የመስጊዶቹ መቃጠልና የጤፍ ውዝግብ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 08.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የመስጊዶቹ መቃጠልና የጤፍ ውዝግብ

ጎንደር ውስጥ በአንድ የሙስሊም ሠርግ ላይ ክርስትናን የሚነቅፍ ድርጊት ተፈፅሟል በሚል ከተማይቱ ዉስጥ የሚገኙ ሁለት መስጂዶች መቃጠላቸው እና ከጤፍ የሚገኙ ምርቶች መብት ባለቤትነት ላይ የውጭ ሃገራት ኩባንያዎች መወዛገባቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሳምንቱ ዐበይት መነጋገሪያ ጉዳዮች ነበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:49

የማኅበራሚ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጎንደር ውስጥ በአንድ የሙስሊም ሠርግ ላይ ክርስትናን የሚነቅፍ ድርጊት ተፈፅሟል በሚል ከተማይቱ ዉስጥ የሚገኙ ሁለት መስጂዶች ተቃጥለዋል።  በሳይንሳዊ ምርምር በሚል የጤፍ ባለቤትነት መብቷን አሳልፋ ሰጥታለች የምትባለው ኢትዮጵያ መብቷን ለማስመለስ ላይ ታች ማለት መጀመሯም አነጋግሯል፤ በዚሁ ሳምንት። ከጤፍ የሚገኙ ምርቶች መብት ባለቤትነት የእኔ ነው የሚል የኔዘርላንድ ኩባንያ ሌላ የኔዘርላንድ ኩባንያ ላይ ዘሄግ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ውድቅ ተደርጓል። በጤፍ ጉዳይ ላይ ኔዘርላንድ ውስጥ ማንም ባለመብት እንደሌለውም በዚሁ ሳምንት ውሳኔ ተላልፏል። 

የጤፍ ባለቤትነት መብትን የማስመለስ ዘመቻ

ሰሞኑን በኔዘርላንድስ የሚገኙ ሁለት የውጭ ኩባንያዎች በጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ ያደረጉት የፍርድ ቤት ሙግት መዘጋቱ ተሰምቷል። ዘ ሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረትም በኔዘርላንድስ ማንም የጤፍ ባለቤትነት መብት የለውም ተብሏል። ኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪዎች በአንድ በኩል ፍርድ ቤቱ ለኢትዮጵያ ወሰነ በሚል የተሳሳተ መረጃዎችን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሰራጭተዋል።

ቡ ብርሃን በሚል ፌስ ቡክ የቀረበ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ «ኢትዮጵያዉያኖች የጤፍ ብቸኞቹ ባለቤቶች እንደሆኑ ኔዘርላንድ ውስጥ በተላለፈው የሕግ ውሳኔ መሰረት ተረጋግጧል። ኔዘርላንደሮች የጤፍ ባለቤትነታቸውን ተቀምተዋል።»

ኢብራሒም ሰዒድ በበኩሉ በትዊተር ጽሑፉ የጤፍ መብት ለኢትዮጵያ እንደተመለሰ ይጠቅሳል። «ረጂም ጊዜ በወሰደው የጤፍ ባለመብትነት ጉዳይ በሀገረ ኔዘርላንድ ዘሄግ ላይ በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድ የተደረገው ክርክር በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቋል እየተባለ እኛም እየቦረቅን ነው» ሲል ጽፏል።

በርካቶች የኔዘርላንዱ ፍርድ ቤት ለኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብት ፈረደ፤ የጤፍ መብት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ ሲሉ በደስታ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተጋብተዋል። አድርገው በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ከጤፍ የሚገኙ ምርቶች መብት ባለቤትነትን የሚመለከተው የኔዘርላንዱ የፍርድ ቤት ውሳኔን ለኢትዮጵያ እንደተሰጠ አድርገው የወሰዱት የአቶ ፍጹም አረጋ የትዊተር መልእክት ብዙዎች ጋር ከደረሰ በኋላ ነው።  

በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኾነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ፍጹም አረጋ በእንግሊዝኛ የትዊተር ጽሑፋቸው ሰበር ዜና ሲሉ ቀጣዩን ጽፈዋል። «ሰበር ዜና፤ እንኳን ደስ ያለን፤ ምሥጋና ለሁላችሁም» ሲል ይንደረደራል የአምባሳደሩ ጽሑፍ። ዘ ሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት የጤፍ ባለመብት ነኝ የሚለው ኩባንያን በመቃወም ውሳኔ ማሳለፉን የጠቀሱት አቶ ፍጹም፦ «ይኽ ታላቅ ዜና ነው። ብሔራዊ እሴቶቻችን በኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ወዳጆች መጠበቅ  እንዳለባቸው ከዚህ መማር እንችላለን የሚል ተስፋ አለኝ»  ብለዋል።

ዳዊት ሰለሞን በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ተችቷል። «ባድመ ተወሰነ ብለው ሰልፍ ያስወጡን ሰዎች በጤፍ መጡ "ጤፍ ተወሰነልን "ባሉን ቅፅበት ወፍ የለም» በማለት።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፦ በትዊተር የመገናኛ አውታር ገጻቸው ላይ ጤፍን በተመለከተ የተሰራጨው መረጃ አሳሳች እና ትክክል ያልኾነ እንደነበር ጠቁመዋል። «ሙግቱ የነበረው በኹለት የግል ኩባንያዎች መካከል ሲኾን፤ ኔዘርላንድ ውስጥ የተሰጠው ብይን ከኢትዮጵያ መብት ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም። እንዲያም ኾኖ ኢትዮጵያ መብቷን ለማስከበር ዝግጅቷን አጠናቃለች» ብለዋል።

ፌስ ቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ፦«ኢትዮጵያ ገና ከሌላ የሆላንድ ኩባንያ ጋር ክርክር አላት ማለት ነው?....ይደንቃልል» ሲል የጠየቀው ደረጀ በላይ ታደሰ፦"ከሞኝ በራፍ ሞፈር ይቆረጣል" አሉ» ሲል ትዝብቱን ገልጧል።

ነገሩ እንደዘበት የጀመረው፤ ጥናት እና ምርምር እናድርግ በሚል ነበር ። የዛሬ 12 ዓመት ግድም። ያኔ የኔዘርላንዱ ዓለም ዓቀፍ የጤናና የምግብ አዘገጃጀት በምህጻሩ (HPFI) ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም ጋር አብሮ ለመሥራት ውሱን የመግባቢያ ሰነድ ይፈራረማል። ኩባንያው ምርምር እንዲያደርግባቸው በሚልም 1400 ኪሎ ግራም ማለትም ወደ 14 ኩንታል፤ 12 አይነት ዝርያ ያላቸው የጤፍ አይነቶችን ወደ ኔዘርላንድ እንዲወስድ ይደረጋል። ብዙ ሳይቆይ ግን ኩባንያው ከሰርኩ ብሎ፤ በጎን ኔዘርላንድ ውስጥ የጤፍ የባለቤትነት መብት ይገባኛል ሲል አመለከተ።

ኩባንያው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ለማድረግ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጥረት አድርጋ እንደነበር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ከዚህ ቀደም ከዲደብሊው ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ተናግረው ነበር። የኔዘርላንዱ ኩባንያ ባይሳካለትም ቅሉ፦ ከአዉሮፓ ሃገራት በተጨማሪ በአሜሪካና በጃፓን ጤፍን በባለቤትነት ለማስመዝገብ ተንቀሳቅሶ ነበር።

የኔዘርላንድ ኤምባሲ ከጤፍ የሚገኙ ምርቶች ላይ የቀረበው የባለቤትነት መብት ጉዳይ ሙግት መዘጋቱን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ላይ ገልጧል። «ብይኑ አኹን ተጠናቋል» ያለው ኤምባሲው የባለቤትነት መብት አለኝ ባለው ኩባንያ የቀረበው «ጥያቄ ኔዘርላንድ ውስጥ ሕጋዊ አይደለም» ብሏል። የፍርድ ቤቱ ሙግት ብይን የተሰጠበት ኅዳር ወር ላይ ቢኾንም እስካሁን ይፋ ሳይደረግ ቆይቶ የነበረው ይግባኝ የሚል ካለ እድል ለመስጠት እንደነበር ኤምባሲው አክሏል። ኾኖም በተሰጠው የጊዜ ገደብ ይግባኝ ባይ ባለመቅረቡ ውሳኔው መጽናቱን ይፋ አድርጓል።​​​​​​​

የኔዘርላንዶቹ ኩባንያዎች የጤፍ ባለመብት «እኔ ነኝ የለም እኔ» ሲሉ መካሰሳቸው ያስደመመው ወንድወሰን ዳርሴቦ፦ «ፈረንጆቹ "ከመ ጤፍም አልቆጠሩን፤ በሰው ጤፍ ሲካሰሱ" ሲል ጽፏል ትዊተር ላይ።

ዳግም መኮንን ደግሞ፦ «ይሄን ጤፍ የኔ ነው የሚለውን ሰውዬ ለአንድ ዓመት ቁርስ ምሳ እራቱን እንጀራ በሚጥሚጣ ብቻ እንዲበላ ማዘዝ፤ በማግስቱ እጅ ይሰጥ ነበር። ይሄን ፊት ከሰጡት ኢትዮጵያም የኔ ናት ይላል፤ እነሱም የባለቤትነት ምዝገባውን እምቢ አይሉትም። እብድ ዓለም» ሲል በቀልድ በተዋዛ ጽሑፉ ገልጧል።

«ብሔር አልባውን ጤፍን ማን ይጩህለት? ብሔር ብሔረሰቦች አሁን አብራችሁ የምትቆሙለት አጀንዳ ተፈጥሯል ዳይ ወደ ሥራ!» ሲል የጻፈው ደግሞ ዮሐንስ አካ ነው ትዊተር ላይ።

ናቃቸው አትዘንጋ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «አይ የኢትዮጵያ 27 ዓመት የኋላ ጉዞ፤ መሪዎቿ በኮንትሮባንድ ንግድ ሲባዝኑ ምን ያልተዘረፈችው አለ? ያሳዝናል» ብሏል።

የመስጊዶቹ መቃጠል

Symbolbild Religion Islam Christentum

ባሳለፍነው ሳምንት ደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ እየሱስ ከተማ ሁለት መስጊዶች መቃጠላቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ሌላኛው መነጋገሪያ ርእስ ነበር። ከአንድ ማተሚያ ቤት እንደወጣ የተነገረለት የኦርቶዶክስ እምነት መገለጫ የኾነ ምስል በአንድ የሙስሊም ሰርግ ላይ ተቆራርጦ ተገኘ መባሉ ያስነሳው ቁጣ ለመስጊዶቹ መቃጠል ሰበብ መኾኑ ተነግሯል። አብዛኛው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ክርስቲያን ሙስሊም በሚል ሳይለዩ የመስጊዶቹን መቃጠል አውግዘዋል። በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ቤተ አምልኮዎች ፈጽሞ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደማይገባም አበክረው አሳስበዋል።  

ሳሚ ሳሚ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «በደቡብ ጎንደር እስቴ ወርዳ የተቃጠለውን መስጂድ የአቃጠሉት ሰዎች በአስችኳይ ተጣርቶ ለፍርድ እዲንዲቀርቡ እንጠይቃለን።»

የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ የእስቴው ድርጊት በአኹኑ ወቅት ሊፈጸም የማይገባው መኾኑን ለዲ ደብሊው ተናግረዋል።  በውይይት ሊፈታ የሚገባው ነው ሲሉም አክለዋል። በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት 17 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መስጊዶቹ ወደተቃጠሉበት ስፍራ እንደሚያሄድ ገልጠዋል።  «የኮሚቴው የልዑካን ቡድን በቦታው በመገኘት አጋርነቱን የሚገልጽ ሲሆን ለመስጊዶቹ መልሶ ግንባታ እየተደረገ ያለውን ጥረት በተለያየ መልኩ ለማገዝ እንደሚንቀሳቀስም ታውቋል» ብለዋል ፌስቡክ ገጻቸው ላይ።

መምህር ዘመድኩን በቀለ ፦ «የእስቴውን መስጊድ እንሠራዋለን» በሚል ርእስ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባስነበበው ጽሑፉ፦ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ፍፁም ሰላማውያን፣ ፍቅር መሆናችንን ስናሳይ የምንውልበት ቀን ነው ዛሬ» በማለት የእምነት መቃቃር የሚፈጥሩ አካላትን ሴራ ለማክሸፍ ትብብር ወሳኝ መኾኑን ጠቁሟል። መስጊዶቹን ለማሠራት ኮሚቴ መቋቋሙን፤ የባንክ ሒሳብ ቁጥርም መከፈቱን ዘለግ ባለው ጽሑፉ ጠቅሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic