1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውሉ ያልታወቀው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ

ሰኞ፣ መስከረም 11 2013

የኢትዮጵያ ስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ አንድ ጊዜ ሀገሪቱ በገጠማት የፖለቲካ ቀውስ፣ በሌላ በኩል በአለም አቀፉ የኮሮና ተኅዋሲ ስጋት ሳቢያ ጊዜው ይህ ተብሎ ባልታወቀ ሁኔታ ተራዝሟል። ከሰሞኑም የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ስርጭት ለመግታት የተሻለ መረጃ መኖሩን በመጥቀስ ምርጫ ማከናወን እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳውቀዋል።

https://p.dw.com/p/3inQ3
Äthiopien Wahlkommission
ምስል NEBE

ውሉ ያልታወቀው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ

ስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ አንድ ጊዜ ሀገሪቱ በገጠማት የፖለቲካ ቀውስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአለም አቀፉ የኮሮና ተኅዋሲ ስጋት ለዚህ ተብሎ ላልታወቀ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል። 
2012 ዓ.ም መጨረሻ ተካሂዶ መስከረም 30/ 2013ዓ.ም ከመድረሱ በፊት የስልጣን ርክክብ ለምክር ቤቶች ማድረግ የማይቻልበትን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ምርጫውን ማካሄድ አልችልም ያለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ለፌደሬሽን ምክር ቤትም ተመርቶ ፣ ፌደሬሽን ምክር ቤትም የሕገ መንግስት ትርጉም ጠይቆ የሁለቱን ምክር ቤቶችና የክልል ምክር ቤቶችን እንዲሁም የአስፈፃሚውን አካል ሥልጣን አራዝሞታል።
የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ግን ይህንን ውሳኔ ሕገ ወጥ በማለት መንግሥት ከመስከረም ሰላሣ በኋላ ሕጋዊ መሰረትም ሆነ ቅቡልነት አይኖረውም በሚል አቋም ፀንተው ተከራክረዋል። የሽግግር መንግሥት እንዲዋቀርም ተጠይቆ ነበር ። በሌላ በኩል ባለፈው አመት የፀደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በፓርቲዎችና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ፍጥጫን ፈጥሮ ፓርቲዎቹ በአዋጁ እንዲካተቱ ያስገባናቸው ዝርዝር ሀሳቦች ሳይካተቱ ሕግ ሆኗል፣ በመሆኑም ቦርዱ ከወዲሁ የገለልተኝነት ችግር ውስጥ ገብቷል በማለት የሀሳብ ፍጭት ሲያደርጉ ነበር።
በዚህ መሃል ደግሞ በሀገሪቱ ታሪክ አንድ ክልል ብቻ ክልላዊ ምርጫ ያደረገበት የጳጉሜን አራቱ የትግራይ ክልል ምርጫ ተካሄደ። ምንም እንኳን የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትግር ዐቢይ አህመድ ምርጫው እንደተደረገ የማይቆጠርና ተቀባይነት የሌለው ቢሉትም ክልሉ ምርጫውን ያከናወነበትና በፌደራልና በክልሉ መንግሥት መካከል የነበረውን ቅራኔም ይበልጥ ያከረረ ክስተት ሆኖ አልፋል። ሀገር አቀፍ ምርጫው ከወራቶች በፊት ሲራዘም ምርጫው መች እንደሚከናወን ሲያስቀምጥ ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑ ከተረጋገጠ በሗላ እና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ አመት ባለ ጊዜ ይላል። ከሰሞኑም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ወረርሽኙ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል እና አሁን ላይ የተኅዋሲውን ስርጭት ለመግታት የተሻለ መረጃ መኖሩን በመጥቀስ ምርጫ ማከናወን እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳውቀዋል።
ከጅምሩ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሲጠይቅ የነበረው አብሮነት ይህንን የጤና ሚኒስትራን እቅድ የመንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ እንጅ በእርግጥም የተኅዋሲው ስፋት እና የስርጭት መጠን ተፈትሾ የቀረበ እንዳልሆነ አስታውቋል።
ይልቁንም ለብሔራዊ መግባባት የተጀመሩ ሁሉን ያሳተፉ ውይይቶች መካሄድና ከውይይቱ በመነሳት ምን መደረግ እንዳለበት ሊወሰን ይገባል ነው የሚለው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ደግሞ በመጀመርያ ደረጃ ጤና ሚኒስቴር ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ የሚለው ጉዳይ ላይ ሳይሆን ተኅዋሲው ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብቻ ነው ለምክር ቤቱ ሀሳብ ማቅረብ ያለበት ይላሉ። በሌላም በኩል ምርጫው ይካሄድ ሲል ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄደው ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋትነቱ ሲያበቃ ነው የሚለውን ድንጋጌውን የሚቃረን እንደሆነ ይገልፃሉ።
አዋጁ ሲታወጅ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱን የምርጫ አፈፃፀም ዝግጁነት የሚጨምሩ ተግባራትን ሲያከናውን እንዲቆይ ተብሎም ነበር ። ቦርዱም ይህንን የቁሳቁስ ግዥ እና አቅርቦት ብሎም የምርጫ ሂደት አስተዳደር ላይ ዋና ዋና ተግባራትን ሲከውን መክረሙን፣ በቦርዱ የተመዘገቡ ፓርቲዎችን ሕጋዊ መስፈርት የመመርመር ሥራ ሲያከናውን እንደቆየ፣ 27 የፓለቲካ ፓርቲዎችንም ከምዝገባ ዝርዝሩ መሰረዙን ገልፃል። ስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ መች እንደሚከናወን ፣ በምን ሁኔታ ሊፈፀም እንደሚችል የፓርላማውን ውሳኔ ይጠብቃል።


ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ