1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዳሴ ግድቡ 13ኛ ዓመትና ውስብስብነት

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ማጠናቀቂያ ዋዜማ ላይ መድረሱ ተገለጸ። ይህንኑ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የህዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጊይ የተጣለበት 13 ዓመትን ምክንያት በማድረግ በተካሄደ ውይይት ላይ ይፋ ያደረጉት አምባሳደር ስለሺ በቀለ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4eJnr
የህዳሴው ግድብ
የህዳሴው ግድብ መሠረት ከተጣለ 13 ዓመት ሞላው። ምስል AMANUEL SILESHI/AFP/Getty Images

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ትግበራ፣ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሥራው 13ኛ ዓመት ላይ መድረሱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እንዲሁም የግድቡ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል። የዓመታቱ ጉዞና የተራዘመበት ምክንያት፣ የግድቡ የግንባታ ውስብስብነትና የኮንትራት ሁኔታ መሆኑንም አመልክተዋል። ውስብስብነቱ፣ የመሠረት ቁፋሮና ግንባታው ረጅም ጊዜ መውሰዱን የገለጹት ዶክተር ስለሺ፣ የኮንትራት ሁኔታውን መከናወን ያልቻለውና ልምድ ሳይኖረው የተሰጠው ያሉት ሜቴክ፣ ሥራውን ቢያንስ በአምስት ዓመታት በማጓተቱ መሆኑን አውስተዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደት፣ በኢትዮጵያ የኮረና፣ ጦርነት እና የሰላም እጦት የገጠሙ ቢሆንም ፣ ግንባታው እንዳይስተጓጎል፣ በጉዳዩ ዙሪያ ችግር እንዳይገጥም በመጠንቀቅና በመስዕዋትነት ጭምር በበቂ ጥበቃ ተሰርቷል፣ እየተሰራም ይገኛል ሲሉ አምባሳደሩ ገልፀዋል።

ግድቡ በኢትዮጵያ ልማት ምን ይዞ መጣ?

መጋቢት 24 ቀን፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በይፋ የተጀመረበት ዕለት፣ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ እጅግ ትልቅ ቁም ነገር ይዞ የመጣና፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ግንባታ ከፍተኛ እመርታ ያመጣ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ዕለት መሆኑን ዶክተር ስለሺ አስረድተዋል።

አምባሳደር ስለሺ፣ በግድቡ በአሁኑ ጊዜ በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በፎቶግራፍ በማስደገፍ፣ በአካልና በበይነ መረብ አማካይነት ለታደሙ እንግዶች ገለጻ አድርገዋል።

 

የህዳሴው ግድብ
የህዳሴው ግድብ የኃይል ማመንጫ ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

«በሕብረት ችለናል»

የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13 ኛ ዓመትና «በሕብረት ችለናል» በሚል መርዕ በተካሄደው፣ በዚሁ ዝግጅት ላይ በግድቡ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶች አምባሳደር ስለሺ ምሥጋና አቅርበዋል። ትናንት በተካሄደው በዚሁ የውይይትና የምስጋና ዝግጅት ላይ፣ የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ እንዲረዳ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

የተሣታፊዎች አስተያየት

በዚሁ ዝግጅት ላይ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ ፋኑኤል፣ በግድቡ ሥራ ላይ እንደታየው ትብብር ሁሉ፣ ለሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የፈርስት ሂጂራ ተወካይ በበኩላቸው፣ ከፖለቲካ ልዩነት በመውጣት የግድቡን ግንባታ ዳር ማድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 ታሪኩ ኃይሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ