1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2016

መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ታጥቀው ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉት ኃይሎች ጋር ለመነጋገር እና ለመወያየት ፍላጎት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሸኔም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂ ኃይሎች" መሳሪያቸውን አስቀምጠው በሰላም ውይይት እንዲያደርጉ አሁንም መንግሥት ፍላጎት አለው" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4c5pr
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

መንግሥት አሁንም ከታጣቂዎች ጋር ለመወያየት ፍላጎት አለው

መንግሥት አሁንም ከታጣቂዎች ጋር ለመወያየት ፍላጎት አለው 

መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ታጥቀው ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉት ኃይሎች ጋር ለመነጋገር  እና ለመወያየት ፍላጎት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ"ሸኔም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂ ኃይሎች" መሳሪያቸውን አስቀምጠው በሰላም ውይይት እንዲያደርጉ አሁንም መንግሥት ፍላጎት አለው" ብለዋል። 

"በጠብመንጃ እና በዐፈሙዝ ከእንግዲህ በኋላ ስልጣን መያዝ አይቻልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ሕግ ማስከበርን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፣ ሆኖም በዚህ ሂደት ለሰላም ፍላጎት ካለ መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቀዋል።  የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያን የሚጎዳ ፍላጎት እንደሌለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የሶማሊያ መንግሥትም ከኢትዮጵያ ጋግ የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም" ብለዋል። 
 

ከምክር ቤቱ የተነሱ ዐበይት ጥያቄዎች 
350 የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል በተባለበት የዛሬው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ 16 አባላት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አብዛኞቹ ጥያቄዎች የኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ የተመለከቱ ናቸው። መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር የጀመረው ድርድር ለምን ስኬታማ መሆን አልቻልም ? በአማራ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለማስተካከል የተወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? ችግሩ የተራዘም እንዳይሆን መንግሥት ምን አስቧል? አዲስ አበበን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ዜጎችን እየፈተነ ያለ ውንብድና ተበራክታል። በዚህም አንዳንድ የፀጥታ አካላት እየተሳተፉ መሆኑ ፣ እሥር መብዛቱ ተጠቅሶ "መንግሥት አምባገነን እየሆነ ነው" የሚለል አቤቱታ ስለመኖሩ ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሶማሊላንድ የሀገርነት ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት መቋጫ ያላገኘ በመሆኑ ጉዳዩ "ኢትዮጵያን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ"  በማስገባቱ ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት ምን አይነት ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እየተሰራ ነው ? የሕዳሴ ግድብን የሦስትዮሽ ድርድር አለመሳካት ተከትሎ በግብጽ በኩል እየቀረበ ያለው ዛቻ የ"ብሔራዊ ደህንነት ሥጋት" ስለመሆኑ፣  ከፍተኛ ድርቅ ያስከተለው ሥጋት ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት የመሪነት ሚና ምን ደረጃ ላይ ነው ? የኢትዮጵያ የእዳ ጫና እና የመክፈል አቅም ፣ ሕገ ወጥ የፋይነንስ ፍስሰት መበራከት ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ እና በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ጋር ያለው ግንኙነት መፋዘዝ አለ የሉት በምክር ቤቱ አባላት የቀረቡ ዋና ዋና ጥያቄዎች ናቸው።
የፖለቲካ ፍላጎት የማሳኪያ ስልት እና ልምምዱ በጠብመንጃ አፈሙዝ መሆኑ እና የችግር መፍቻ መንገዱ ውይይት አለመሆኑ የሰላምና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምክር ቤቱ አባላት ቢያነሱ ይሻል የነበረው ድርድር ለምን አልተሳካም ሳይሆን "ከጦርነት ምን አተረፍን" የሚለው እንደነበር ገልፀዋል።

እዚህ ተቀምጦ የታጣቂዎችን መምጣት የሚጠብቅ አለ

"ግለሰቦችን ማገት፣ መኪና ማቃጠል ፣ ልማትን ማደናቀፍ" ሥራው ሆኗል ያሉት ኦነግ ሸኔ አስመራ ላይ በምን ተስማምቶ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባም ዘርዝረዋል። "ኦነግን ወክለው አስመራ ላይ ከመንግሥት ጋር ከተወያዩት አብዛኞቹ አዲስ አበባ ላይ ናቸው"፣ የተወሰኑትም ሥልጣን ተጋርተዋል። በሚል ከኦነግ ጋር የተለየ ድርድር እንዳልነበር ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚህ ሆኖ ታጣቂዎችን የመጠበቅ አዝማሚያ ስለመኖሩም ጠቅሰው ያንን የማይጨበጥ ተስፋ ብለውታል። "እዚህ ተቀምጠው ከሸኔም ይሁን በሌሎች አማፂያን ይመጣሉ የሚል "የማይጨበጥ ተስፋ የሚጠብቁ አሉ" በማለት "በሞኝነት የመጠበቅ" ያሉትን ተስፋ እንዲወገድ አሳስበዋል። "በጠብምንጃ ፣ በአፈሙዝ ከእንግዲህ በኋላ ስልጣን መያዝ አይቻልም"። ብለዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ ምስል Solomon Muche/DW


መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር የመነጋገር ፍላጎት አሁንም አለው

አማራ ክልል የልማት ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እና የወሰን ጥያቄዎች መኖራቸውን የግለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄው በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ታይቶ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኝ ፣ የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው የወሰን ጥያቄዎች በሕዝበ ውሳኔ በሰላማዊ ውይይት የሚፈታ መሆኑን ገልፀዋል። "አንስተን የምናቀያይረው ጉዳይ አይደለም፣ በሪፈረንደም ሕዝቡ ወደፈለገው ይቀላቀል" የሚል ነው ውሳኔው ብለዋል።  የታጠቁ ኃይሎች አሁንም ለውይይት እንዲቀርቡ  የመንግሥታቸው ፍላጎት መሆኑንም ገልፀዋል። "ሸኔም  ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂ ኃይሎች መሳሪያቸውን አስቀምጠው በሰላም ውይይት እንዲያደርጉ አሁንም መንግሥት ፍላጎት አለው" ብለዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰጡት ማብራርያ ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምም፣ ችግርም  አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉም በሚዛኑ እንዲታይ ጠይቀዋል።
"መንግሥት ወደ አምባገነንነት እየተለወጠ ነው" የሚለውንም ከዴሞክራሲ አተገባበር የመነጨ በሚል ውድቅ አድርገውታል። ድርቅ የነበረ ችግር መሆኑን አስታውሰው ድርቅን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ማዋል ተገቢ አለመሆኑንም አብራርተዋል። 
 

የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያን የሚጎዳ ፍላጎት የለውም

ኢትዮጵያ ሶማሊያን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም የመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታዊ ሙስና አለመኖሩን፣ ገንዘብ የሚያሸሽ መንግሥት እንደሌለ አብርልርተዋል። መንግሥታቸው 9.9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈሉን እና ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘም የሦስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አብራርተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ