአፋር ክልል በረታ?” የሚል ተጨማሪ ጥያቄ አንስቼላችኋለሁ፡፡ 

“በኢትዮጵያ ውስጥ ዝናባማ ወቅት የምንለው ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉትን አራት ወራት የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በስተቀር አብዛኛው ክፍል ዋነኛውን የዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ  በአብዛኛው መብረቅ የሚስተዋለው እና የተለመደው በእርግጥ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ጥቅጥቅ ያለ ደን አለ፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ የሆነ እርጥበት ስላለ፣ ምንጩም እዚያው ስለሆነ የሚፈጠረው ዳመና ብዙውን ጊዜ ቁልል ዳመና ይሆንና ከሚያገኘው ሙቀት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መብረቅ የሚስተዋልበት ነው፡፡ ሌላው ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ምስራቅ ኢትዮጵያም ለእርጥበት ምንጭ ቅርብ ስለሆነ ማለት ከአረብ ባህር እና ከህንድ ውቅያኖስ የሚገባው እርጥበት ቅርብ ስለሆነ እዚያ አካባቢ ይስተዋላል፡፡ 

በሶስተኛ ደረጃ እንግዲህ የአፋር ክልል የሚታወቀው በተለይ በሐምሌ እና ነሐሴ ላይ የሙቀት መጠኑ እጅግ የሚጠነክርበት ጊዜ ነው ባብዛኛው የቀኑ የሙቀት መጠን እስከ 45፣ 47 ዲግሪ ሴልሼየስ የሚደርስበት ወቅት ሰለሆነ ከፍተኛ ሙቀት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ቅርብ ካለው የአረብ ባህር እና ቀይ ባህር የሚገባው እርጥበት በሚጠናከርበት ጊዜ አልፎ አልፎ የዚህ አይነት ነጎድጓድ ዘል ዳመና የሚስተዋልበት ሁኔታ አለ፡፡ ምክንያቱን የዝናባማ ቀናትም በዚያ አካባቢ ላይ በጣም ውሱን ነው፡፡ ቢበዛ አንድ ወር ተኩል ነው የሚዘንበው ግን ሲዘንብ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ዶፍ የሚጥልበት እና አልፎ አልፎ እንግዲህ የመብረቅ ክስተት የሚከሰትበት ነው፡፡ የተለመደ አይደለም ግን አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ዝናብ በሚኖርበት ጊዜ የዚያን ዓይነት አጋጣሚ ይስተዋላል” ሲሉ በአፋር መብረቅ የበዛበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡

መብረቅ በዝናባማ ወቅት የሚከሰት በመሆኑ በገጠር ያሉ ነዋሪዎች ተከታዮቹን ጥንቃቄዎች እንዲያደርጉ ባለሙያው ይመክራሉ፡፡ “አንደኛው ነገር በዝናብ ውስጥ አለመሄድ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በተቻለ መጠን ብረት ነክ የሆኑ ቁስ አካላትን አለመያዝ ነው፡፡ ሬድዮ አለማዳመጥ፣ መዝጋት፤ ቴሌቪዥን አለማየት ሞባይልን ማጥፋት ይመረጣል፡፡ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና አሌሌክትሪክን አለመጠቀም ይመረጣል፡፡ ብዙውን ጊዜ ዣንጥላ አለመጠቀም ነው፡፡ ምክንያቱም ዣንጥላ ውስጥ ብረት ስላለ በብረቱ አማካኝነት ይሄ ሙቀት ተስቦ በሰው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዝናብ መመታቱ ነው የሚሻለው፡፡ ሶስተኛ ከዝናቡ ዛፍ ስር አለመጠለል ነው፡፡ ወይንም ከብቶችን በሚበዙበት አካባቢ አለመቆየት ነው፡፡ ጎድጓዳ አካባቢ፣ ቦይ ወይም ሸለቆ አካባቢ ካለ እዚያ ስር ዝናቡ እስኪያልፍ መደበቁ ነው የሚሻለው፡፡ በዚህ ላይ በጎርፍ ላለመወሰድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ይላሉ ዶ/ር ድሪባ፡፡

በአፋር የእዋ ወረዳ ነዋሪው መብረቅን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ያውቁ እንደው ሲጠየቁ የ“ፈጣሪ ስራ” ስለሆነ “መከላከያ የለንም” ይላሉ፡፡ በቅርቡ በወረዳቸው የደረሰው ጉዳት ግን ያስተማራቸው እንዳለ አልሸሸጉም፡፡ “መቼም ከዚህ ከዛፍ ስር ተጠልሎ የሚመታ አለ፣ ሳይመታ የሚቀር አለ፡፡ የእግዚያብሔር ጉዳይ ነው ብለን ስለምናስብ እንዲህ አይነቱን ነገር ትኩረት ሰጥተን አንነጋገርም፡፡ አሁን እኛ ሞባይል እየተነጋገሩ እያለ ሞባይላቸው ከእጃቸው ጭምድድ አለ፡፡ [በመብረቅ] ተመቱ፡፡ ያው በህመም ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በእኛ ባለንበት በአፋር ባህል ዳጉ የሚባል አለ፡፡ ዜና እርስ በእርስ ማስተላለፍ ነው፡፡ በዚያ መልኩ በዳጉ ዝናብ በሚጠልበት ጊዜ ማንም ሞባይል እያነጋገረም ሆነ ከፍቶ እንዳይሄድ፣ ባትሪ ድንጋያቸውን አውጥተው ከመብረቅ ጋር ተያይዞ አደጋ እንዳያደርስባቸው ዳጉ ተደራርገናል” ሲሉ የአካባቢው ሰው የደረሰበትን ስምምነት ያጋራሉ፡፡

የአየር ንብረት ተመራማሪው እንደ ገጠሩ ሁሉ ለከተማ ሰዎችም የጥንቃቄ ምክር አላቸው፡፡ “በአብዛኛው ቤት በሚሰራበት ጊዜ ብረት፣ ገመድ ይዘረጋል፡፡ ከቤቱ ጫፍ መሬት ውስጥ የሚገባ ማለት ነው፡፡ ያንን ገመድ ይዞ መሬት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በእርሱ ብቻ አይደለም መከላከል የሚቻለው፡፡ ቤት ውስጥ ያሉ [የኤሌክትሮኒክስ] መሳሪያዎች ሊወድሙ ስለሚችሉ ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን የመሳሰሉትን መንቀል ነው፡፡ የእዚህ አይነት ዝናብ በሚኖርበት ጊዜ ወይንም ብልጭታ፣ ነጎድጓድ በሚሰማበት ጊዜ ኃይል መሙላት (ቻርጅ ማድረግ) ጥሩ አይደለም፡፡ በመኪና የሚጓዝ ሰው ካለ ደግሞ በተቻለ መጠን መስኮቶችን መዝጋት፣ ሬድዮ አለማዳመጥ፣ በግልጽ መኪና አለመሄድ ነው፡፡ ከመኪና ኋላ [መጫኛው] ላይ ወጥቶ አለመሄድ ይመረጣል” ሲሉ የጥንቃቄ ምክራቸውን ይደምድማሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic