ወጣቱ የፊልም ሰው | ባህል | DW | 07.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ወጣቱ የፊልም ሰው

በአዳጊው የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ አብዛኛውን ስራ የሚያከናውኑት ወጣቶች ናቸው፡፡ በዘርፉ ካለው የሰው ኃይል እና የልምድ እጥረት የተነሳም በርካታ ዘርፎችን ደራርበው ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹ በሚሰሯቸው ፊልሞች እየተማሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰውመሆን ይስማው አንዱ ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:48 ደቂቃ

ሰውመሆን በ16 ፊልሞች አሻራውን አሳርፏል

ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ሰውመሆን ይስማው በአስራ ስድስት የኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ አሻራውን ያሳረፈ ነው፡፡ የዘመን ተጋሪው ወጣቱ የፊልም ዳይሬክተር ዳዊት ተስፋዬ “ስለሰው መሆን ሲወራ” መረሳት የሌለበትን ይጠቁማል፡፡

“ሰውመሆን ሲኒማቶግራፈርም፣ ዳይሬክተርም፣ ስክሪን ፕሌይ ጸሀፊም ስለሆነ ስለሰውመሆን ስናወራ ስለየትኛው እንደሆነ ማወቅ ወሳኝ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የራሱ ቀለም ያለው፣ የሰራውን ስራ አይተህ  የሰውመሆን ስራ ይመስላሉ የሚባሉ ስራዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ በሰኒማቶግራፊም፣ በዳይሬክቲንግም ያ ነገር አለው ብዬ አስባለሁ” ይላል ዳዊት፡፡

የስነ መቼት እና የሜካፕ ባለሙያው ተስፋዬ ወንድማገኝ የሰውመሆን የቅርብ ጓደኛ ነው፡፡ የሰውመሆን የቅርብ ሰዎች እንደሚጠሩት ጓደኛውን “ሶሚክ” ነው የሚለው፡፡

“እውነት ለመናገር ሰውመሆን 24 ሰዓት ስለፊልም የሚያወራ ፊልም የሚወድ ልጅ ብዙ ቮካብለሪ ያለው ልጅ ነው፡፡ ሶሚክ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳለፋቸው ጊዜያቶች በጠቅላላ ቀጥታ ወደፊልም ስራ እያንደረደሩ ነው ያመጡት፡፡ ሁልጊዜ ስለአባቱ፣ እናቱ፣ ስለሰፈሩ ልጆች እንዳለ ታሪካቸውን በሚያወራኝ ጊዜ በቃ ይሄ ልጅ ታሪክ ተናጋሪ እንዲሆን ተመርጧል ብዬ አስባለሁ፡፡ እርሱ ጋር ያለው የፊልም ፍቅር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነገር ነው” ይላል ተስፋዬ፡፡ 

ጎንደር ተወልዶ ያደገው ሰውመሆን “የነፍስ ጥሪው” ወደተባለለት የፊልም ሙያ እንደው በቀጥታ ዘው አላለም፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲቀላቀልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ ያጠናው “ፐርቼዚንግ” ነበር፡፡ ምንም እንኳ ትምህርቱ ንግድ ተኮር ቢሆንም ለዩኒቨርስቲ ትምህርቱ በአዲስ አበባ መቆየቱ ወደ ፊልም ስራ የሚሳብበትን አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡

ሰው መሆን ትምህርቱን የሚከታተልበት የንግድ ስራ ኮሌጅ የማደሪያ አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ አጎቱ ሻለቃ ተስፋዬ ይግረም ዘንድ እንዲያርፍ ይሆናል፡፡ ፎቶ አንሺ የሆኑትን አጎቱን ለመርዳት ከትምህርቱ ጎን እርሳቸው ፎቶ ቤት ያዘወትር ያዘ፡፡ ያኔ እንዳሆኑ ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ዲጂታል ፎቶ ካሜራዎች አልነበሩም እና በአናሎግ ካሜራዎች ሲሰራ ቆየ፡፡ “አንዳንድ ሰርጎች አነሳ ነበር፡፡ ሌላም ሌላም ስራዎች እየሰራሁ ከዚያ ቀስ ብሎ ከፎቶግራፍ ማንሳት ወደ ቪዲዮ መቅረጽ መጣ፡፡ ግን ምንድነው ከድሮም ጀምሮ ሲኒማ ላይ ለየት ያለ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ልጅ እያለሁ፣ ሁለተኛ ደረጃም ሆኜ ቪዲዮ ቤቶች አዘወትር ነበር፡፡ ሲኒማ ይሄ ታሪክ መንገር የሚባለው አካባቢ መንፈሴ ነበር፡፡ እና ቀስ እያለ ወደ ፊልም እያደገ መጣ” ይላል ያን ጊዜን ሲያስታውስ፡፡ ፡፡

የቪዲዮ ፊልሞችን ለሰፈር ተመልካች የሚያከራይበት የራሱ ሱቅ የነበረው ሰውመሆን የመጀመሪያ ፊልሙን ሊሰራ ሲነሳ ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ለመሞከር ተነሳ፡፡ ከርዕሱ ጀምሮ ወጣ ያለ የነበረው ይህ ፊልም የወቅቱ መነጋገሪያ ነበር፡፡ “862” የተሰኘ ስያሜ ስለሰጠው ስለዚህ ፊልሙ ሰውመሆን ሲገልጽ “ቅዥት የመሰለ” ይለዋል፡፡ “ለምንድነው ፊልም ሀ፣ ለ፣ሐ…ተብሎ የሚተረከው?፡፡ ለምን ከመጨረሻ አይጀምርም? የሚል ፍልስፍና የነበረው ፊልም ነው ይዤ የመጣሁት” ይላል ስለ መጀመሪያ ፊልሙ አካሄድ ሲናገር፡፡

“ታሪኩ ወደ ፊት እየሄደ ወደ ኋላ ይመጣል፡፡ በጊዜው አንዳንድ ልጆች የፈረንጅ ተጽእኖ ያለበት ታሪክ ነገራ ዘዴ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እኔ ደግሞ ከዚያ የተለየ ተቃራኒ የሆነ የእኛ ነው ብዬ ነበር የማምነው፡፡ ለምሳሌ ቢሊጮ የሚባል ገጸባህሪ ተረት ሲነግሩህ ‘ቢሊጮ ከዚያ ምንጣጥሊት እያባረረችው ሄደና እና ወንዝ ተሻገረ፤ ከዚያ እርሷ ወንዝ ወሰዳት’ ይሉህና ‘መጀመሪያማ እንደዚያ አይደለም፤ እንዴት ተሻገርሽ ብሎ ጠየቃት’ ይሉሃል፡፡ ይሄ ነው ቅርጹ፡፡ ሄደህ ታልፍና ተመልሰህ መጥተህ  ‘እንዴት እዚህ ደረሰ ?’ ስትል  ‘እንዲህ የሆነው በዚህ መንገድ ስለሄዱ ነው’ ብሎ በሚናገር መንገድ ነው ታሪኩን የተረኩት፡፡ እና ህይወት ራሱ ሁሌ ቀጥተኛ አይደለም፡፡ ዛሬ ቁጭ ብለን ነገን እናስባለን፡፡ ነገ ላይ ሆነን ከአራት፣ ከአምስት ቀናት በፊት ወይም ከዓመታት በፊት የሆነን ነገር ነጋችንን ተጽእኖ እንደሚያሳድርበት እናስባለን፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሲኒማ ለምን አንሰራም የሚል ሀሳብ ነበረኝ፡፡ ትንሽ ይለይ ነበር” ሲል አጀማመሩን ይተርካል፡፡

ለቀረጻ እንዲያመቸው አድርጎ የጻፈውን ይህን የመጀመሪያ ፊልሙን በወቅቱ ስም ላላቸው ተዋንያን እንዲተውኑለት ሲሰጣቸው በድፍረት ነበር፡፡ ጽሁፉን ያነበቡት ግሩም ኤርሚያስ፣ ዕንቁስላሴ አገኘሁ እና ይገረም ደጀኔን የመሳሰሉ ዕውቅ ተዋንያን በሀሳቡ ተስማምተው በፊልሙ ተሳተፉ፡፡ ተዋንያኑ “ሀሳቡን ወደውት፣ አምነውኝ ነው የሰሩት” ይላል ሰውመሆን፡፡ ሰማንያ ሺህ ብር ገደማ ከወጣበት ከዚህ ፊልም ግማሹ የተከፈለው ለዋናው ተዋናይ ግሩም ሲሆን ቀሪውን ሌሎቹ ተዋናዮች መከፋፈላቸውን ያስታውሳል፡፡ ፊልሙ አብዛኛው ቀረጻው በአንድ ቤት ውስጥ በመከናወኑም ብዙ ወጪ አልስወጣውም፡፡ “862” ሰውመሆን በመጀመሪያ ፊልሙ ሊያሳካ የሚያስበውን ግብም መትቶበታል፡፡

“ምን እላለሁ መሰለህ? የመጀመሪያ ስራህ ሁልጊዜ ወይ አነጋጋሪ መሆን አለበት ወይም ደግሞ ትልቅ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ፊልሙ በወጣ ጊዜ ሁለት ዓይነት ተመልካች ነበረው፡፡ አንዳንዶቹ ‘ይህን ፊልም ከምናይ ፒዛ ብንበላ ይሻላል’ ብለው ይወጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‘እንዴት አይነት የተለየ ፊልም ነው’ ብለው ወጡ፡፡ በዚህ ግርግር ውስጥ ይህ የሞከርኩት ነገር ዋጋ አግኝቶ፣ ሰዎችም እውቅና ሰጡት፡፡ የፎቶግራፍ እውቀቴም እየቀጠለ ሄዶ በደንብ ወደ ሲኒማው ገባሁ” ይላል በመጀመሪያ ፊልሙ ስላገኘው ምላሽ ሲያስረዳ፡፡ 

በራሱ ፊልም እጁን ያፍታታው ሰውመሆን በመቀጠል በቶም የፊልም ትምህርት ቤት ባለቤት በተሰራው “ፔንዱለም” በተሰኘ ፊልም በሲኒማቶግራፈርነት ተሳተፈ፡፡ አዳዲስ እና ያልተለመዱ ነገሮች ሁሌም መሞከር የሚወደው ሰውመሆን በዚህም ፊልም ከዚያ ቀደም በሌሎች ፊልም ሰሪዎች ያልተደፈረ ነገር አድርጓል፡፡ እስከዚያን ጊዜ በነበረው አሰራር ፊልም የሚቀረጸው በቪዲዮ ካሜራ አሊያም ለሲኒማ ተብሎ በተሰራ መቅረጫ ነበር፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በእጅ የሚንጠለጠሉትን የፎቶ ካሜራዎች ቪዲዮም እንዲቀርጹ አድርጎ አሻሻላቸው፡፡ እንዲህ አይነት ካሜራዎች ወደሀገራችን ቢዘልቁም ደፍሮ ለፊልም የሚጠቀምባቸው አልነበረም፡፡ ተስፋዬ ወንድማገኝ በዚያን ወቅት የነበራቸውን ሙከራ ያስረዳል፡፡

“ፔንዱለም የመጀመሪያው የ7D የፊልም ስራ ነው፡፡ 7D የሚባል ካሜራ ከመምጣቱ በፊት በኒከን D90 በሚባል ካሜራ እኔ እና ሶሚክ ከተማ እየዞርን እንቀርጻለን፡፡ ‘እንደአይን የሚያይ ነገር በደንብ እንዴት መስራት እንችላለን? ሌንስ የመጠቀም አቅማችንን እንዴት ነው [የምናዳብረው]’ እያልን በዚያ D90 ትንንሽ ነገሮች እንቀርጽ ነበር፡፡ ከዚያ 7D የሚባል ካሜራ ሲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ ነን ያመጣነው፡፡ ሶሚክ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ  ‘ፔንዱለም’  ላይ የቀረጸበት፡፡ እና ከብዙ ትግል በኋላ ነው ያመኑን፡፡ በትክክል በፎቶ ካሜራ እንደሚቀረጽ ማለት ነው” ይላል ተስፋዬ፡፡      

ሰውመሆን በፊልም ስራ ውስጥ መስመር ያስያዘኝ የሚለውን “የጸሃይ መውጫ ልጆች” ፊልምን ከመስራቱ በፊት ሲኒማቶግራፈርነቱን አጠናክሮ ቀጥሎበት ነበር፡፡ “ኦፕሬሽን አክሱም” የተሰኘ የትግርኛ ፊልም፣ ሄርሞን ሃይላይ ያዘጋጀችውን “ባላገሩ” እና እስካሁን ለዕይታ ያልበቃ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የተቀረጸ “ለአንድ ዲግሪ 360 ዲግሪ”ን በተከታታይ ቀረጸ፡፡ በመሃል “ይሉኝታ” በተሰኘው የሚካኤል ሚሊዮን ፊልም ላይ በረዳት አዘጋጅነት ተሳትፏል፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ቀረጻው በተከናወነው “የጸሃይ መውጫ ልጆች በዝግጅት (ዳይሬክቲንግ)፣ በፊልም ጽሁፍ እና የፊልም ቀረጻ ድርሻዎችን ጠቅሏል፡፡ ፊልሙን ፕሮዲዩስ ካደረጉ አምስት ሰዎችም አንዱ ነው፡፡

በቢኒያም ወርቁ የተጻፈው ይህ ፊልም ሰውመሆን እጅ ሲገባ በ28 ገጽ ነበር፡፡ ይህን አስፋፍቶ፣ ለፊልም በሚሆን መልኩ አደራጅቶ  በ70 ገጽ ለመጻፍ አንድ ዓመት ተኩል እንደወሰደበት ይናገራል፡፡ በፊልሙ ላይ ዋና ተዋናይ የነበረው ግሩም ኤርሚያስም አግዞታል፡፡ ሰውመሆን “በደንብ ተፈትኜበታለሁ” ስለሚለው “የጸሃይ መውጫ ልጆች” ማብራሪያ አለው፡፡

“ይሄ የመንገድ ጉዞ ፊልም ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነበር ጥንቃቄ ይፈልግ ነበር፡፡ ‘የጸሃይ መውጫ ልጆች’ የቀረጻ ሂደቱ ከባድ ነበር፡፡ ምን መሰለህ? ‘የጸሃይ መውጫ ልጆች’ የወጣበት ገንዘብ እና የፈጀው ጉልበት የሚነጻጸር አይደለም፡፡ በገንዘብ ብቻ ለ‘ጸሃይ መውጫ ልጆች’ የወጣው 150 ሺህ ብር ነው፡፡ ከዚያ ግን ግሩም ኤርሚያስ፣ ብርቱካን በፍቃዱ፣ ሰለሞን ቦጋለ አልተከፈላቸውም፡፡  ማንም ባለሙያ ገንዘብ አልተከፈለውም፡፡ እብደት ነበር፡፡ ዝም ብለን ወጥተን ነበር ያበድነው፡፡ መንገድ ላይ በጣም ብዙ አስቂኝ፣ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመውናል፡፡ አፋር በረሃ ውስጥ ቀርጸናል፡፡ አፋር በረሃ ውስጥ ስንቀርፅ አይሱዙ መኪና ነበር ተከራይተን የሄድነው፡፡ አይሱዙ ላይ ‘ግሪን ስክሪን’ እያነጠፍን ነበር የምናድረው፡፡ ‘እባብ፣ ጊንጥ አለ’ እየተባልን እንደዚህ ነበር የሰራነው ፊልሙን፡፡ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ለሁላችንም ትልቅ መሰረት፣ ትልቅ ትምህርት ጥሎ ያለፈ ሲኒማ ነው” ይላል፡፡     

ሰውመሆን በዚህ ፊልም የጀመራቸውን አዳዲስ ነገሮችን የመሞከር ሂደት “ዓለሜ” በተባለው ቀጣይ ፊልሙ ላይም አሳይቷል፡፡ ስለሰውመሆን ሞካሪነት ዳይሬክተሩ ዳዊትም መስካሪ ነው፡፡

“ሲኒማቶግራፊ ላይ ስንመጣ ብዙ ጊዜ በአቀራረጽ፣ በተለይ ደግሞ በመብራት እና ብርሃን አጠቃቀም የራሱን ዘይቤ የፈጠረ ሲኒማቶግራፈር ነው ማለት እንችላለን፡፡ በዳይሬክተርነት እንደእኔ ሰውመሆን እየተጓዘ ያለ ዳይሬክተር ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ብዙ ነገሮችን እየሞከረ፣ እርሱ የሚወደውን እና የሚያምንበትን አይነት ነገር ላይ ለመድረስ እየሞከረ ያለ ዳይሬክተር ነው፡፡ ‘የጸሃይ መውጫ ልጆች’ን ምሳሌ ብናደርግ፣ ሌሎቹንም ፊልሞቹንም ብናያቸው ተመሳሳይ ሙከራዎች ውስጥ ያልሆኑ በጣም ብዙ አይነት ሙከራዎች እና ሙከራ ብቻ ሳይሆን የሲኒማ ስኬቶችን ጭምር የሚያገኝ ዳይሬክተር ነው፡፡

‘የጸሃይ መውጫ ልጆች’ ፣ ‘ዓለሜ’ን ካየኸው ሌሎችም ፊልሞቹን የሚወጡትን፣ የወጡትን ፊልሞችም ካየኻቸው አንደኛ ታሪኩ የሚፈልገውን ነገር በመገንዘብ አዲስ ነገርን ለመፍጠር ይሞክራል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከታሪኩም ውጭ እርሱ እንደፊልም ሰሪ የራሱን ቀለም እና አሻራ [ያሳርፋል]፡፡ ምናልባት እርሱ ቀለም እና አሻራ ለማሳረፍ የሚያደርገው ሙከራ ላይሆን ይችላል ግን የሚያደርገው ጥረት አሻራውን እዲያሳርፍ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፣ ‘ዓለሜ’ን ከወሰድኸው በጣም ቀዝቀዝ ባለ ፍጥነት፣ በጣም ጥልቅ የሆነ ታሪክን ለመንገር የሚሞከርበት ፊልም ነው፡፡ ‘የጸሃይ መውጫ ልጆች’ን ደግሞ ካየኸው ፈጠን ባለ ፍጥነት፣ በጣም የሚያስገርም፣ በስሜት ልብ የሚያንጠለጥል አድርጎ ለመንገር የሚሞከርበት ነው፡፡ ለሁለቱም እንደሲኒማቶግራፈርም፣ እንደዳይሬክተርም ሁለቱም ላይ የሞከራቸውን እና ያደረጋቸውን ነገሮች ስታይ የተለያዩ ግን ለየፊልሞቹ በጣም ተገቢ የሆኑ ነገሮችን የሞከረው” ይላል ዳዊት ስለሰውመሆን ሙከራዎች እና ጠንካራ ጎኖች ሲተነትን፡፡      

“ዓለሜ” ሰውመሆን በሀገር አቀፍ የፊልም ውድድሮች ሽልማቶችን የሰበሰበት ነው፡፡ እርሱም ራሱ “የእኔ ምርጥ ፊልም” ነው ይላል፡፡ “ደግሜ እሰራው ይሆን ብዬ ሁሉ የምጠራጠረው ነው” ሲልም ለፊልሙ ያለውን መውደድ በፈገግታ ታጅቦ ያስረዳል፡፡

“ከሰኒማቶግራፊ አልፌ ማዘጋጀት አካባቢ ስመጣ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት እፈልጋለሁ፡፡ ወደዚያ ታሪክ የሚወስደኝ፡፡ ‘ዓለሜ’ መጀመሪያ ተጽፎ ሲመጣ ‘ኮሜዲ’ የሚመስል ዘውግ ነበረው፡፡ ፕሮዲዩሰሯ ዳግማዊት ክፍሌ ትባላለች፡፡ ይዛልኝ ስትመጣ መጀመሪያ የእኔ ጥያቄ  ‘እንደፈለግሁት እንድጽፈው ትፈቅጅልኛለሽ ወይ?’ [የሚል ነበር] ‘ከፈቀድሽልኝ ልስራው’ አልኳት፡፡ እንደፈልግኹት እንዳደርገው ፈቀደችልኝ፡፡ ሰለሞን ቦጋለ ነበር በጊዜው፡፡ ‘ዓለሜ’ ላይ ምንድን ነው ያደረግሁት ? ‘ዓለሜ’ እንደሀሳብ ትንሳኤ ላይ ነው የተሰራው፡፡ አውነታን ያለመቀበል ሀሳብም አለበት፡፡ ግን ዋናው ሃሳቡ ትንሳኤ ነው፡፡  የሰው ልጅ በጣም የሚወደውን፣ የሚያፈቅረውን ሰው ድንገት በሞት ሊያጣ ይችላል፡፡ ከዚያ ምንድነው የሚሆነው? ምንድነው መሰለህ? ‘በጣም የምትወደውን ሰው ህልም በመኖር ሰውየውን ማኖር ትችላለህ፡፡ እድሜ ልክ ሊኖሩ ይችላሉ’  የሚል ሀሳብ ያለው ሀሳብ ያለው፣ ትንሽ ጥልቅ ፊልም ነው፡፡ አንድ ሰው ከሁለት አሻንጉሊቶች ጋር የሚጫወተው ፊልም ነው፡፡ እና ትልቁ ተግዳሮት የነበረው አንድን ተዋናይ ከሁለት አሻንጉሊት ጋር ሙሉ ሰዓት ከተመልካች ጋር ግብብ ፈጥሮ እንዲቆይ ማድረጉ ነው፡፡

ሌላ ‘ዓለሜ’ ላይ ትልቅ ሙከራ ያደረግኹት የፊልም ስራውን ነው፡፡ ፊልም ስራው አሁንም በጣም የምኮራበት ነው፡፡ በ5D ነው የተቀረጸው፣ ካሜራው ትንሽ ፎርማት ነው ግን በጣም ኃይለኛ Computer Generated Images (CGI) የሚሰራ ዳንኤል ታምራት የሚባል ልጅ እና ሌላኛው Production Designer ተስፋዬ ወንድማገኘሁ የሁለቱ ግብዓት ፊልሙን ለምናቤ የቀረበ [አድርጎታል]፡፡ ‘እኔ በምናቤ የምስለውን ነገር ቀርጩ አላውቅም’ እላለሁ፡፡ ‘ዓለሜ’ ግን ለምናቤ የቀረበ ፊልም ነው፡፡ ያሰብኩትን ነገር በትክክል ለማሳካት የተጠጋሁበት ነበር፡፡ በእነዚህ ሁለት ልጆች እገዛ ወደዚያ፣ ወደ ህልሜ ቀርቧል ብዬ አምናለሁ” ይላል ሰውመሆን፡፡  

የወጣቱ ፊልም ሰሪ ስራ ከሀገር ተሻግሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው በቅርቡ በሰራው “እውር አሞራ ቀላቢ” በተሰኘው ፊልሙ ነው፡፡ ዘካሪያስ ጥበቡ በተባለ ኢትዮጵያዊ የስደት እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ይህ ፊልም በፌስቲቫሎች ሽልማቶች እና እውቅናዎች አግኝቷል፡፡ ባለፈው ግንቦት በተካሄደው የኒውዮርክ አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የፌስቲቫሉ ዋና ፊልም ሆኖ ተመርጧል፡፡ በዳላስ ኢንተርናሽናል አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ሽልማት አግኝቷል፡፡ ከአዲ ዳዕሮ-አዲግራት እስከ ገላባት ሱዳን፣ ከመተማ እስከ ጅቡቲ ድንበር፣ ከአፋር እስከ ትግራይ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር ተዘዋውሮ የተቀረጸው ይህ ፊልም በመጪው መስከረም ወር በኢትዮጵያ መታየት ይጀምራል ተብሏል፡፡ ወጣቱ የፊልም ባለሙያ በዚህኛው ፊልም ከሙከራዎች አልተገታም፡፡

“በ‘እውር አሞራ ቀላቢ’ም በተወሰነ መልኩ ሙከራ አድርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የዶክመንተሪ ድራማ ይዘት ያለው ስራ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? እውነተኛ ድርጊቶቹን እንደገና መልሰን ሰርተናል፡፡ ተዋንያን ስንመርጥም በህይወት የሌሉትን ሰዎች ብቻ ነው [ተተኪ ተዋናይ] ያደረግነው፡፡ በህይወት ያሉትን ራሳቸው ባለታሪኮቹን ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ ድረስ እየሄድን ነው የቀረጽነው፡፡ ዋናው ታሪክ ከስደት በኋላ ቤተሰቦቹን፣ አጎቱን እና የአጎቱን ልጆች ለማግኘት ስለሚመጣ ልጅ ነው፡፡ ወደ አጎቱ ልጆች ቤት የሚሄደውም በእውን ነው የቀረጽነው፡፡ ሲገናኙ፣ እናቱ እና አባቱ መቃብር ሄዶ የሚያይበት፣ ለቅሶ የሚደርስበት ገቢሮች አሉ፡፡ እነርሱ የእውነት ነው የተቀረጹት፡፡ ከእዚያ ደግሞ ከእርሱ ተነስተን ጉዞውን፣ የተሰደደውን፣ የሄደውን መንገድ፣ የተሰቃየውን ስቃይ እርሱን ደግሞ በድራማ አድርገን ነው የሰራነው፡፡ ሁለቱን ቀላቅለን ነው ፊልም ያደረግነው፡፡ የሄኛው ሌላ ዓይነት መንገድ ነው” ይላል ሽልማት ስላጎናፈው ፊልም ለየት ያለ ዘውግ ሲያብራራ፡፡   

“ከፊልም ፊልም እየተማርኩ ነው” የሚለው ሰውመሆን የሁለት ቀጣይ ስራዎችን ቀረጻ አጠናቅቋል፡፡ ባህር ዳር ላይ የተቀረጸው አንደኛው ፊልሙ በተለይ እስከዛሬ ከሰራኋቸው ሁሉ ሃሳቦቼን በደንብ የገለጽኩበት ነው ይላል፡፡ በፊልም ስራ ስለሚከተለው ፍልስፍና  ሲጠየቅ በረጅሙ ተነፍሶ፣ የፊልም ባለሙያው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከዚህ ቀደም የተናገሩትን አጣቅሶ ተከታዩን ምላሽ ይሰጣል፡፡

“ምንድነው መሰለህ? ፍልስፍና ይሁን፣ ምን ይሁን አላውቅም ብቻ ጋሽ ኃይሌ በጣም ደጋግሞ ‘የሰው ልጅ በጣም የሚውቀውን ነገር መስራት አለበት’ ይላል፡፡ እኔም ደጋግሜ ስሰማው በጣም እየገባኝ የመጣው ነገር እርሱ ነው፡፡ በጣም የምታውቀውን ነገር ስትሰራ ኃይለኛ ይሆናል፡፡ አለም ላይ በደንብ መታየት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በደንብም የሰው ልጅ የሚያውቀውን ነገር መስራት አለበት፡፡ በጣም ብዙ ነገር አለን፡፡ አንዳንድ ልጆች ይመጣሉ የፊልም ጽሁፍ ይዘው ይመጣሉ፡፡ የሆነውን ገቢር ስታነበው የሆነ ፊልም ይመስልሃል፣ ሌላኛውን ገቢር ስታነበው ሌላ ፊልም ይመስልሃል፡፡ ከዚያ እስኪ የ‘እናትህን ታሪክ ንገረኝ፣ እናትህ እንዴት ናቸው?፣ አባትህ እና እናትህ እንዴት ተገናኙ ስትለው ጉደኛ ታሪክ ይነግርሃል፡፡ ‘እና ምን ሆነ ነው ከዚህ ጋር የምትላፋው፣ ምን ይሰራልሃል ይሄ፣ የምትነግረኝ ነገር እኮ በጣም የሚገርም ነው’ ስትለው አፉን ይዞ ልጁ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ በትክክል የሰው ልጅ የሚያውቀውን ነገር መስራት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ነው ለእኔ ሲኒማ ውስጥ ያለኝ ሀሳብ ፡፡ እና የእውነት መነሳሳት ያስፈልገዋል፡፡ በቃ! ከነፍስህ፣ ከልብህ ጋር ሲገናኝ ታገኘዋለህ፡፡ የእውነት ከውስጥህ ሲወጣ ነው በትክክል የሚሰራው ብዬ አምናለሁ” ሲል እምነቱን ያጋራል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ    

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic