1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 11 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 11 2013

በጀርመን ቡንደስሊጋ ታዳሚያን በተወሰነ ደረጃ ስታዲየም መግባት ተፈቅዶላቸዋል። ባየር ሙይንሽን ከሻልከ ጋር ባደረገው የመክፈቻ ግጥሚያ ግን ተመልካቾች ስታዲየም እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ስምንት ግጥሚያዎች 39 ግቦች ተቆጥረዋል። ሊቨርፑል በዐሥር ተጨዋች የተወሰነው ቸልሲን አሸንፏል።

https://p.dw.com/p/3inut
Tour de France 2020 - 21. Etappe - Tadej Pogacar
ምስል Benoit Tessier/Reuters

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ታዳሚያን በተወሰነ ደረጃ ስታዲየም መግባት ተፈቅዶላቸዋል። ባየር ሙይንሽን ከሻልከ ጋር ባደረገው የመክፈቻ ግጥሚያ ግን ተመልካቾች ስታዲየም እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ስምንት ግጥሚያዎች 39 ግቦች ተቆጥረዋል። ሊቨርፑል በዐሥር ተጨዋች የተወሰነው ቸልሲን አሸንፏል። ሳዲዮ ማኔ ዳግም ብቃቱን ዐሳይቷል። የቱር ደ ፍሯንስ 21ኛ የመጨረሻ ዙር የብስክሌት ሽቅድምድም በስሎቬኒያ ብስክሌተኞች የበላይነት ተጠናቋል።

የጀርመን ቡንደስሊጋ ባሳለፍነው ዐርብ በባየር ሙይንሽን እና ሻልከ የመክፈቻ ግጥሚያ ተጀምሯል። በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያቸውን ካስተናገዱ 9 ቡድኖች መካከል በስድስቱ ስታዲየሞች ተመልካቾች እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር። የመክፈቻ ውድድሩ ግን ያለተመልካች ነበር የተከናወነው።

Fußball Bundesliga | VfB Stuttgart | Stadion Tribüne
ምስል picture-alliance/dpa/M. Murat

ባለፈው ሳምንት የሙይንሽን ከተማ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ቊጥር ቀደም ሲል ከነበረው መጠን በመጨመሩም ነበር በከተማው ከንቲባ ውሳኔ ስታዲየም ውስጥ ታዳሚያን እንዳይገቡ የተከለከለው። ምንም እንኳን ሰዉ ስታዲየም እንዳይገባ ቢከለከልም በከተማው አንዳንድ ቦታዎች ላይ በርካታ ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ተሰብስበው ሲዝናኑ ታይተዋል።

አሊያንስ አሬና ስታዲየም ውስጥ የባየር ሙይንሽን እና ሻልከ ግጥሚያን 7,500 ኳስ አፍቃሪዎች እንደሚታደሙ ተጠብቆ ነበር። ኾኖም ያለተመልካች በተከናወነው የመክፈቻ ግጥሚያ በርካቶችን ያስገረመ ክስተት ታይቷል። ስታዲየም ውስጥ የባየርን ሙይንሽን ኃላፊዎች ያለ ምንም ጥንቃቄ ጎን ለጎን ተጠጋግተው መቀመጣቸው አነጋጋሪ ኾኗል። ኃላፊዎቹ የአፍ እና የአፍንጫ መከለያ አንዳቸውም አላደረጉም ነበር።

ባየር ሙይንሽ

ባየር ሙይንሽን ሻልከን 8 ለ0 ጉድ አድርጎ ዘንድሮም ኃያልነቱን አስመስክሯል። ሠርጌ ግናብሬ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። ሌሮይ ሳኔም በቀድሞ ቡድኑ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ቀሪ ግቦች፦ የሊዮን ጎሬትስካ፤ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ፤ ቶማስ ሙይለር እና ጃማል ሙሳይላ ነበሩ። ስምንት ግቦች ከተቆጠሩ በኋላ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ፦ ሠርጌ ግናብሬ፤ ሊሮይ ሳኔ እና ተከላካዩ ጄሮም ቦአቴንግን በጊዜ እንዲያርፉ አድርገዋል።

Fußball Bundesliga FC Bayern München - FC Schalke 04
ምስል Matthias Balk/dpa/picture alliance

ጃማል ሙሲያላ በባየር ሙይንሽን ታሪክ በእድሜ ትንሽ ኾኖ ግብ በማስቆጠር የመጀመሪያው ኾኗል። ታዳጊው አማካይ አጥቂ 17 ዓመት ከ6 ወር ከ23 ቀን ነበር ግቡን ሲያቆጥር። በ72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በ81ኛው ላይ ነበር የመጀመሪያ ግቡን ከመረብ ያሳረፈው። ጃማል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 ከቸልሲ ነበር ወደ ባየርን ሙይንሽን የተዛወረው። ከዛ በፊት ለቸልሲ 8 ዓመት ተጫውቷል። እንግሊዛዊው ጃማል ወላጆቹ ከጀርመን እና ናይጀሪያ ናቸው። በ7 ዓመቱ ነበር ወደ እንግሊዝ ከወላጆቹ ጋር ያቀናው።

የጃማላ የቀድሞ አማካሪ ወንድም ካሉም ሑድሰን ኦዶይ ከቸልሲ ወደ ባየርን ሙይንሽን መዛወሩ ጃማል ወደ ባየርን እንዲመጣ መንገድ ከፍቷል። ጃማል ለባየርን ወጣት ቡድን በሦስተኛ ዲቪዚዮን እየተሰለፈ ብቃቱን ዐሣይቶ ነበር። በሻምፒዮንስ ሊግ ባየር ሙይንሽን ባርሴሎናን 8 ለ2 ሲያሸንፍ ታዳጊ ቢኾንም እንደ ቡድን አባልነቱ አብሮ በመጓዝ ተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር።

ባየር ሙይንሽን ዘንድሮ በርካታ ታዳጊ ወጣቶችን ያሰልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ከፓሪስ ሳንጄርማ የመጣው የ18 ዓመቱ ታንጉይ ኒያንዙም ከባየርን የወደፊት ተስፋዎች እንደ አንዱ ተደርጎ ተወስዷል። ከደረሰበት የታፋ ጉዳት ሲያገግም ብቃቱን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።  

ከሁለት ዓመት በፊት ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣው ተከላካዩ ክሪስ ሪቻርድስም ከወጣቶቹ ተጨዋቾች አንዱ ሲኾን፤ 20 ዓመቱ ነው። የኔዘርላንዱ አጥቂ ዮሹዋ ሲርክዚ 19 ዓመቱ ቢኾንም በ9 ጨዋታዎች 4 ግብ ማስቆጠር የቻለ ግብ አዳኝ ነው።

Deutschland Fußball Bundesliga FC Bayern München - Schalke 04
ምስል Matthias Schrader/P Photo/picture alliance

የ19 ዓመቱ ሠርጂዮ ዴስትንም ባየር ሙይንሽን ከአያክስ ለማስመጣት ከፍተኛ ፍላጎት ዐሳይቷል። ባርሴሎናም የራሱ ሊያደርገው የሚፈልገው ይኸን ወጣት አያክስ አምስተርዳም 20 ሚሊዮን ዩሮ ጠይቆበታል። ሠርጂዮ ለባየርን ሙይንሽን ከፈረመ የቀኝ ተከላካይ መስመሩን ሌላ ታዳጊ ይይዘዋል ማለት ነው።

ባየርን ሙይንሽን በቀጣይ በሚያደርጋቸው ወሳኝ ግጥሚያዎች እነዚህ ታዳጊዎች ተጨማሪ ዕድል አግኝተው ብቃታቸውን ሲያስመሰክሩ መመልከት የበርካቶች ምኞት ነው። ባየር ሙይንሽን የፊታችን ሐሙስ ከሴቪያ ጋር ለአውሮጳ ሱፐር ካፕ ዋንጫ ይፋለማል። የሩቡዕ ሳምንት ደግሞ በጀርመን ሱፐርካፕ ዋንጫ ጨዋታ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ይጋጠማል።

በባየር ሙይንሽን የ8 ለ0 አሸማቃቂ ሽንፈት የደረሰበት ሻልከ ውጤቱ ያስከፋው አይመስልም። ባለፈው የጨዋታ ዘመን 16 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ለተሳናቸው የሻልከ አሰልጣኝ ዴቪድ ቫግነር ምንም እንኳን በሰፊ የግብ ልዩነት ቢሸነፉም፤ በጊዜ ከዓለም ምርጡ ቡድን ጋር መጋጠማቸውን ግን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደውታል። ከባየርን ጋር 15ኛው ዙር ላይ ከመጋጠም ውጤቱ ምንም ይኹን ምን በመክፈቻው መጫወቱ ያዋጣል ብለዋል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ

ከየትኛውም ስታዲየም በበለጠ ቅዳሜ እለት በቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ግጥሚያ በርካታ ታዳሚያን እንዲገቡ ተፈቅዶ ነበር። ሲግናል ኤዱና ፓርክ ስታዲየም ውስጥ 9300 ተመልካቾች ታድመው ጨዋታውን ተከታትለዋል።

Bundesliga - Borussia Dortmund vs. Borussia Moenchengladbach
ምስል Ina Fassbender/AFP

ቦሩስያ ዶርትሙንድም፦ ዘንድሮ እንደ ባየር ሙይንሽን በወጣቶች ለመደራጀት ሞክሯል። በቅዳሜው ግጥሚያ ዩሊያን ብራንድት እና ማርኮ ሮይስ ተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጠው ሬና እና ሳንቾ ተሰልፈው ነበር። የ17 ዓመቱ ጂዮቫኒ ሬና በ35ኛው ደቂቃ በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። እንግሊዛዊው ጁድ ቤሊንግሀምም 17 ዓመቱ ነው። ኖርዌጂያዊው አጥቂ ኧርሊን ሃላንድ እና ጄደን ሳንቾም ገና 20 ዓመታቸው ነው። በአጠቃላይ ቡንደስሊጋው እንደ ዘንድሮ ለታዳጊ ወጣቶች መልካም አጋጣሚ የኾነበት ጊዜ የለም። 

ላይፕሲሽ

ላይፕሲሽ ማይንትስን ትናንት 3 ለ1 አሽንፏል። ባየር ሌቨርኩሰን ከቮልፍስቡርግ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። በመጀመሪያ የቡንደስሊጋ ፍልሚያው አርሜኒያ ቢሌፌልድ አንድ እኩል በመውጣቱ እና ነጥብ በመያዙ ከወዲሁ ተስፋ ሰንቋል። ፍራይቡርግ ሽቱትጋርትን 3 ለ2፤ ሔርታ ቤርሊን ቬርደር ብሬመንን 4 ለ1 ፤ ሆፈንሃይም ኮሎንን 3 ለ2 እንዲሁም አውግስቡርግ ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ1 አሸንፈዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ትናንት ሊቨርፑል አንድ ተጨዋቹ በቀይ የተሰናበተበት ቸልሲን 2 ለ0 አሸንፏል። ዛሬ ማታ ማንቸስተር ሲቲ ከዎልቨርሀምፕተን ዎንደረርስ እንዲሁም አስቶን ቪላ ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር ይጋጠማሉ። ትናንት ላይስተር ሲቲ በርንሌይን 4 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ኒውካስል ዩናይትድ በብራይቶን 3 ለ 0 ተበራይቷል። ቶትንሀም ሳውዝሀምፕተንን 5 ለ2 አሰናብቷል። ቅዳሜ ዕለት፦አርሰናል ዌስትሀም ዩናይትድን 2 ለ1፤ ሊድስ ዩናይትድ ፉልሃምን 4 ለ3 አሸንፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ በክሪስታል ፓላስ 3 ለ1 ሲሸነፍ፤ ኤቨርተን ዌስትብሮሚች አልቢዮን 5 ለ2 ድል አድርጓል። በሳምንቱ መጨረሻ አጠቃላይ ስምንት ግጥሚያዎች 39 ኳሶች ከመረብ ማረፍ ችለዋል።

Mohamed Salah I Liverpool
ምስል picture-alliance/AP/S. Botterill

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ መስከረም 11 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ባካሄዱት ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤቶች (CECAFA) ውድድር እንዲሳተፉ ወስነዋል። በዘንድሮ የሴካፋ ውድድር ዕድሜያቸው ከ20 እና 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች በማጣሪያ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ተወስኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር በዚህ ዓመት እንዲሳተፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ወስኗል፡፡የሥራ አስፈፃሚኮሚቴው ሌሎች ተጨማሪ ውሳኔዎችንም አስተላልፈዋል።

ብስክሌት

ምስል Kenzo Tribouillard/AFP

በቱር ደ ፍራንስ ውድድር ታሪክ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዕድሜ አነስተኛው ወጣት ትናንት አሸናፊ ኾኗል።  ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ የቱር ደ ፍራንስ ውድድሩን በ87 ሰአት ከ20 ደቂቃ ከአምስት ሰከንድ ያሸነፈው ታድዬ ፖጋካር ሃያ ኹለት ዓመቱን የደፈነው በዛሬው ዕለት ነው። የባለፈው ዓመት ዙር አሸናፊ የነበረው ኤጋን ቤርናል ውድድሩን ያሸነፈው በ22 ዓመቱ ነበር።  ቱር ደ ፍራንስ ውድድርን የስሎቫኒያ ዜጋ ሲያሸንፍም ታድዬ ፖጋካር የመጀመሪያው ነው።

ለ23 ቀናት በፈጀው የ21 ዙር ሽቅድምድም አሸናፊ የኾነው ስሎቬኒያዊ ወጣት በሽልማት ያገኘውን ግማሽ ሚሊዮን ዩሮ ወደ ሀገሩ ያቀናል። የዛሬ 117 ዓመት በ19 ዓመቱ ለድል የበቃው ሔንሪ ኮርኔ እስካሁንም ድረስ በዕድሜ ትንሹ አሸናፊነቱን እንደያዘ ነው። በዘንድሮ የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ሌላኛው የስሎቬኒያ ዜጋ ፕሪሞዥ ሮግሊች የኹለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ የአውስትራሊያው ብስክሌተኛ ሪቺ ፖርቴ በሦስተኛነት አጠናቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ