1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2016

ጀርመናዊትዋ የፊልም ተዋናይ ሳንድራ ሁለር በምርጥ ዘርፍ ተዋናይት ኦስካር ባታሸንፍም፤ የሚሊዮኖችን ልብ በተወነችበት ፊልም አግኝታለች። ቀደም ሲል አዉሮጳ ላይ ሽልማትዋን እንድትወስድ ወደ መድረክ ስትጠራ፤ በአዳራሹ የነበረዉን ህዝብ ለዓለም ሰላም በፀጥታ መልክት እንዲያስተላልፍ ለሰላም እንዲቆም ጠይቃ ነበር።

https://p.dw.com/p/4dWfp
ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ
ጀርመናዊቷ የፊልም ተዋናይ ሳንድራ ኹለር በ96ኛው የኦስካር አካዳሚ ሽልማት ላይ በሎስ አንጀለስምስል Kevin Sullivan via ZUMA Press Wire/picture alliance

ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ

ጀርመናዊትዋ የፊልም ተዋናይ ሳንድራ ኹለር በስኬቷ ቀጥላለች። ጀርመናዊትዋ የፊልም ተዋናይ ሳንድራ ሁለር በምርጥ ተዋናይት ኦስካር ባታሸንፍም፤ የተወነችባቸው ሁለት ፊልሞች ሽልማቶችን ተቀብለዋል። ሳንድራ ኹለር ወርቃማውን የኦስካር ሽልማት በእጅዋ ባታስገባም የሚሊዮኖችን ልብ በተወነችበት ፊልም አግኝታለች። እሷ የተወነችበት ፊልም " The Zone of Interest " የዓመቱ ምርጥ ፊልም በመባል ተሸላሚ ሆንዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የስዕል ጥበብና ሳይንስ ማዕከል የሚዘጋጀዉ ዓመታዊ የፊልም ዘርፍ ሽልማት ማለት በ«ኦስካር» ላይ በምርጥ የፊልም ተዋናይ ዘርፍ ታጭታ የነበረችዉ የ 45 ዓመትዋ ጀርመናዊት ሳንድራ ኹለር፤ በዋና ተዋናይ የተጫወተችበት "Anatomy of a Fall" የተሰኘዉ ፊልም የባልዋን አሟሟት ምክንያት ሴት ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል። በጀርመናዊት ደራሲ የተፃፈዉ ይህ ፊልም፤ የተሰራዉ ፈረንሳይ አገር ዉስጥ ሲሆን በጀርመንኛ በፈረንሳይኛ እና በእንጊሊዘኛ ለእይታ የቀረበ ፊልምምነዉ።  ጀርመናዊትዋ  ሳንድራ ሁለር በዋና ተዋናይነት የተወነችበት ይህ ፊልም በአሜሪካኑ የፊልም አካዳሚ ኦስካር በምርጥ ተዋናይነት ለኦስካር ሽልማት ታጭታ ነበር።  

ጀርመናዊትዋ የፊልም ተዋናይ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 2023 ጥቅምት ወር ላይ በአሜሪካን አገር በፊልም ኢንዱስትሪዉ ሆሊዉድ ላይ በሚታተም አንድ ጋዜጣ ሽፋን ላይ መቅረብዋ፤ ለጀርመን ተዋናይ ያልተለመደ በመሆኑ ክብር እንደሆነ ተነግሮላታል።

በቅርቡ ለፊልም እና ለምርጥ የቴሌቭዥን ድራማ እና ፊልሞች የሚሸልመዉ ጎልደን ግሎብ ላይ "በድራማ ፊልም ምርጥ ተዋናይት" ተብላ ታጭታ የነበረችዉ ጀርመናዊትዋ ሳንድራ ኹለር፤ ጎልደን ግሎብ ባለፈዉ ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ባካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት "Killers of the Flower Moon" በተባለዉ ፊልም ላይ በተጫወተችው ሚና አሜሪካዊቷ ሊሊ ግላድስቶን ተሸንፋለች። ”

ሳንድራ ኹለር: በአዉሮጳ የፊልም ሽልማት ላይ 2023
ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ ምስል Christoph Soeder/dpa/picture alliance

ይሁን እና ጎልደን ግሎብስ ሽልማት ከመካሄዱ ቀደም ብሎ  ጀርመናዊትዋ ሳንድራ የአውሮጳ ፊልም ሽልማት ላይ ኮከብ ተሸላሚ ነበረች።  

ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በርሊን ላይ በተካሄደዉ የአውሮጳ የፊልም ሽልማት ላይ፤ ሳንድራ ኹለር በምርጥ መሪ  ተዋናይ ዘርፍ ሽልማትን ተቀብላለች። ሽልማትዋን እንድትወስድ ወደ መድረክ ስትጠራ፤ በአዳራሹ የነበረዉን ህዝብ ለዓለም ሰላም በፀጥታ  መልክት እንዲያስተላልፍ ለሰላም እንዲቆም ጠይቃ ነበር።

"በሰላም መስራት በመቻሌ እድለኛ ነኝ። እናንተም በሰላም መስራት በመቻላችሁ እድለኛ ናችሁ። ግን ብዙ ሰዎች በሰላም መኖር አይችሉም ወይም በሰላም መኖር አልቻሉም! ያ ነው እና አብረን ማሳካት ያለብን!"

"Anatomy of a Fall"  በጀርመንኛዉ «Anatomie eines Falles» የተባለዉ ጀርመናዊትዋ ተዋናይት የምትጫወትበት ፊልም

ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ
ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ ምስል C Flanigan/imageSPACE via ZUMA Press Wire/picture alliance

በፈረንሳዩ የፊልም ሽልማት መድረክ አሸንፋለች። ባለፈዉ ታህሳስ ወር ጀርመናዊትዋ የፊልም ተዋናይ ሳንድራ ሁለር፤  "Anatomy of a Fall " እና "The Zone of Interest" በተባሉት ፊልሞች ዉስጥ ላሳየችዉ ብዙ የሞያ ብቃት በአሜሪካ የሎስ አንጀለስ ፊልም ተቺዎች ማህበር (LAFCA) ሽልማትን ተቀብላለች።    

 የትያትር መሰረትዋ ምስራቃዊ ጀርመን ነዉ

ታዋቂዋ ጀርመናዊት የፊልም ተዋናይት ሳንድራ ኹለር እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር ሚያዝያ 30 ቀን 1978ዓ.ም በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን፤ ቱሪንጂያ ግዛት ፍሪድሪሽሮዳ በተባለች አነስተኛ ገጠራማ ከተማ ተወለደች። በአደገችባት በዚህ ከተማ የጀመረችዉ የትያትር ትምህርት እና በትምህርት ቤት የምታሳያቸዉ የትያትር ትወና ብቃት ብሎም ያላት የትያትር ፍቅር ቆየትብሎ  ሳንድራን ወደ በርሊን እንድትመጣ መንገድ ከፈቶላታል። ሳንድራ ወደ በርሊን መጥታ በታዋቂው ኧርነስት ቡሽ የትያትር ድራማ አካዳሚ ማመልከቻ አስገብታ ተቀባይነት ስታገኝ የ17 ዓመት ልጅ ነበረች።

ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ
ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ ምስል JU Bochum

በርሊን የሚገኘዉን ኧርነስት ቡሽ የትያትር ድራማ አካዳሚን የተቀላቀለችዉ ወጣትዋ የትያትር ባለሞያ በጀርመን የቲያትር ዓለም አናት ላይ ለመዉጣት የነበራት ጉልበት እና የትያትር ፍቅር በጣም ፈጣን እንደነበር ይነገርላታል።  እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 2003፣ ከድራማ ትምህርት ቤቱ  በተመረቀችበት ዓመት “ቲያትር ዛሬ” የተሰኘ የተችዎች ጥያቄ መዘርዝርን የሚያወጣዉ  የጀርመን መጽሔት ባደረገው የዳሰሳ ሳንድራ ኹለር ምርጥ ወጣት ተዋናይት ተብላ ተመርጣም ነበር።

ሳንድራ፤ ከትያትር አካዳሚ ተመርቃ ከወጣች በኋላ ላይ ወደ ፊልም ሥራዉ ዓለም ቀይራ ስትገባ  ለቲያትር ያላት ፍቅር እና ሞያዊ ሥነ-ምግባር እስከዛሬ ታማኝ ሆና ዘልቃለች። በፊልም ትወና ሚናዎች ጎን ለጎን በየጊዜው ወደ ትያትር መድረክም ትመጣለች፤ የትያትር ዓለሙንም በስራዋ ትገነባለች። ወደ ትወና ስራ ከመግባትዋ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደነበረው ሁሉ “ቲያትር ዛሬ” የተሰኘ የተችዎች ጥያቄ መዘርዝርን የሚያወጣዉ  መጽሔት በጎርጎረሳዉያኑ  2010 ፣ 2013 ፣ 2019 እና በቅርቡ በ 2020 ዓመታት የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ተብላ ተሰይማለች።  

ሳንድራ ኹለር በተለያዩ የፊልም ገፀ-ባህርያት

ሳንድራ ኹለር ገና ከመጀመርያዉ መጀመርያ ላይ በተወነችበት ፊልም ላይ የተሰጣትን ገፀ-ባህሪ ጥሩ አድርጋ መጫወትዋን ብዙዎች ይመሰክሩላታል።  ሳንድራ ኹለር ጀርመናዊዉ የፊልም ዳይሬክተር እና መሪ በክርስቲያን ሽሚድ በተሰራዉ "ሪኪየም" በተሰኘዉ እና በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓመት በወጣዉ ፊልም ላይ አንዲት የሚጥል በሽታ ያለባት ወጣት ሴት ገፀ-ባህሪን በያዘችበት ፊልም ላይ ባሳየችዉ የትወና ብቃት በጀርመኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል በርሊናሌላይ ምርጥ ተዋናይት ተብላ የብር ድብን ተሸልሟለች። ሳንድራ ኹለር በመቀጠል ከአስር ዓመት በኋላ 2016 አባት እና ልጅ ታሪክን በሚያሳየዉ እና The Greatest Schnuck of በተሰኘዉ ፊልም  ፤ የለንደን የፊልም ተቺዎች ክበብ፣ የቶሮንቶ ፊልም ተቺዎች ማህበር እና የአሜሪካ ብሔራዊ የፊልም ተቺዎች ማህበር የኹለርን የዓመቱ ምርጥ ፊልም ተዋናይት ሲሉ አዉድሳዋታል።  በዚሁ ዓመት የአዉሮጳ የፊልም ማህበር ምርጥ ተዋናይት ሲል ሽልማቱን አበርክቶላታል።

ሳንድራ ኹለር: ዓለምአቀፍ እዉቅናን ያገኘችዉ ጀርመናዊት ተዋናይ
ሳንድራ ኹለር: ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ለኦስካር የታጨችበት ፊልም ላይምስል Neon/AP/picture alliance

"Anatomy of a Fall" እና "The Zone of Interest" የተሰኙት ሳንድራ ኹለር የተጫወተችባቸዉ ፊልሞች የተለያዩ ትረካዎችን የያዙ እና የሳንድራን ከፍተኛ የትወና ክህሎት ያንፀባረቁ ናቸዉ።  በጀርመናዊት ደራሲ የተፃፈዉ "Anatomie of a Fall" የተባለዉ ፊልም   ባለቤቷን ገድላ ሊሆን ይችላል የተባለች አንዲት፤ በፈረንሳይ አልፐን ተራሮች ላይ የምትኖት ሴት ጉዳይን የሚተርክ ነዉ። 

"The Zone of Interest" የተሰኘዉ ሌላዉ ሳንድራ ኹለር የተወነችበት ፊልም ታሪክ ቀመስ በተለይ ናዚ ሆሎኮስት የፈፀመበት የአዉሽቪትስ ማጎርያ ጣብያን እና ግፍን የሚተርክ ፊልም  ነዉ ። ይሁንና እና በፊልሙ ግፍ ግድያ እና ስቃይ የማይታይበት ይሁንና የአዉሽቪትስን የናዚ ጭፍጨፋን የሚተርክ ፊልም ነዉ። ፊልሙ ከጎርጎረሳዉያኑ 1940 እስከ 1943 የናዚ ጦር በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በግፍ በጨፈጨፈበት በአዉሽቪትዝ ማጉርያ ጣብያ እና በማጊርያ ካምፑ አዛዥ እና ቤተሰባቸዉ ዙርያ ላይ ይተርካል። የማጎርያ ጣብያዉ አዛዥ እና ሚስታቸዉ ልጆቻቸዉን ወንዙ ዳር ለሽርሽር ሲሄዱ፣ ከልጆቻቸው ጋር በአትክልት ስፍራ ሲጫወቱ ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ሲበሉ ሲጠጡ ይተርካል። ከእይታ ባሻገር ግን የተኩስ ድምጽ፣ የሚጮሁ ውሾች እና የስቃይ ጩኸቶች ከሩቅ ይሰማሉ።  

ሳንድራ ኹለር: ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ለኦስካር የታጨችበት ፊልም ላይ 2024
ሳንድራ ኹለር: ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ለኦስካር የታጨችበት ፊልም ላይ 2024 ምስል A24/Everett Collection/picture alliance

በፊልሙ ኦሽዊትዝ-ቢርኬናው መታሰቢያ ሜትሮች ርቀት ላይ፣ የካምፑ አዛዥ ቤት ተገንብቶ ተዋናዮቹን በትዕይንታቸው ላይ ለመቅረጽ ካሜራዎች ተገጥመዉ፤ የማጎርያ ካምፑ አዛዥ ቤት በፊልሙ የ “ናዚ ሃውስ” ተብሎ ተገልጿል። ባለፈዉ እሁድ ጀርመናዊትዋ ሳንድራ ኹለር ወርቃማውን የኦስካር ሽልማት በእጅዋ ባታስገባም የሚሊዮኖችን ልብ በተወነችበት ፊልም አግኝታለች። እሷ የተወነችበት ፊልም " The Zone of Interest " የዓመቱ ምርጥ ፊልም በመባል ተሸላሚ ሆንዋል።

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረሥላሴ