1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስቀል በዓል አከባበር እና ወቅታዊ የጸጥታ ተግዳሮት በኦሮሚያ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አንድምታው ባሻገር በባህላዊ እሴቱ በጉጉትና በደማቅ ሥነስርዓት ከሚከበርባቸው አከባቢዎች የኦሮሚያ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የበዓል ድባብ ግን ዘንድሮ በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የቤተሰቦችን መገናኘት በመገደቡ የተለመደውን የበዓሉን አከባበር አደብዝዞታል ይላሉ አስተያየት ስጪዎች።

https://p.dw.com/p/4l9oe
Äthiopien Religion l Feierlichkeiten zum Meskel-Fest
ምስል Amanuel Sileshi/AFP via Getty Images

የመስቀል በዓል አከባበር እና ወቅታዊ የጸጥታ ተግዳሮት በኦሮሚያ

መስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አንድምታው ባሻገር በባህላዊ እሴቱ በጉጉትና ደማቅ ስነስርዓት ከሚከበርባቸው አከባቢዎች የኦሮሚያ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡በክልሉ የበዓላት ሁሉ አለቃ ተብሎ የሚከበረው መስቀል ከወርሃ ክረምት ወደ ጸደይ ወቅት የመሸጋገሪያ የመስከረም ወር ትልቅ ምሳሌ ተደርጎ የሚታይም ነው ይባላል።ይህ በጉልህ የሚከበረውን የበዓል ድባብ ግን በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ሁኔታ የቤተሰቦችን መገናኘት በመገደቡ የተለመደውን የበዓሉን አከባበር  አደብዝዞታል ነው የሚባለው፡፡

የመስቀል በዓል ጥንታዊ አከባበር

አቶ ድሪቢ ደምሴ የአንጋፋው መጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ፕሬዝዳንት እና በኦሮሞ ህዝብ ባህል፣ ሃማኖትና ገዳ ስርዓት ላይ ወደ አምስት መጽሃፍትን የጻፉ የባህል አጥኚ ናቸው፡፡ የ73 ዓመት እድሜ ባለጸጋው አቶ ድሪቢ የበስቀል በዓል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እንደ ዘመን መለወጫም የሚታይ ነው ይላሉ፡፡ “መስቀል በአጭሩ የዘመን መለወቻ ማለት ነው፡፡ አከባበሩም በዋናነት ከመስከረም 15 እስከ 17 ቀደማ ይሁን እንጂ ከነሃሴ አጋማሽ ጀምሮ ለመስቀል መዳረሻ የሚደረጉ ብዙ ባህላዊ ክዋኔዎች አሉ፡፡ እናቶች አቴቴ አላቸው፡፡ ወጣቶች ሽኖዬና ጎቤ እያሉ በመዳረሻው ከክረምት ውጥተህ ብርሃን ያሳየህን ለማለት ደመራ የማብራት ስርዓት ይከናወናል” ብለዋል፡፡ በዚህም የጥጋብ በኣል የሚባልለት መስቀል እንኳ ሰው ከብቱም ሳይጠግብ የማይውልበት ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የመስቀል በዓል እንደ ዘመን መለወጫ ነው።
በገዳ ስርዓት ላይ ወደ አምስት መጽሃፍትን የጻፉት የባህል አጥኚ አቶ ድሪቢ የበስቀል እንደሚሉት የመስቀል በዓል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እንደ ዘመን መለወጫም የሚታይ ነው ፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

የአብሮነትን በዓል መስቀልን ያደበዘዘው የጸጥታ ተግዳሮት

ታዲያ በክልሉ በርካታ አከባቢዎች በተለይም በአራቱም የሸዋ ዞኖች እና በወለጋ ዞኖች የበዓላት ሁሉ አለቃ እየተባለ ጎልቶ የሚከበረውን ይህን አውደ ዓመት ለማክበር ከሩቅ የሚኖር ልጅ እንዲሁም የቅርብ ዘመድ አዝማዱ ወደቤተሰቦቹ እየሄዱ አብሮ ማክበር የተለመደ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በክልሉ የሚስተዋለው የጸጽታ ይዞታ ለዚህ አመቺ የሆነ አይመስልም፡፡ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ካሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር መስቀልን አብሮ ማሳለፍ ሁለቴ እንኳ የማይታሰብበት የወትሮ ተግባራችን ነበር የሚሉት አንድ የአከባቢው ተወላጅ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአከባቢው የተስፋፋው ግጭት አለመረጋጋት ከዚህ የአውዳመት የዘወትር ተግባራቸው እንደገታቸው ያስረዳሉ፡፡

“እውነት ለመናገር ከመስከረም ጀምሮ ወደ ገጠር እንመላለስ ነበር፡፡ በዚያም ከወለዱን አሳድገው ካስተማሩን ወላጆቻችን ጋር እንደ መስቀል ያሉትን ክብረ በዓላት አብረን እናሳልፋለን፡፡ ይህን የሚምር ወቅት አሁን ላይ መሄድ ባለመቻሉ እዚሁ አዲስ አበባ ባለንበት እያሳለፍን ነው፡፡ በዓሉ አይደለም በከተማ የምንኖር እዛ ህደን ማክበር በዚያም ላሉ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዓል በዓል የሚመስለው በዚያ ሁሉም

 ከቤተሰብ ጋር በማክበር ሁሌም የበኣሉን መምጣት የሚናፍቁቱ ቢሆንም ዘንድሮ በፀጥታ ችግር ከቤተሰብ ጋር ማክበር አልተቻለም
አንድ አስተያየት ሰጪ በኦሮሚያ ክልል መስቀልን ከቤተሰብ ጋር በማክበር ሁሌም የበኣሉን መምጣት የሚናፍቁቱ ቢሆንም ዘንድሮ በፀጥታ ችግር ከቤተሰብ ጋር ማክበር አልተቻለም ብለዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በተሰበሰበበት ነው፡፡ እኛ አለመሄዳችን ብያሳዝነንም ይበልጡንም ደግሞ በዚያ ያሉት ሁኔታቸው ያሳዝናል፡፡ የጸጽታ ይዞታው ቅር የሚያሰኝ ነው” ብለዋል፡፡
ወትሮም ምስራቅ ወለጋስሬ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር እየሄዱ መስቀልን የሚያከብሩ አስተያየት ሰጪም በቅርቡ ይህን ማድረግ ቀርቷል ይላሉ፡፡ “አሁን በዓሉ ምኑ ይከበራል ብለህ ነው፡፡ ከቤተሰብ መሄድ ካቆምን ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ ከበዓል ሁሉ የሚደምቅ ነበር መስቀል” ብለዋል፡፡

የወደፊት  ተስፋ…

መስቀልን ከቤተሰብ ጋር በማክበር ሁሌም የበኣሉን መምጣት የሚናፍቁቱ አሁንም አንድ ቀን በዚያ በለመዱት መንገድ ለማክበር የሚያስችላቸው የእርቅ፤ የሰላምና የአንድነት ቀን እንዲመጣ ጉጉት-ምኞታቸውን ያስረዳሉ፡፡ “ተፋላሚዎች የህዝባችንን ችግር ተረድተው ኑሮያቸው እየታመሰ ነው ብለው ቆም ብለው ካሰቡ ያ የምንናፍቀው ቀን ነገ ጠዋት ሊሆን ይችላል” የሚሉት አሰድተያየት ሰጪው፤ ተስፋው የማይታቸው የነበረው ግጭት አሁንም ከቀጠለ ብቻ ነው፡፡ እናም አሉ “ተፋላሚዎች የእርቅ መንገድን መከተል ያለባቸው ስለህዝባቸው ሲባል ሊሆን ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ያም ሆነ ይህ ከቤተሰብ ጋር ደምቆ የሚከበረውን የመስቀል በኣል ከቤተሰብ መቅረት የሚያሳዝንና የሚቆጭ ብለውታል፡፡ ገልጸዋል።

ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ፀሐይ ጫኔ