ፍትህ ለሔቨን አወት ፣ የሰገን ጥቃት እና የህወሓት አመራሮች ውዝግብ
ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2016የቆንጅዬዋ ሔቨን አወት ፎቶግራፎች በሣምንቱ ፌስቡክ እና ኤክስን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወሩ ለሞት ያበቃትን አሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት የሚያስታውሱ ነበሩ። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች “ፍትህ ለሔቨን” እያሉ ነው።
የ7 ዓመቷ ታዳጊ ቦርቃ ሳትዘግብ በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ጌትነት ባዬ በተባለ ግለሰብ ተገዳ ከተደፈረች በኋላ ከተገደለች አንድ አመት አልፏል። አሰቃቂው የሔቨን ታሪክ ተመልሶ መነጋገሪያ የሆነው የ25 ዓመት እስራት የተፈረደበት ወንጀለኛ ይግባኝ ማቅረቡ ከተሰማ በኋላ ነው። በርካቶች ወንጀለኛው ሞት አሊያም ዕድሜ ልክ ሊፈረድበት ይገባ ነበር እያሉ ይሞግታሉ።
ቅድስት የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “የሰባት ዓመት ልጅ አስገድዶ የሚደፍር ትውልድ እንዴት ኢትዮጵያ አፈራሽ?” ሲሉ ጠይቀው መልስ ባያገኙም “ሔቨን ነፍሷ በሰላም እንድታርፍ ስለ ፍትህ እንጩህ” ብለዋል። “ተገዳ የተደፈረችባቸው ደቂቃዎች ምን ያህል አስቀያሚ እንደሆኑ መገመት አልችልም። ስትገደል ያለፈችበትን ሰቆቃ አላውቀውም” የሚሉት ፊያሜታ አዙር “ቢያንስ ፍትህ እንድታገኝ እጠይቃለሁ” የሚል አስተያየት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ አስፍረዋል። ሰላማዊት ጋሻው “ፍትህ ሰብዓዊ የመኖር መብታቸዉን ለተነፈጉ፣ ለተገፈፉ ሴቶች፣ ወንዶች ፣ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎች፣ አረጋዉያን፣ ፍትህ ለግፉዓአን” ሲሉ ይወተውታሉ።
ሐብታሙ አምጣቸው “ብዙ እኅቶቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደፈሩ፤ ብዙ እናቶቻችን ጾታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው፤ ያኔ እንዳላየን እንዳልሰማን ሆነን አለፍን። ከዚያም አልፈን ራሳቸውን አጠንክረው፣ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ብቅ ብለው በደላቸውን 'ዓለም ይወቅልን' ሲሉ የተማጸኑ እኅቶቻችንን ተሳለቅንባቸው፤ በቁስላቸው ላይ እንጨት ጨመርንባቸው። ተቋማትም ስላቅ በሚመስል መልኩ ፍትኅ ነፈጓቸው” ሲሉ ጉዳዩ ሥር የሰደደ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
“የዛሬዋ ተበዳይ እኅታችንም የዚያ ሁሉ ግፍ ድምር ውጤት ናት። በአካል ያልጠነከረች፣ በአዕምሮ ያልዳበረች፣ የእርሷን መውጣት መግባት በጉጉት የምትጠብቅ፣ ሮጣ ያልጠገበች እምቦቀቅላ ልጇን፣ የአብራኳን ክፋይ፣ በመከራው ስጥ ሆና ያሳደገቻትን የዓይኗን አበባ ለሰሙት እንኳን በሚዘገንን አረመኔያዊ ሁኔታ በጭካኔ ደፍሮ ያም አልበቃው ብሎ ከገደለ በኋላ........ በሀዘን የተቆራመደች ምስኪን እኅታችንን በዚህ ልክ ማሳደድ 'የእንገልሻለን' ማስፈራሪያ ማብዛት ምን ሊባል ይችላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “በቀንም በሌሊትም የደም እንባ እያጎረፈች ትኖር ዘንድ ለምን ተፈረደባት? የ 'ፍትኅ' ተቋማትስ በዚህ ደረጃ እንዴት በቁም በሰበሱ?” የሐብታሙ ጥያቄዎች ናቸው።
የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር “በሕፃን ሔቨን ላይ በተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል በእጅጉ” ማዘኑን ገልጿል። ይሁንና “ቅጣት አንሷል” እንዲሁም “ተከሳሹ ይግባኝ ሊጠይቅበት አይገባም” በሚል እየተካሔደ የሚገኘው ዘመቻ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አለው። ዘመቻው “ዳኞች ህግ እና ማስረጃን ብቻ መሰረት አድርገዉ በነፃነት እንዳይሰሩ ያልተገባ ጫና” እንደሚፈጥር ሥጋቱን ገልጿል።
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ግሎባል ስተዲስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሱራፌል ወንድሙ “እየተጠየቀ ያለው መሰረተ ቢስ የደቦ ፍርድ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው። “የሔቨን እናት፣ አያሌ ተደፋሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው እየጠየቁ ያሉት፤ ህዝቡም እያስተጋባ የሚገኘው፤ ህጉ ሆን ተብሎ በማን አለብኝነት እና በሙስና ተጥሷልና ይስተካከል የሚል ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
“የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ከአንጀት ወስዶ ለመፍትሔዎች መስራት ለተንሰራፋው የመድፈር እና የማቁሰል እንዲሁም የመግደል ወንጀል፤ መንግስትም ጭምር የሚሳተፍባቸውን እና ሴቶችና ህፃናት የሚጠቁባቸውን ጦርነቶች ጨምሮ፤ ሥርዓታዊ መልስ የመስጠት አንድ እርምጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል የሚልም ነው” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ሱራፌል ሊንክድኢን ላይ ባሰፈሩት ረዥም ሐተታ ይሞግታሉ።
በሰገን ያልተፈታ ውዝግብ ያስከተለው ሌላ ጥቃት
ባለፈው እሁድ በሰገን ከተማ የተፈጸመው ጥቃት እና የደረሰው የጉዳት መጠን ኢትዮጵያ ከገባችበት የግጭት አዙሪት የምትወጣበት ጊዜ እንዲህ ቅርብ እንዳልሆነ የሚያስታውስ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ መቀመጫ የሆነችው ከተማ የጥቃት ሰለባ የሆነችው ነሐሴ 12 ቀን 2016 ነበር። ጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ቅዳሜ ምሽት እንደተጀመረ የሚጠቁሙ መረጃዎችም አሉ።
ከፊታ ካሻላ በፌስቡክ ከከተማዋ ጭስ ሲትጎለጎል የሚያሳይ ፎቶግራፍ አያይዘው ባሰፈሩት መልዕክት ጥቃቱ ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት እንደተጀመረ ገልጸዋል። ሰገን “በታጣቂ ፅንፈኞች እየጋየች፤ እየወደመች ትገኛለች” ያሉት ከፊታ “የመንግስት አካላት ስለጉዳዩ ዝምታን መርጠዋል” ብለው ነበር። ከፊታ ጋዮላ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ከጥቃቱ ጀርባ “በጣም የሚያናድድ የፖለቲካ ቁማር” እንዳለ ጠቆም አድርገዋል።
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተዘዋወሩ ምስሎች ተገድለው በየቦታው የተጣሉ በርካታ አስከሬኖች አሳይተዋል። የሰገን ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በጥቃቱ 8 ፖሊሶች እና 5 ሲቪሎች በአጠቃላይ 13 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ በፌስቡክ ባሰራጨው መረጃ የወረዳው አስተዳደር፣ የግብርና፣ የፖሊስ፣ አካባቢያዊ ምክር ቤት እና የማዘጋጃ ቤት ሕንጻዎች፣ ጄኔሬተሮች በእሳት መጋየታቸውን፤ የሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁሶች እና 23 የመንግሥት ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን ይፋ አድርጓል። የተቃጠሉ እና የፈረሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሚያሳዩ ምስሎችም አያይዞ አቅርቧል።
ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ወገን ባይኖርም የኮንሶ ዞን “ጸረ-ሰላም ኃይልና የሽብር” ያለውን ቡድን ወንጅሏል። አማኑኤል ያቴኔ አይላቴ ጥቃት የፈጸመው ኃይል “ሸሸ ብሎ መተዉ ለሕዝብ ደሕንነት ዋስትና ማረጋገጫ ስለማይሆን” ከሪፖርት ያለፈ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ጽፈዋል። ካልማ ገለቦ ኮኖኖ የተባሉ የፖሊስ መኮንን በጥቃቱ መገደላቸውን የገለጹት አማኑኤል ያቴኔ “ጨቅላ ልጆቹ አባት እና አሳዳጊ አጥተዋል” ብለዋል። ኦራኖ አሌ “መንግሥት በፅንፈኛቹ እና ፅንፈኞችን በጉያቸው የሚሸሽጉ ተባባሪዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል።
የኮንሶ ዞን ከቀድሞው የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ወጥቶ የራሱን መንግሥታዊ መዋቅር ከመሠረተ በኋላ አካባቢው በተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት ውስጥ ወድቋል። ከኮንሶ፣ ከአማሮ፣ ከቡርጂ እና ከደራሼ አስራ ሰባት ቀበሌዎች በማውጣጣት የጉማይዴ ልዩ ዞን እንዲመሠረት የሚፈልጉ ኃይሎች ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተከስተዋል።
ከጉባኤው በኋላ የህወሓት አመራሮች ውዝግብ
አወዛጋቢው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሰባተኛ ቀኑ ባለፈው ሰኞ ሲጠናቀቅ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን በድርጅቱ ሊቀ-መንበርነት አቶ አማኑኤል አሰፋን በምክትል ሊቀ-መንበርነት መርጧል። ጉባኤው አወዛጋቢ የሆነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በርከት ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልተሳተፉበት በመሆኑ ነው።
ህወሓት በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ የምርጫውን ውጤት ይፋ ሲያደርግ ሐፍታሙ ደርቤ “ባዶ እና ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ጽፈዋል። ጸጊቱ ዮሐንስ “በጣም ጥሩ እና መልካም የሥራ ዘመን ይሁንላችሁ አንበሶቻችን” በማለት የመልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ ኃይለማርያም ተክለሚካኤል “ምን ተለወጠ?” ሲሉ ጠይቀዋል። አርአያ ሐፍቱ “ያው የተለመደው ህወሓት” ሲሉ ዮሴፍ ገብረእግዚዓብሔር ደብረፅዮን በሊቀ-መንበርነት መመረጣቸውን ጠቅሰው “ለውጡ የታለ? ቆይ ለምንድነው የምትቀልዱት? ለምን አዳዲስ አመራሮች፤ የተማሩ ወጣቶች ወደፊት አታመጡም?” በማለት ጠይቀዋል።
ምርጫውን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አማረ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “የትግራይ ህዝብ ከተቀበለው፤ ህብረተሰቡ በሰላም መኖር ከቻለ፤ የመምራት አቅም ያለው ማንም ይምራ ማን ዋናዉ አላማ ትግራይ የተረጋጋ ክልል ሆና ማየት ነው” የሚል አስተያየት አላቸው።
ጎይቶኦም ወልዋሎ የሁለቱ የህወሓት አመራሮች ልዩነት “ወዴትም አያመራም። ይታረቃሉ” ሲሉ ዶይቼ ቬለ በሰራው ዘገባ ሥር ጽፈዋል። በዩ አጋ “የፕሪቶሪያ ሥምምነት ለሠላም፣ ለሕዝብ ሲባል መከበር አለበት። ከግል ጥቅም ይልቅ ሕዝብ እና ሀገርን እናስቀድም” የሚል ውትወታ አቅርበዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በበርካቶች ዘንድ ሥጋት የፈጠረ ሆኖ ነበር። የጠቅላላ ጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ያልተሳተፉ የማዕከላዊ አባላትን ከፓርቲው አባሯል።
ጠቅላላ ጉባኤ ባካሔደው የህወሓት አንድ ክንፍ ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በኃላፊነት የተቀመጠውን የእነ አቶ ጌታቸው ረዳ አመራር ፓርቲያቸው የመተካት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ሥልጣን ከተካፈሉት የትግራይ ሠራዊት፣ ምሁራን፣ ከተቃዋሚው ባይቶና እንዲሁም ከፌድራል መንግሥት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከትግራይ ቴሌቭዥን ጋር በእንግሊዘኛ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ከጓዶቻቸው ጋር የተከሰተውን ልዩነት የነበረው እንዲቀጥል በሚሹ የፓርቲው አመራሮች እና በፓርቲው አሠራር የተወሰኑ ለውጦች ማድረግ በሚፈልጉ መካከል የተፈጠረ የሥልጣን ትንቅንቅ አድርገው አቅርበውታል። ቃለ-መጠይቁን ባጋሩበት የፌስቡክ ገጻቸው ሥር ደጋፊዎቻቸው እና ተቃዋሚዎቻቸው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አተያይ አንጸባርቀዋል።
ንጉሤ አብርሐ “ፈተናው የቱንም ያክል ሥር የሰደደ ቢሆን ከሕልውና ጥያቄያችን በላይ አይሆንም። ዴሞክራሲ፣ ተጠያቂነት፣ ዕኩልነት፣ ነጻነት፣ የመናገር ነጻነት እና የኃይል ሚዛን ማረጋገጥ እስካመጣ” ድረስ በአመራሮች መካከል የሚፈጠር ልዩነት ክፋት እንደሌለው ጠቁመዋል።
ኤልያስ ለምለም “ሰዎች በእርስዎ እና በአመራርዎ እምነት አጥተዋል። ህወሓት አዲስ አመራር መርጧል። እርስዎም በጨዋታው ተሸንፈዋል። ባቡሩ ጥሎዎት ሔዷል። አሁን ሥልጣንዎን በክብር ቢለቁ ይሻላል” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
አቶ ጌታቸውን “በተለይ እርስዎ እና ዶክተር ደብረፅዮን ፖለቲካዊ ሥልጣን የምትለቁት መቼ ነው?” ሲሉ የጠየቁት ብሩክ ዋይጂ ናቸው። ከመርፈዱ በፊት ሁለቱ ሹማምንት በፍጥነት ሥልጣን እንዲለቁ የጠየቁት ብሩክ “የትግራይ ሕዝብ እንደ አሁኑ ተከፋፍሎ አያውቅም። ለዚህ ጥልቅ ክፍፍል ዋና አስተዋፅዖ ያበረከታችሁ እናንተ ናችሁ” ሲሉ ይከሳሉ።
የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ የሚሻው ሕጋዊ ምዝገባ እና በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረ ልዩነት ከፌድራል መንግሥቱ ጋር ጭምር የሚያነካካው አሳሳቢጉዳይ ነው።
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር