1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የሥነ ውበት እይታ

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2016

አዳጊ ሴቶች በሥነ ውበት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ፣ ከፅንሰ ሀሳቡ ጀምሮ ሥለውበት አጠባበቅ ያላቸው እይታ እንደየአመለካከታቸው ሊለያይ ይቻላል ፡፡ በሀዋሳ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑት የአብሥራ እና ሽታዬ በተመሳሳይ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆንም ሥለውበት ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4dQWe
በሀዋሳ ከተማ  የ2ኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑት የአብሥራ እና ሽታዬ  ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊሻን ጋር
በሀዋሳ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑት የአብሥራ እና ሽታዬ ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊሻን ጋርምስል DW

የአዳጊ ሴቶች የሥነ ውበት እይታ

አዳጊ ሴቶች በሥነ ውበት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ተመሳሳይነት አለው ተብሎ አይታሰብም ፡፡  ይልቁንስ ከፅንሰ ሀሳቡ ጀምሮ ሥለውበት አጠባበቅ ያላቸው እይታ እንደየአመለካከታቸው ሊለያይ ይቻላል ፡፡ የ17 ዓመት ታዳጊ የሆኑት ተማሪ የአብሥራ ነመሮ እና ተማሪ ሽታዬ መሀመድ ከገጠራማ አካባቢ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ  እንደሚገኙ ይናገራሉ ፡፡ የአብሥራ እና ሽታዬ በተመሳሳይ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆንም ሥለውበት ያላቸው አመለካከት ግን የተለያየ ነው ፡፡ የአብሥራ አዳጊ ሴቶች ፀጉር ፣ ቅንድብ እና ጥፍሮቻቸውን ጨምሮ ለተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸው ተጨማሪ የውበት ግብዓቶችን መጠቀም አላሥፈላጊ ነው የሚል አመለካከት እንዳላት ትናገራለች ፡፡

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች : የሴት ልጅ አለባበስ ከፆታዊ ጥቃት ያድናል?

ሴት ልጅ ከፈጣሪ ባገኘችው የተፈጥሮ ውበቷ ብቻ መገኘት እንዳለባት የጠቀሰችው የአብሥራ “ በአዳጊ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት የግል ንጽህናዋን ከመጠበቅ ባለፈ እራሷን ተፈጥሯዊ ባልሆኑ / አርቲፊሻል / የውበት ግብዓቶች በማስዋብ መጨነቅም ሆነ ጊዜዋን ማባከን አይጠበቅባትም  ፡፡

የአፍሪቃውያን የውበት ሱቅ
አዳጊ ሴቶች ፀጉር ፣ ቅንድብ እና ጥፍሮቻቸውን ጨምሮ ለተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸው ተጨማሪ የውበት ግብዓቶችን ይጠቀማሉምስል Picture alliance/dpa

ለምሳሌ እኛ በምንማርበት ትምህርት ቤት ሠው ሠራሽ ፀጉር መቀጠል የተከለከለ ነው፡፡ ይሁንእንጂ አንዳንድ ተማሪዎች ሰው ሠራሽ  ፀጉር በመቀጠል ከመምህራን ቁጥጥር ለማምለጥ ፀጉራቸውን በልብስ ሸፈነው ወደ ግቢ ለመግባት ሲሞክሩ ይስተዋላል ፡፡ እነኝህ ተማሪዎች ያን ያህል መጨነቅ አለባቸው  ብዬ አላሳብም ፡፡ አኔ እንደምታይኝ ለመዋብ ብዬ ምንም አይነት ተጨማሪ ነገር አልጠቀምም “ ብላለች።

ከተሜ ወጣቶችና አለባበሳቸው

በአንጻሩ ተማሪ ሽታዬ መሀመድ በአብሥራ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደማትሳማማ ትናገራለች ፡፡ ሽታዬ ሴት ልጅ ተጨማሪ የውበት ግብዓቶች ብትጠቀም ክፋት የለውም ትላለች ፡፡ ማህበረሰቡ ውበቷን ለመጠበቅ በምትሞክር አዳጊ ሴት ላይ በጎ አመለካከት ላይኖረው እንደሚችል የምትናገረው ሽታዬ “ ዋናው ነገር ትምህርቷን እስከተማረችና ጊዜዋን በአግባቡ እስከተጠቀመች ድረስ ተጨማሪ ግብዓቶችን ተጠቅማ ብትዋብ ችግር አለው ብዬ አላምንም ፡፡ ለምሳሌ አኔ ከትምህርት ቤት ውጭ ተጨማሪ የውበት ግብዓቶችን እጠቀማለሁ ፡፡ ይህን ማድረጌ  ያስከተለብኝ ችግር የለም  “ ብላለች ፡፡

ሊሻን ዳኜ / ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ