1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ስለ መርአዊ ግድያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 26 2016

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይላት ጥር ወር በአማራ ክልል መርአዊ ከተማ ከታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ውጊያ በርካታ ንጹሓን ዜጎችን ገድለዋል ሲል ሁዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ዘለግ ያለ ዘገባ አመለከተ።

https://p.dw.com/p/4eQyf
ሒዩማን ራይትስ ወች እንደሚለዉ ባለፈዉ ጥር መርዓዊ ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ኃይልና አማራ ክልል የተደራጀዉ የፋኖ ኃይል የገጠሙት ግጭት እየተባባሰ ነዉምስል AP/picture alliance

የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ስለ መርአዊ ግድያ

 በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ መከላከያን ጨምሮ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ብዙ በደል ፈጽምዋል ያለው የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ፤ የተባበሩት መንግሥታት አስቸኳይ ገለልተኛ ምርመራ እንደሚያሻ እና የጥፋቱን አዛዦች ተጠያቂ አለማድረግ ሊቆም እንደሚገባ ጠቅሷል። ድርጅቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው የምርመራ ዘገባው የተገደሉትን ንጹሓን ዜጎች ቁጥር ይፋ ባያደርግም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ከአዲስ ስምሪት ማገድን ሊያስቡበት ይገባል ብሏል። በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ድኤታዎች ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። በመርአዊ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን የ45 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ አስመልክቶ ዶቼ ቬለ በወቅቱ የጠየቃቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ «የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዓይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም» ማለታቸው ይታወሳል።

የመብት ድርጅቱ ዝርዝር የምርመራ ዘገባ 

ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ. ም በመርአዊ ከተማ በርካታ ያላቸውን ንጹሓን ዜጎች መግደሉንና «ሌሎች የጦር ወንጀሎችን» መፈፀሙን በዘገባው ጠቅሷል። ይህ ድርጊት የፌዴራል ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያን ተከትሎ መፈፀሙንም አስታውቋል።

ድርጅቱ ይህንን ድርጊት ፈጽመዋል ያላቸው የጦር አዛዦች ለፈፀሙት አስከፊ የመብት ጥሰት ኃላፊነት ወስደው ተጠያቂ እስኪሆኑ ድረስ የተመድ እና አፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያን የፌዴራል ኃይላት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ ከማሰማራት ማገድን ታሳቢ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ድርጉቱ በተፈፀመበት ጥር 20ቀን 2016 ዓ. ም የፋኖ ታጣቂዎች በመከላከያ ሠራዊት ላይ ቀድመው ጥቃት መክፈታቸውንና ቆይተው ከተማውን ለቀው መውጣታቸውን ያተተው የድርጅቱ ዘገባ ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለስድስት ሰዓታት ንጹሓንን በተለይም ወንዶችን በአደባባይ እና በቤት ለቤት አሰሳ መረሸናቸውን፣ ንብረትም ማውደማቸውን ዘርዝራል።

እንደ ጎርጎሪያን የዘመን ቀመር ከየካቲት 9 እስከ መጋቢት 14 የጉዳቱ ሰለባዎችን ፣ ቤተሰቦቻቸውን እና እማኞችን ጨምሮ 20 ሰዎችን በስልክ ማነጋገሩን የጠቀሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች ለዚህ ዘገባው ሌሎች የመረጃ ምንጮችንም መመርመሩን አስታውቋል።

ድርጅቱ ነዋሪዎች ነገሩኝ ባለው መሠረት የኢትዮጵያ «ወታደሮች ቤቶችን ዘርፈዋል፣ 12 ባለ ሦስት ጎማ ባጃጅ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ፣ ሆቴሎችን እና የንግድ ተቋማትን አቃጥለዋል።»

ትክክለኛውን የማቾችን ቁጥር ማረጋገጥ አለመቻሉን የገለፀው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ የአካባቢ መሪዎች የ40 ሟች ሰዎችን ስም ዝርዝር ማጋራታቸውንና ሦስት ሰዎች እስከ 80 የሚሆኑ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ መግለፃቸውን አትሟል። አክሎም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ 89 ሰዎች ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ደግሞ 45 ሰዎች መርአዊ ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን ማሳወቃቸውን አስታውሷል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኢሰመኮ አርማ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመርአዊ ከተማ «ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች «'ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል» በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን» በወቅቱ የገልጿል።ፎቶ ከማኅደር፤ የኢሰመኮ አርማምስል Ethiopian Human Rights Commission

በትንሿ መርአዊ ከተማጎዳና ላይ በወታደሮች ክልከላ የተደረገበት የ22 ሰዎች አስክሬን ደጅ ውሎ ማደሩን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መመርመሩንም የመብት ድርጅቱ ጠቅሷል።

አማራ ክልል ውስጥ የተደረጉት ጥፋቶች በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከሉ እና የጦር ወንጀል የሚባሉ መሆናቸውንም ድርጅቱ ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ «የኢትዮጵያ መንግሥት የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለሚያደርሷቸው የመብት ጥሰቶች ትርጉም ያለው ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለመቻሉ፤ ቀጣይነት ላለው የጥቃቶች አዙሪት እና አጥፊዎችን ያለመክሰስ ችግር አስተዋጽኦ አድርጓል» ሲል በዘገባው አመልክቷል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌቲሽያ ባድር «በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ሆን ተብሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በሚያሳዝን ሁኔታ በግጭት አካባቢዎች ላሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት አኗኗር መገለጫ ሆኗል» ሲሉ የሁኔታውን አስከፊነት አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አጋሮች፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በደል የፈጸሙት የጦር አዛዦች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ጠይቀዋል።

 

በወቅቱ የነበሩ የመንግሥት፣ የመብት ድርጅቶች እና የሃገራት መግለጫዎች 

በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ድኤታ ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ( ዶ/ር ) በወቅቱ ለዶቼ ቬለ ሰጥተውት በነበረው ምላሽ ግን «የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዓይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም» ብለው ነበር። ታጣቂዎቹ  «በተለያዩ አቅጣጫዎች መከላከያ ሠራዊቱ የሰፈረበትን ካምፕ በአራት አቅጣጫ በማፈን መሣሪያ እና ሎጂስቲኩን ለመዝረፍ በመንቀሳቀሳቸው ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ ነው እርምጃ የወሰደው።» 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመርአዊ ከተማ «ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች «'ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል» በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን» በወቅቱ የገለፀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ደግሜ በዚህ ክስተት 89 ሰዎች መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል። ድርጊቱን የአሜሪካን ጨምሬ የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ኤምባሲዎች እና የመብት ድርጅቶች አውግዘው ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ አሳስበዋል። በአማራ ክልል ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ. ም ጀምሮ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን የትጥቅ ግጭቶች ግን አሁንም ቀጥለዋል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ