የሀማስ ከፍተኛ መሪ ኢስማኤል ሀኔይ ግድያና ተጽእኖው
ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016የሀኔይ ግድያ መቼና እንዴት ተፈጸመ
የሐማሱ ከፍተኛ መሪ ኢስማኤል ሀኔይ መገደላቸውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ያሳወቀው ዛሬ ማለዳ ነበር። ከጠባቂዎቻቸው አንዱም ከርሳቸው ጋር መገደሉንም አረጋጋግጧል። የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽክያን የቃለ መሀላ ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ቴህራን የነበሩት ሀኔይ የተገደሉት ቴህራን የሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ከተመታ በኋላ መሆኑን አብዮታዊ ዘቡ አስታውቋል። ግድያው እየተጣራ መሆኑን ውጤቱም ከዚያ በኋላ እንደሚገለጽ ነው የተናገረው።
ስለግድያው ወዲያውኑ ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም፣ እስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ሌሎችም በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ በያኔው 1200 ሰዎች የተገደሉበትንና 250 የታገቱበትን የመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ምህርቱን ጥቃት በእስራኤል ላይ ከፈጸመ በኋላ ሀኔይንና ሌሎች የሀማስ መሪዎችን ለመግደል የዛተችው እስራኤል በግድያው ተጠርጥራለች።መሪው የተገደሉበት ሀማስ ሀኔይ በእስራኤል ጥቃት ኢራን ውስጥ ተገድለዋል ሲል አረጋግጧል። እውን ሀማስን ሙሉ በሙሉ «ማጥፋት» ይቻላል?
ግድያው የተኩስ አቁሙን ድርድር ይጎዳል
የሀኔይ ቢሞቱም የርሳቸውን ዓላማ ከግብ ማድረሳችን አይቀርም የሚሉ ወገኖቻቸው ቢኖሩም ግድያው ሐማስን እንደሚጎዳ በሰፊው ተገምቷል። ዘላቂ ትምሕርት በተባለው የብሪታንያ የጥናት ተቋም የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ጥናቶች ሃላፊ ሮክሳን ጋርማን ፋርማያን የሀኔይ መገደል ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል። በርሳቸው አስተያየት በተለይ ሐማስና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም ፤በዚህም ተጎጂው ሀማስ ብቻ ሳይሆን አደራዳሪዎቹም |ጭምር መሆናቸውን አስረድተዋል።
«ግድያው በጣም ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው ነው። በመጀመሪያ እርሳቸው የሀማስ ተደራዳሪ ነበሩ። «እስራኤልና ሐማስ» የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በሚኖሩበት በቀጠር ከዩናይትድ ስቴትስና ከእስራኤል ጋር ሲደራደሩ ነበር ።ምናልባትም ያ ወደፊት ላይጓዝ ይችላል። በርግጠኝነት እስካሁን በሄደበት መንገድ ላይቀጥል ይችላል። የተግባር ሰው በመሆናቸው ይታወቃሉ ። እርሳቸው በድርድር በጣም የተካኑ ሰው መሆናቸውን የተገነዘቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አሉ። እናም ሀማስ በዚህ ቡድን ውስጥ አንድ ትልቅ ሰው አጥቷል፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አደራዳሪዎችም ጭምር ።»
የኢራን እስራኤልን የመበቀል ዛቻ
ኢራን ትናንት ለሊት ቴህራን ውስጥ ለተፈጸመው የሀኔይ ግድያ እሥራኤልን እንደምትበቀል ዝታለች። የኢራን የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ዛሬ እንዳሉት እስራኤል ራስዋን ለአሰቃቂ ቅጣት አዘጋጅታለች፤ ተወዳጁ እንግዳች ያሏቸውን የሀኔይን ግድያ መበቀሉ የኛ ሃላፊነት አድርገን ነው የምንቆጥረው ብለዋል።የአለማቀፍ ወንጀሎች መዳኛ ፍርድ ቤት በእስራኤልና ሀማስ መሪዎች ላይ ያቀረበው ክስ ጭብጥ ከቴህራን ዩኒቨርስቲ የኢራን ጉዳዮች ተንታኝ ስለኢራን የበቀል ዛቻ በሰጡት አስተያየት እንዳሉ ከዚህ ቀደም በእሥራኤል ላይ የድሮኖችና የሚሳይል ጥቃቶችን ያዘነበችው ኢራን የዛተችውን ጥቃት መፈጸሟ የሚቀር አይመስልም።የአለማቀፍ ወንጀሎች መዳኛ ፍርድ ቤት
«እንደሚመስለኝ ቀጥተኛ የአጸፋ ጥቃት ይኖራል። ታስታውሱ እንደሆነ ባለፈው ኢራን ከ300 መቶ በላይ ድሮኖችንና ሚሳይሎችን እሥራኤል ላይ ተኩሳለች።እነዚህን ጥቃቶች ለማክሸፍ እሥራኤል ባደረገችው ሙከራ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ስታወጣ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ከስክሰዋል። ይህም ደግሞ ለውጥ አምጥቷል። የእሥራኤል መንግሥት ሶሪያ የሚገኙ ኢራናውያንን ዒላማው ማድረግን አቁሟል። አሁን ኢራናውያን ፣ የእስራኤል መንግሥት ኢራን ውስጥ ሰዎችን ለመግደል እንዳያስብ ከባድ ቅጣት እንዲደርስበት ማድረግ ይፈልጋሉ። »
የሐማስ ደጋፊ በሆነችው በኢራን የሦስት ቀናት ሀዘን ታውጇል።
ቱርክና የዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ስለሀኔይ ግድያ የሰጡት አስተያየት
የቱርክ ፕሬዝዳንት ናሬሴፕ ጠይብ ኤርዶጋን የሀኔይን ግድያ አውግዘው ድርጊቱንም የፍልስጤማውያንን ጥያቄ ያኮሰሰ የህዝቡንም ሞራል የሚሰበርና የሚያመሸማቅቅ ብለውታል።
ሟቹ ሀኔት የጋዛ ሰርጥን ለቀው በስደት ቀጠር መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት ግድም ሆኗል። ሀኔይ የተገደሉት ዩናይትድ ስቴትስ ሃማስ እና እስራኤል ቢያንስ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ግፊት ለማድረግ በመሞከር ላይ ባለችበት ወቅት ነው። ይህን ለማሳካትም የዩናይትድ ስቴትስ የእሥራኤል የቀጠር እና የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቅርቡ ተገናኝተው ሊነጋገሩ ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ ስለ ሀማሱ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሀኔይ ግድያ የምታውቀው ነገር እንደሌለና እጇም እንደሌለበት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንተኒ ብሊንከን በጉብኝት ላይ ካሉባት ከሲንጋፖር ተናግረዋል። በዚሁ አጋጣሚም የተኩስ አቁሙን ጥሪ አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። የተባባሰው የእስራኤል ሀማስ ጦርነትና የአውሮጳውያን አቋም
«በርግጥ ዘገባዎችን አይቻለሁ አሁን ልነግራችሁ የምችለው እንዳልኩት ከተኩስ አቁሙ አስፈላጊነት የሚወስደን ነገር የሚኖር አይመስለኝም። ይህ ታጋቾችን ወደ ቤታቸው የመመለስ ፤ በየቀኑ እጅግ የሚሰቃዩትን ፍልስጤማውያን ፍላጎት ነው።»
ቻይና በበኩልዋ የሀኔይን ግድያ አውግዛ ግድያው በአካባቢው ውጥረቱን ያባብሳል ስትል ስጋቷን ገልጻለች። የእስማኤል ሐኔይ የአስክሬን ሽኝት ሐሙስ ኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ይከናወናል ተብሏል። የጸሎት ሥርዓት እና ቀብራቸው ደግሞ በስደት ይኖሩባት በነበረችው የኳታር ዋና ከተማ ዶሐ ውስጥ እንደፈጸም ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ