1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሬቻ ከፖለቲካ እንዲርቅ ማሳሳቢያዎች ሲሰጡ ሰንብቷል

ዓርብ፣ መስከረም 19 2010

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ሰሞንኛ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ የያዙት ሁለቱ ከዓመታዊ በዓላት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አንደኛው ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ቦታዎች ሲከበር የቆየው መስቀል ሲሆን ሌላኛው በመጪው እሁድ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ የሚከበረው ኢሬቻ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2kyXj
Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

ኢሬቻ ከፖለቲካ እንዲርቅ ማሳሳቢያዎች ሲሰጡ ሰንብቷል

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለበዓላት እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ የበዓል ዝግጅቶችም እየሰፉ የመጡ ይመስላል፡፡ በዓላትን የሚያሰናዱ አካባቢዎች ዘንድ ያለው ፉክክርም እየተጋጋለ፣ ለከርሞውስ ምን አዲስ ነገር ይዤ ልምጣ እያስባለ ነው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች በቀላሉ በእጃቸው ያለውን ዘመናዊ ተንቃሳቃሽ ስልክ ተጠቅመው የሚያሰራጯቸው መረጃዎች፣ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች በዝግጅቶቹ ያልተገኘን ሰው እንኳ በቦታው እንደነበር እንዲሰማ እያደረገ ነው፡፡ ማክሰኞ መስከረም 16 በተከበረው የመስቀል ደመራ የሆነውም ይኼው ነው፡፡ 

Meskel Festival
ምስል DW/A. Hahn

የበዓል ተሳታፊዎች ከየቦታው የሚያጋሯቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ፌስ ቡክ እና ትዊተርን አጥልቅልቀውት ነው የዋሉት፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ እዚህም እዚያም በበዓሉ ላይ ይታዩ የነበሩ ባንዲራዎች ጉዳይ ከውዝግብ ርቆ የማያውቀውን የኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምህዳር ወደ ሌላ ዙር ክርክር ከትቷል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ደሴ እና ጎንደር እንደዚሁም በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች በበዓሉ አክባሪዎች ተይዘው የታዩት የኢትዮጵያ ባንዲራዎች ምንም ዓይነት አርማ የሌላቸው ልሙጥ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ መሆናቸው አነጋግሯል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የታየው የሞአ አንበሳ ምልክት ያለበት ባንዲራም እንዲሁ አከራክሯል፡፡ 

“አንዳንድ ማህበረሰቦች እና ተቋማት የፌደሬሽኑን ባንዲራ ለመያዝ እንቢተኛነት ማሳየታቸውን” በፌስ ቡክ ገጻቸው የጠቀሱት ሊባን ጃልዴቻ የዚህን አንደምታ እንዲህ አመላክተዋል፡፡ “በኢትዮጵያውያን መካከል የትኛውን ባንዲራ ለፌደራል መንግስት እንጠቀም በሚለው ላይ የሀሳብ ስምምነት የለም፡፡ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመስቀል በዓል ወቅት ባለቀስተደመናው የደርግ ዘመን ባንዲራ በአሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ይህ በእርግጠኝነት የሚያሳየው ህወሓት በስልጣን ላይ ያለው እንደው ለስም ብቻ መሆኑን ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

አርማ የሌለው ልሙጥ ባንዲራ በመስቀል በዓል ላይ “በአደባባይ ተጀንኖ መውለብለቡን” የተቃወመው አቡበከር አለሙ ሙሄ በበኩሉ “ይህ ባንዲራ ለእኔ ጨለንቆን እንዳስታውስ የሚያደርገኝ የአፄ ምኒልክ ባንዲራ ነው፡፡ ደግሞሞ ይህንን ባንዲራ ከቀድሞው የአንኮበሪዝም ርዝራዦች በስተቀር፣ የእኔ ነው ብሎ የሚቀበለው የኢትዮጵያ ብሔረሰብና ህዝብ አለ ብዬ አላምንም” ብሏል በፌስ ቡክ፡፡ 

የእዚህ ተቃራኒ ሀሳብ በዚያው ማህበራዊ ገጽ ተንጸባርቋል፡፡ ኢዮብ ብርሃነ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “ደመራ በጎንደር እና በደሴ በእውነተኛዋ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆ ተከበረ” ብለዋል፡፡ ውብሸት ታደለ ደግሞ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የጸደቀውን ባንዲራ ለምን እንደማይወዱት ምክንያታቸውን በፌስ ቡክ ገጻቸው አስረድተዋል፡፡ “እኔ በባንዲራችን የሚመጣ ሁሉ አይመቸኝም። ለምን ካልከኝ የልጅነቴን ኢትዮጵያን ይዤ መቀጠል ነው የምፈልገው። በየጊዜው የሚሻሻል ባንዲራ እንዲኖረኝ አልሻም። በኮከብ ምናምን የተዥጎረጎረውን ባንዲራ ልዋደቅለት ቀርቶ እንደጠላት አገር ባንዲራ ያበሽቀኛል። አልወደውም። የማልወደውን ባንዲራ እያውለበለበ ስለአገር ፍቅር የሚሰብከኝ ኢህአዴግ የተረገመ ይሁን! አሜን!” ብለዋል፡፡ 

Meskel Festival
ምስል DW/A. Hahn

ዘጸአት ሴቭአድና አናንያም ከውብሸት ጋር በከፊል ይስማማሉ፡፡ ሆኖም በአማራ ክልል በተደጋጋሚ አስተዋልኩት የሚሉትን የባንዲራ አጠቃቀም ግድፈት በፌስ ቡክ ገጻቸው ይተቻሉ፡፡ “በበኩሌ መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር አርማዎቻችን መለዋወጥ አለባቸው ብየ አላምንም፡፡ እንደውም አርማ አስፈላጊ ነው ብየ አላምንም (ባንዲራችን ልሙጥ ቢሆን እመርጣለሁ)፡፡ ሆኖም ግን ይህ በመግባባት፣ በስምምነት ሊሆን የሚገባው እንጂ የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸው አካሎች፣ ቡድኖች፣ ወዘተ የየራሳቸውን ባንዲራ ይዘው ሊወጡ አይገባም። በሀገር ደረጃ የተፈቀደውና የሀገሪቱ ፌደራላዊ ስርዓት መገለጫ እንዲሆን የተባለን ባንዲራ መገልበጥ ምን ማለት እንደሆነ ግን ለማናችንም ግልፅ ይመስለኛል። ሲጠቃለል አማራ ክልል ላይ የሚታየው ከፌደራል ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት የመሸሽ ዝንባሌ በጊዜ ካልተገታ አደጋው የበዛ ነው ባይ ነኝ፡፡ እንደውም የእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች መደጋገም የሀገሪቷን አንድነትና ሕልውና ከጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ ሀገሪቷን ወደ ዘመነ-መሳፍንት ዓይነቱ ሁኔታ የሚመልስ ነው ባይ ነኝ። እያስተዋልን” ሲሉ አስተያየታቸውን በምክር ቋጭተዋል።

ተስፋ ኪሮስ ሳህለ በበኩላቸው ተከታዩን አስተያየት በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ “በእኛ ዘመን ቤተክህነት በሃይማኖታዊ በዓላትና ስርአቶች ሰንደቅ ዓላማ የምትጠቀመው ለሃገሪቱ ምልክቶች ክብር ለመስጠት እንጂ የእምነቷ አንድ አካል አድርጋ አይደለም። ደግሞ ቤተ እምነት እና ቤተ መንግስት ተለያይተዋል። ነገር ግን የአሁኗን ኢትዮጵያ በሚያንፀባርቅ መልኩ ሰንደቅ ዓላማችን ላይ የተደረገው ለውጥ የማይቀበሉ የፖለቲካ ሃይሎች ቤተክህነትን መሸሸጊያቸው በማድረግ በቤተእምነትና በቤተ መንግስት መካከል የተፈጠረውን ድንበር አፍርሰው ሊቀላቅሉት ይጥራሉ። በዚህ መሰረት ዓለማዊውን ሰንደቅ ዓላማ ሃይማኖታዊ ትርጉም እየሰጡ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ውጪ ያሉ የሌላ እምነትና ሃይማኖትተከታዮችን እንዳይወክል ይጥራሉ። ይህ አካሄድ የሌላ እምነትና ሃይማኖት ተከታዮች ሰንደቅ ኣላማው አይወክለንም እንዲሉና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚወክል ሌላ ሰንደቅ ዓላማ ይዘጋጅ ወደሚል ሊያመሩ ስለሚችሉ በሰንደቅ ዓላማችን ቀጣይነት ላይ ጋሬጣ እየጣሉበት ይገኛል” ብለዋል ዘለግ ባለው ጽሁፋቸው። 

ታደገ ምህረቱ አይነው ለእንደዚህ ዓይነት አስተያቶች የተሰጠ የሚመስል ምላሽ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስነብበዋል፡፡ “አቅም እና አቋም ቢጠፋ ነው እንጂ የቤተክርስቲያናችን እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ልዩነት እንዳለው ለ'ኢህአዴግ ጀሌዎች' የሚያስረዳ እና የሚያስማማ ጠፍቶ ነው ይህ ሁሉ ቀውስ? ቤተክርስቲያን ራሷ ትርጉም የምትሰጠውን የራሷን ባንዲራ በቤቷ እና በልዩ ልዩ ጉባኤዎቿ ላይ የመጠቀም ነጻ መብቷ ሊነካ አይገባም። የቤተክርስቲያኒትን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ምልክት እንደመጠቀም፤ የመንግስትንም ባንዲራ እንደመቃወም የሚቆጥሩ ሞኞች እና ግልፍተኞች ብዙ ናቸው። ቤተክርስቲያኒቱ አገሪቱን በምትወክልበት ጊዜ የኢትዮጵያን ባንዲራ ልትጠቀም ትችላለች። የኢትዮጵያ ባንዲራ በየዘመኑ እንደዘወራት የመንግስት ሥርዓት ፍላጎት በቤተክርስቲያኒት ሰንደቅ ዓላማ ላይ ጥገኛ ሆኖ ሲቀያየር ኖሯል” ሲሉ ተከራክረዋል። 

በባንዲራ አጠቃቀም ላይ የተካሄደውን ሙግት በተቃዋሚ ፖለቲከኛው አስራት አብርሃም አስተያየት እናጠቃልል፡፡ “ሰው የፈለገውን ባንዲራ የማውለብለብ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ምንድነዉ በሆነ ባልሆነ መጨቃጨቅ?! ስርዓቱ ሳይወድቅ እንዲህ የሆነ ስርዓቱ የወደቀ ዕለት ባለምልክቱ ባንዲራ አንድም ሰው የሚያውለበልበው የሚኖር አይመስልም። ያን ዕለት ነው ማየት!” 

Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

ወደ ሌላው በዓል ተኮር ርዕሰ ጉዳያችን ተሻግረናል፡፡ በአዲስ አበባ አቅራቢያ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሀይቅ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ከዓመት ዓመት እየደመቀ፣ የተሳታፊዎችም ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በኦሮሞ ተወላጆች ባህል እና ወግ መሰረት “ፈጣሪን የማመስገኚያ ቀን” የሆነው ኢሬቻ ባለፈው ዓመት አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ እና የብዙዎችን ልብ የሰበረ አደጋ አስተናግዷል፡፡ የተቃውሞ ድምጾችን ለመበተን የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰድ ሲጀምሩ በተፈጠረ ግርግር እና መገፋፋት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር እስካሁንም እንዳወዛገበ አለ፡፡ 

በመጪው እሁድ የሚከበረው የ2010 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል እንዳምናው እንዳይሆን የተለያዩ ወገኖች ማስጠንቀቅ የጀመሩት ከበዓሉ መዳረሻ አስቀድሞ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው ሰፋ ያለ ዘገባው የኢትዮጵያ መንግስት እና የጸጥታ ኃላፊዎች ተመሳሳይ አደጋ ለማስቀረት ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ብሎ ነበር፡፡ ድርጅቱ ከጠቆማቸው እርምጃዎች ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥርን መቀንስ እና ከኃይል እርምጃ መታቀብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከቀናት በፊት እንዳስታወቀው በበዓሉ ላይ የጦር መሳሪያ የታጠቁ  የጸጥታ ኃይሎች አይገኙም፡፡ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ላይም የገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይውለበለብ ውሳኔ መተላለፉን የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ገልጿል፡፡   

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ንቁ ተሳታፊ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች እና አራማጆች (አክቲቪስቶችም) የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ኡቱባ ጋዲሳ  በፌስ ቡክ ገጻቸው “አክሱም ሃውልት የሰላም አየር እየተነፈሰ ኢሬቻ የሚሸበርበት ምክንያት የለም! ኦሮሞ እራሱን ማስከበር አለበት። ኢሬቻ የኦሮሞ የማንነት ቅርስ ነው። የኦሮሞ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ እሴቶች መዋቅር ነው። ኢሬቻ ከክብረ በዓልነት አልፎ እንደነ አክሱም የሰላም ቀጠና እንዲሆን ኦሮሞ በቆራጥነት መስራት አለበት” ብለዋል፡፡   

ደረጃ ገረፋ ቱሉ በበኩላቸው “ሁሉም ወገን ኢሬቻ በሰላም እንዲጠናቀቅ ግልፅ መልዕክት ማስተላለፍ አለበት። የኢሬቻ በሰላም መጠናቀቅ የመላው ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ሲሆን ይህንንም የአባገዳ ምክር ቤት ተቀብሎ አፅድቆታል። ስለዚህ ኢሬቻ በሰላም ይለቅ ብሎ ማስተጋባት የመላውን ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ማስተጋባት ነው። ይህንን ማድረግ የማይፈልግ ወገን እየተሸረበ ላለው ሴራ እና እልቂት ተባባሪ ለመሆን ተዘጋጅቷል ማለት ነው” ሲሉ አስጠንቀዋል፡፡ 

አብዲ ለሜሳ ሐሙስ ረፋዱን በፌስ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት “እሁድ በሚደረገው የኢሬቻ ፌስቲቫል ከዋዜማው ጀምሮ በሚካሄዱ ስነ ስርዓቶች ኦህዴድ እንደ ድርጅት በባለስልጣናቱና በአርማ ምልክቶቹ ጣልቃ ገብቶ ከማደፍረስ ራሱን መቆጠብ አለበት። ቢቻል ቢሾፍቱ ላይ የተከሉትን የስድብ ድንጋይንም ከበዓሉ በፊት መላ ቢሉት ጥሩ ነው” ብሎ ነበር፡፡ ትላንት ከሰዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ያጋሩት ፎቶ የአብዲን ጥያቄ በከፊል የመለሰ ሆኗል፡፡ ምስል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባለፈው ዓመት በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት የሞቱ ሰዎችን ለማስታወስ በቢሾፍቱ ያሰራውን ሀውልት ያሳያል፡፡ ከወር በፊት በተመረቀው በዚህ ሀውልት ላይ በበዓሉ ላይ የሞቱት ሰዎች በድንገተኛ ሞት ህይወታቸውን እንዳጡ መጻፉ ተተችቶ ነበር፡፡ አቶ አዲሱ ያጋሩት ፎቶ ግን በሀውልቱ ላይ ሰፍሮ የነበረው እና ቁጣ የቀሰቀሰው “ድንገተኛ” የሚል ቃል መታረሙን አሳይቷል፡፡ 

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

በኢሬቻ ላይ ተቃውሞ ያስነሳል ተብሎ ተፈርቶ የነበረው የሀውልቱ ጉዳይ እንዲህ ማስተካከያ ቢደረግበትም የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበዓሉ ላይ ይገኙ፣ አይገኙ የሚለው ግን ማወዛገቡን ቀጥሏል፡፡ ጸጋዬ አራርሳ በጉዳዩ ላይ ተከታዩን አስተያየት በፌስ ቡክ ገጹ ለንባብ አብቅቷል፡፡ “ጥያቄው በበዓሉ ለይ እነማን ይገኙ፥እነማን አይገኙ አይደለም። የሕዝብ፣ የባሕል በዓል እንደው ማንም ፈቃጅ፣ ማንም ከልካይ የሚሆንበት አይደለም። እኔም እከሌ አይገኝ፣ እከሌ ይገኝ አላልኩም። እንደግለሰብ ማንም ሰው መገኘት ይችላል። አቶ ለማ መገርሳም ሆነ ሌሎች የኦህዴድ አባላት። ኦህዴድ እንደ ድርጅት፣ አቶ ለማ እንደክልሉ ፕሬዝዳንት ግን በቦታው ተገኝተው በዝግጅቱ ለመሳተፍ፥ ወይም ንግግር ለማድረግ መሞከር ግን ተገቢም አስፈላጊም አይደለም ነው ያልኩት። ይህን ለማድረግ የሥነ-ምግባርም፣ የሕግም፣ የፖለቲካም ብቃት (እና ተቀባይነት) ይጎድላቸዋልና። ቤተ-እምነት እና ቤተ-መንግሥት፥ ሃይማኖትና ፖለቲካ ሊኖራቸው ስለሚገባው ልዩነት እና ርቀት የሚደነግግው ሕገ-መንግሥታዊ መርህም ሊዘነጋ አይገባም። ስለዚህ መሪዎቹ አስፈላጊውን ርቀት ከበዓሉ ቢጠብቁና በዓሉን ለሕዝቡ፣ ለአባ ገዳዎቹ፣ ለባሕል ባላደራዎችና ለእምነቱ አባቶች ቢተዉ ትክክል ይመስለኛል። ለራሳቸው ሲሉ!” ብሏል ጸጋዬ።

ብሩክ ሚኬል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በኢሬቻ ላይ ንግግር የማድረግን ሀሳብ አጥብቀው ከሚቃወሙት ወገን ነው። “ኢሬቻ ላይ የመንግስት ባለስልጣንና የማንም ፖርቲ ባንዲራ እንደማይኖር ከአባገዳዎች ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል። አከተመ። ‘ድንገት ሞቱ’ የሚል ሀውልት ደረቱን ነፍቶ የመረቀን ሰው ኢሬቻ ላይ ከፍ ለማድረግ ከከጀለህ ካድሬ ነህ። ለማ መገርሳን ማሻሻል ከፈለጋችሁ ሲያጠፋ ቅጡት፤ ስህተቱን አታድበስብሱ” ሲሉ ሀሳባቸውን በፌስ ቡክ ገጻቸው አካፍለዋል፡፡  


ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ