1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልዩ ኃይሎች አደረጃጃት የቀሰቀሰዉ ዉዝግብ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2015

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት የተባለውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተጀመረው ጠንካራ ተቃውሞ ዛሬም መቀጠሉ ታውቋል ። ዉሳኔውን «ሕገ - ወጥ» በማለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 5 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፖለቲከኞች ተቃውመውታል ። ሌሎች ክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀታቸውን መልሶ ለማዋቀር ሥራ መጀመራቸውን እየገለፁ ነው ።

https://p.dw.com/p/4PuzU
Logo | National Movement of Amhara

የብልፅግና መግለጫና የአብን ተቃዉሞ

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ ያሳለፈዉን ዉሳኔ "ሕገ - ወጥ" በማለት  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ አምስት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፖለቲከኞች ተቃወሙት። የምክር ቤቱ አባላት ባወጡት መግለጫ የገዢዉን ፓርቲ ዉሳኔን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲመረምር  ጠይቀዋልም። ብልጽግና ፓርቲ ትናንት ባወጣው መግለጫ "የፖለቲካ ተዋናያን" ያላቸዉን ግን በስም ያልጠቀሳቸዉን  ወገኖች ከ"ሕገ - ወጥ እና መርህ አልባ"  እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል በማለት አስጠንቅቋል። 

ይህ ውሳኔ "በብዙ ጥናት ፣ በጥልቅ ውይይት፣ በሰከነ ንግግር እና የጋራ መግባባት የተደረሰበት" መሆኑን የጠቀሰው ብልጽግና ፓርቲ "በሁሉም ክልሎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን" መሆኑንም አስታውቋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብንን የሚወክሉት አባላት ባወጡት መግለጫ ደግሞ ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ውይይት ያልተደረገበት የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ ከመሆኑም በላይ በክልሎች ላይ ጣልቃ ገብነት የተስተዋለበት ውሳኔ ነው በሚል ተችተዋል። 

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት የተባለውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተጀመረው ጠንካራ ተቃውሞ ዛሬም መቀጠሉ ታውቋል።ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌሎች ክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀታቸውን መልሶ ለማዋቀር ሥራ መጀመራቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።

ብልጽግና ፓርቲ ትናንት ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም በጽሑፍ ባወጣው መግለጫ "የፖለቲካ ተዋናያን" በሚል ብቻ የገለፃቸው አካላት ሕገ - ወጥ እና መርህ አልባ" ካለው እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አሳስቧል። 

"ለብዥታ እና ተገቢውን መስመር ለሳተ የትርጉም አንድምታ የተጋለጠው" ያለው ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ "የሕዝብን ፍላጎት ከግምት ዉስጥ ያስገባና ሕገ መንግስታዊ እንደሆነ" መረዳት ያስፈልጋል ብሏል።
በዚህ መግለጫ ላይ ከፓርቲው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አልተሳካም።"ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት እጅግ አስከፊ በሆነ ርሀብ፣ ስደትና መፈናቀል፣ ማንነት ተኮር ጅምላ ግድያዎችና የዘር ፍጅቶች እንዲሁም በማያባሩ ግጭቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ይገኛሉ" ያሉት በ6ኛው ዙር ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡ የአብን አምስት አባላት የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከነበረችበት አንፃራዊ መረጋጋት፣ ሰላምና ተስፋ መፈንጠቅ ወደ ትርምስ፣ ሥጋትና የመበተን አደጋ ውስጥ ገብታለች በማለት ዛሬ ባወጡት መግለጫ ገልፀዋል።
ይህንን አቋም ካራመዱት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
"በምክር ቤቶች ደረጃ ውይይት ያስፈልገው ነበር። የማሳመን ሥራ መሠራት ነበረበት"። 
አምስቱ አብንን ወክለው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ላይ በተለይም በአማራ ክልል እያደረገው ነው ያሉት ጣልቃ ገብነት የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን እና ሕገ - መንግስትን ጭምር የጣሰ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ሳይሆን የተሻለ የማስታጠቅ፤ የመበተን ሳይሆን የማደራጀት ሥራ ላይ መሆኑን ገልጿል። "ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ፍጹም ሀሰት  እንደሆነ" ገልጾ በተመሳሳይ ጊዜ  በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር መሆኑን አስታውቋል ። 

በአማራ ክልል ይህንን ውሳኔ በመቃወም እየተደረጉ ያሉ ተቃውሞዎች ዛሬም ቀጥለዋል። ከተሞች መንገዶቻቸው ዝግ ናቸው። የክልሉ ዋና ዋና ከተሞችም ዝርዝር የፀጥታ ክልከላዎችን ያካተቱ ጥብቅ ማመሪያዎችን አውርደዋል። አቶ አበባው የክልሉን የአሁን ሁኔታ ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
" ተቃውሞዎች አሉ። ጥሩ ነገር እየታየ አይደለም"። 
ውጥኑ"በሰላማዊ መንገድ በትእግስት እና ዘላቂ ሕጋዊ መፍትሔን ከማምጣት አንጻር እንዲፈጽም የጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ( ኢሰመጉ ) ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቆሙ ጠይቋል።
መንግስት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የተዘጉ መንገዶችን በማስከፈት የዜጎችን የመዘዋወር መብት አንዲያስከብርም ጠይቋል። 
በሌላ በኩል የሌሎች ክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀታቸውን መልሶ ለማዋቀር ሥራ መጀመራቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው እንደገቡበት የተገለፀው ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ይገኝበታል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ