1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንጀራና የላም ወተት የቀረባቸው የሎጊያ ነጋዴዎች

ዓርብ፣ ግንቦት 23 2016

በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው አፋር ክልል ውስጥ የሚሰሩ ወጣት ነጋዴዎች እንደገለፁልን « በጤና ምክንያት» በሚል ከአማራ ክልል ከዚህ ቀደም ይገባ የነበረ የተጋገረ እንጀራ እና የላም ወተት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባለመግባቱ የወጣቶቹ ንግድ ተስተጓጉሏል።

https://p.dw.com/p/4gSLc
እንጀራ በትሪ
ምስል Lena Ganssmann

እንጀራና የላም ወተት የቀረባቸው የሎጊያ ነጋዴዎች

በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ ነዋሪ የሆነው አህመድ  ከዚህ ቀደም ከአማራ ክልል የሚላኩ እንጀራ እና የላም ወተቶችን እየተቀበለ በሚኖርባት ሎጊያ ከተማ ይሸጥ ነበር። ይሁንና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እነዚህን ባለማግኘቱ የሻይ ቤት ስራው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ይናገራል። « በሻይ ቤት ስራ ነው የተሰማራሁት። የወተት ምርቶች እና እንጀራ ነው የምሸጠው። ግን እነሱ ባልታወቀ ምክንያት እየገቡ አይደለም። ስለዚህ ከስራ ውጪ ሆነናል። መረጃም የለንም። ከዛሬ ነገ ይጀመራል እየተባለ 15 ቀን አለፈው። እኛም ስራ አጥተን ተቀምጠናል። ቤት ተከራይተን ነው የምንሰራው፣ የልጆች አሳዳጊ ነኝ። በአሁን ሰዓት በኑሮ ውድነት ምክንያት ስራ ካልተሰራ በጣም አስቸጋሪ ነው። እና ይኼ ችግር እንዲፈታልን እንደልጋለን።»

ሌላዋ ወጣት ነጋዴ መዲና ትባላለች። እሷም በሎጊያ ከተማ ነዋሪ ስትሆን  ከኮምቦልቻ ከተማ የሚመጣ ወተት እና እርጎ በመሸጥ እስካለፉት ሳምንታት ድረስ ትተዳደር ነበር።  « እስከዛሬ ድረስ ወተት እና እርጎ እየሸጥን ነበር ስንሰራ የነበረው። አሁን ግን ባልታወቀ ምክንያት እርጎ ተቋርጧል። ያው እኛ ወተቱን ማግኘት አልቻልንም። ቤቴ ጠባብ ናት። ስለዚህ ትናንሽ ነገሮች እርጎ እና ቀዝቃዛ ነገር ነው የምሸጠው። ልጅ አሳዳጊ ነኝ እና አሁን ላይ ባልታወቀ ምክንያት ቆሟል።» 

ወተት በብርጭቆዎች
ምስል 0pidanus /Fotolia

መዲና ይህን ስራ ስትሰራ ሰባት አመት ሆኗታል። 29 ዓመቷ ነው። እሷ እንደምትለው ምንም እንኳን ሱቋን እንዳትዘጋ በአሁኑ ሰዓት ውኃ እና ሌሎች ነገሮችን እየሸጠች ቢሆንም ከእንግዲህ በኋላ ወተት የማታገኝ ከሆነ ያላት አማራጭ ንግዷን ማቆም ብቻ ነው ።« አሁን ውኃ እየሸጥን ነው። ይህን የምናደርገው ስለሚያዋጣን ሳይሆን ቤቱ እንዳይዘጋ ነው። እንጀራም እሸጣለሁ። ግን እንጀራ ሸጬ የማገኘው እና ወተት ሸጬ የማገኘው ጥቅም እኩል አይደለም። ከወተቱም ከዚህም ከዚያም ሲጨመር ነው እንጂ አንድ ነገር ብቻ የቤት ኪራይ፣ ግብር እና የሰራተኛ ወጪን አይሸፍንም። በዛ ላይ ካለንበት ቦታ አንፃር ሰዎች የሚፈልጉት ቀዝቃዛ ነገር ነው።»

የላም ወተት እርባታ ላይ የተሰማሩት አቶ ይማም

መዲና «የወተት አከፋፋዮቹ ከዚህ ቀደም በመኪና ጭነው አምጥተው እስከ ጠዋቱ ሶስት ሰዓት ድረስ ያከፋፍሏቸው እንደነበር ነግራናለች። ከእነዚህ የወተት አከካፋፋዮች አንዱ በኮምቦልቻ ከተማ የላም ወተት እርባታ ላይ የተሰማሩት አቶ ይማም ናቸው።  አቶ ይማም ከአማራ ክልል በተጨማሪ የላም  ወተት አፋር ክልል ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ያቀርቡ ነበር።  ይሁንና እሳቸውም ካለፉት ሁለት ሳምንታት አንስቶ ይህን ማድረግ አልቻሉም።« የምንልክ የነበረው ባቲ፣ ሚሌ፣ ሎጊያ እስከ ሰመራ ድረስ አፋር ክልል እንልክ ነበር። በምንልክበት ጊዜ ከሁለት ሳምንት በፊት ወተታችን ከኮምቦልቻ ተጭኖ ሄዶ ሎጊያ ከደረሰ በኃላ ችግሩ ምንድን ነው? ደንበኞቻችን አልቀበል ብለው ነው ወይ ብለን ስንጠይቅ፤ አይ የጤና ሚኒስቴር በጤና ምክንያት በሚል እንዳይገባ ከልክሎ ነው የሚል ምላሽ ሹፌሮቹ ሰጡን። ምክንያቱም እኛ ወተቱን የምንልከው በእምነት ነው። በትራንስፖርት ሹፌሮች የምንልከው። »

በዚህ የወተት ላም እርባታ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ ሁለት አስርተ ዓመታት እንደተቆጠረ የሚናገሩት  አቶ ይማም ምንም እንኳን አሁን ላይ ወተቱን የሚሸጡበት አማራጮች ቢያገኙም  ወደ አፋር ክልል የሚልኩት ወተት በድንገት በተቋረጠበት ሰዓት ኪሳራ ገጥሟቸዋል።« ከግንቦት 4 ቀን ጀምሮ ይኼው እስከ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን አልተጀመረም። እኔ ከ 60 እስከ 80 ሊትር እልክ ነበር። ስለዚህ ከዛን ጊዜ አንስቶ ገበያዬን እዚህ አፈላልጌ እስካገኝ ድረስ የነበረው ኪሳራ ምን ያህል እንደሚሆን መገመት ይቻላል።»

አቶ ይማም ለጊዜው እዛው ያሉበት ኮምቦልቻ ከተማ ወተታቸውን መሸጥ የሚችሉበትን አማራጭ ማፈላለግ ችለዋል። አዲስ ደንበኞች ካገኙ ወደ አፋር ክልል መላካቸውን ያቆሙ ይሆን? « ወተት ለብልሽት ቅርብ ነው። እኔ ደግሞ ገበያ ባለበት አፈላልጌ መሸጥ አለብኝ። የትም ይሁን የት የገበያ ሰንሰለቱን አግኝቼ መሸጥ ነው አላማዬ። ስለዚህ ግቤ ሎጊያ ላይ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ወተት ለብልሽት በጣም ተጋላጭ ነው። ስለዚህ ገበያዬ አፋር ክልል ብቻ ነው ልል አልችልም። እኔ አላቢ ነኝ።  ትኩሱን ወትት ለደንበኞች ማከፋፈል ይኖርብኛል።»

አማራጭ ያጡት የሎጊያ ወጣቶች

የሎጊያ ከተማ ነዋሪ የሆነው አህመድ ግን ለጊዜው ብዙ አማራጮች የሉትም። ስለሆነም አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ይጠይቃል። « መስራት እንፈልጋለን። ካልሰራን ፣ ገቢ ከሌለ ከባድ  ነው። ብዙ ወጪ አለብን። እና የሚመለከተው አካል ተጠይቆ ችግሩ ቢቀረፍልን እና ስራውን ብንጀምር ደስተኛ ነን።» 

ተቃውሞ የሚያሰሙ ወጣቶች
አፋር ክልል በስራ አጥነት ተቃውሞ የሚያሰሙ ወጣቶች 2015 ዓ ምምስል Privat

ሁሉም ነጋዴዎች ካልተረጋጠ መረጃ ይልቅ ከሚመለከተው አካል ትክክለኛ ምላሽ ይሻሉ። ምርቶቹ ወደ አፋር ክልል እንዳይገቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል ወደተባለው የአፋር ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም አልመለሱልንም። በአማራ ክልል ባቲ ወረዳ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በተለምዶ (አተት) መከሰቱን የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ከ1 ወር ገደማ በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።  «ከወተት እና እንጀራ በስተቀር ሌሎች አዝቤዛዎች ከባቲ እየገቡ ነው» የሚለው አህመድ ወተቱን በተመለከተ ሰማሁ የሚለው አዲስ ነገር አለ፤« የተመረመረ እና የተጣራ ወተት መምጣት አለበት ተብሎ አሁን አንዲት ሴት ከደሴ ደረጃውን የጠበቀ ወተት ለማምጣት ብላ ከጤና ጥበቃ እና ግብርናዎች ጋር እየሰራች እንደሆነ፤ ማቀዝቀዣ ባለው መኪና እንዲመጣ እየሰራች እንደሆነ እና በቅርቡ ትጀምራለች የሚባል ነገር ሰምተናል»ይላል አህመድ።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕሮብ ድረስ ወተት ወደ አፋር ክልል ሎጊያ እየገባ እንዳልሆነ ነው አከፋፋዩም ሆኑ ወተት የሚገዙት ደንበኞች የነገሩን። እንጀራ ደግሞ ከዕሮብ አንስቶ አፋር ክልል መግባት ጀምሯል።  

 

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ