1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቱ መደመጥ ይሻል

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2015

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለፈው ወር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የተካሄደው የሰላም ስምምነትን እንዴት ያዩታል? ሶስት ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ምልከታ ለዶይቸ ቬለ DW አጋርተዋል።

https://p.dw.com/p/4KjYK
ቸርነት ሀሪፎ
ቸርነት ሀሪፎ: በዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እና የማህበራዊ መብት ተሟጋች  የሆነው ምስል Privat

ባለፈው ወር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የተካሄደው የሰላም ስምምነት የተለመደ አሰራር ተስተውሎበታል። በኢትዮጵያ ዋና ዋና የሚባሉ ውጣ ውረዶች የሚመሩት በአዛውንቱ ፖለቲከኛ ትውልድ ነው። ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው የተባለው ተቋም እንደሚለው በኢትዮጵያ ካለው የህዝብ ቁጥር አማካይ እድሜያቸው 20 ዓመት ገደማ የሆኑ ወጣቶች ሀሳባቸው የሚደመጥበት ተጨማሪ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ይፈልጋሉ። ይህንኑ በተመለከተ በውጪ አገራት የሚኖሩ ሶስት ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ የራሳቸውን ምልከታ ለዶይቸ ቬለ DW አጋርተዋል።

«እኔ እንደማስበው የሰላም ስምምነቱ  ባለ ድርሻ አካላትን በሙሉ ያካተተ አይደለም» ይላል በዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እና የማህበራዊ መብት ተሟጋች  የሆነው ቸርነት ሀሪፎ ፤ «በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የሁሉም ማህበረሰብ ተወካዮች መካተት ነበረባቸው» ሲል ከስምምነቱ የታዘበውን ድክመትም ይጠቁማል። ቸርነት የሰላም ስምምነቱን ጅምር ቢደግፍም፣ በውስጡ አሁንም መፍትሄ የሚሹ ውስብስብ ነገሮች እንዳሉ ይሰማዋል።

«በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም  ስለ ኤርትራ ወታደሮች በስምምነቱ ላይ  ምንም የተባለ ነገር የለም»  ይላል የትግራይ ተወላጅ የሆነው ቸርነት።  የሰላም ስምምነቱ ሂደት ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ ግራ መጋባቱን የሚገልፀው ይኼው ወጣት « የሰላም ስምምነቱን እደግፋለሁ ነገር ግን ተፈጻሚነቱ ላይ ጥርጣሬ አለኝ ። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በብዙ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚታዩ ግጭቶች ጋር  በቀጥታ የተቆራኘ በመሆኑ የሰላሙ ሂደት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መሆን ነበረበት" ብሏል።
ቸርነት በተጨማሪም የኢትዮጵያ  መንግሥትም ሆነ የትግራይ ተወካዮች በሁሉም ወገኖች መካከል እውነተኛ ዕርቅ መደረግ እንዳለበት አስረግጦ ይናገራል።
«በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ  ኢትዮጵያውያን በሰላም እና በብልጽግና መኖር ብቻ ነው የሚፈልጉት እንጂ፤ ከምንከራከርባቸው አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት  የላቸውም» ። ቸርነት አክሎም ሀገሪቱ  ከብሔር ይልቅ ሰብዓዊነትን የሚያስቀድም መሪ እንደሚያስፈልጋት ይናገራል። « ያለፉትን ቅራኔዎች የሚያርቅ  መሪ እንፈልጋለን ። ነገር ግን ቀድመው የነበሩት ውጥረቶች በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስተዳደር ስር ይበልጥ ተባባሱ እንጂ አልቀነሱም።»

ቸርነት ሀሪፎ
ቸርነት ሀሪፎ : በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በማውገዝ በዋሽንግተን ዲሲ መጋቢት 2014 ዓም በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ምስል Mana Multimedia


ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ
 
የሰላም ሒደቱን አንዳንዶች «ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ» የተገኘበት ጥሩ ማሳያ እንደሆነ አድርገው  ሲናገሩ ቸርነት ግን የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው የሰላም ሽምግልና ውጤታማ  ነው ብሎ አያምንም።  ለዚህም ምክንያቱን ሲናገር «የአፍሪካ ህብረት የሰው ልጅን ህይወት አላስቀደመመም። 
በመንግስት ታጣቂዎች የተፈፀመውን ግፍ በጽኑ ማውገዝ ነበረበት። ስለዚህ  አሁን ባለው አስተዳደር ምክንያት በተቋሙ ላይ ብዙም ዕምነት የለኝም። ይልቁንስ ከሁሉም የተጎዱ ክልሎች የተውጣጡ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብዬ አምናለሁ።» ይላል ። 

ቸርነት በውጪው ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም ሲተች «መሪዎቻችንን ተጠያቂ ማድረግ ተስኖናል። ህይወት ማዳን ተስኖናል። ንፋስ ወደነፈሰበት እንነፍሳለን። የኢትዮጵያን ህዝብ ለሰላም እንዲታገል ከማሰባሰብ ይልቅ ለምንደግፈው አካል በሚሊዮኞች የሚቆጠር ድጋፍ እንለግሳለን» ይላል።  ቸርነት አሁን ያለው አስተዳደር የሀገሪቱን ማህበራዊ መዋቅር የመቆጣጠር አቅም እንደሌለውም ሲያሳስብ « “ይህ የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ያላሳተፈ ከመሆኑም በላይ እርቅን እና ሀገሪቱን እያጋጠሟት ያሉትን ዋና ዋና ፈተናዎች አይጠቅስም። የሰላም ስምምነቱ ህዝቡን ከማካተት ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲ እና መንግሥትን ብቻ የሚመለከት ነበር። ኢትዮጵያውያን እውነተኛ አገራዊ ውይይት ማድረግ ቢችሉ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንችላለን። እኔ በአብይ አህመድ መንግሥት ላይ ምንም ተስፋ የለኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በራሱ የወደፊት እጣፋንታውን መወሰን አለበት። ምንም ይወስን ምን ያኔ እኔም ከህዝብ ጎን ነኝ ። » ሲል ሀሳቡን ይቋጫል።
 
ሌላው አስተያየቱን የሰጠን በካናዳ ነዋሪ የሆነው እና በትርፍ ጊዜው ለአማራ ህዝብ መብትና ጥቅም ለሚከራከር አንድ ማህበር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሆኖ የሚሰራው ሮቤል አለሙ ነው ። «በአጠቃላይ ይህ ስምምነት ዘላቂ ሰላም አያመጣም የሚል እምነት አለኝ፤ ህወኃት ባለፉት ጊዜያት የተኩስ አቁሙን መልሶ ለመደራጃነት እና ተጨማሪ ወረራ ለማድረግ ሲጠቀምበት እንደነበር ተሞክሮው ያሳያል።» ስለሆነም የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ካልፈቱ ተጨማሪ ውድመት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው በካናዳ የPh.D. ተማሪ የሆነው ሮቤል ይናገራል። «የሰላም ስምምነቱ አሁን ባለው መልክ ውጤቱ ለኢትዮጵያና ለሰፊው ቀጣና መረጋጋት ዋስትና አይሆንም።  ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በህወሓት ታጣቂዎች የተፈጸመው ወንጀል በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ተጠያቂነት እንዲኖር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል።»።   
 ተደራራቢ ግጭቶች   

ሮቤል አለሙ
ሮቤል አለሙ የአማራን ብሔር ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛልምስል Privat

«ምንም እንኳን የተኩስ አቅሙን ብቀበልም በሰላም ስምምነቱ ውስጥ በርካታ ስህተቶች  አሉ» የሚለው ሮቤል ወላጆቹ ከአማራ ክልል ናቸው። « ምንም እንኳን በግጭቱ በርካታ ተዋንያኖች የተሳተፉበት ቢሆንም ፣ ጦርነቱ በሁለት ወገኖች መካከል ብቻ እንደተደረገ በመቁጠር ነው ለመፍታት ጥረት የተደረገው። የአማራ፣ አፋር እና ከኤርትራ ማህበረሰቦች ከስምምነቱ እንደተገለሉ ነው የተረዳነው ”ይላል።  ሮቤል በተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረገው ስምምነትን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልክ እንደ 1987ቱ ህገመንግስት ላይ እንዳይሳተፍ መገፋት ጋር ያመሳስለዋል። ይህም ለኢትዮጵያዊያን ጉዳት እንደሆነ ነው የሚያምነው። 
ይህም «ህገመንግስቱ በቁጥር ብልጫ ያላቸው በአናሳዎች ላይ የበላይነትን ከማጎናጸፍ ባሻገር ከአካባቢያቸው ወጥተው ሌላ ቦታ ለሚኖሩት ደግሞ ባይተዋርነት እና እንደ «ሁለተኛ ዜጋ » ወይም «ሰፋሪ»የመታየት ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። » በማለት ይወቅሳል ሮቤል።
 በተፋላሚዎቹ ወገኖች መካከል ስምምነት እና እርቅ ለማውረድ  አሁን ያለው መንግስት  ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚናገረው ሮቤል  ፤ በምትኩ መንግስት ግጭት ቀስቃሽ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ይገልጻል ። “የብልጽግና ፓርቲም ሆነ ህወሓት በሀገሪቱ እየተፈጸሙ ላሉት ግፎች ተጠያቂ ናቸው።» በማለት ያክላል። «መልካም ነገር ከእነርሱ መጠበቅ የለብንም ፤ ይልቁኑ ከታጣቂዎች ውጭ ያሉትን ሁሉንም የፖለቲካ ተዋንያን ያካተተ የፖለቲካ ንግግር እንዲኖር እንፈልጋለን» ሲልም ጠይቋል።


በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ ሮቤል የሰብአዊ ተግባራትን አደራጅቶ ጠቀሜታው ቢኖረውም ጎጂ ሚና እንዳለው በግልጽ ተናግሯል፡ “በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም ጽንፈኛ የመገናኛ ብዙኃን አናሳ ብሄረሰቦች ላይ አሰቃቂ ግድያ እንዲፈጸሙ ሲያደርጉ  አይተናል። ” በማለት ተናግሯል። ግጭቱን ለመፍታት አስፈላጊ ሆነው ነገር ግን ችላ የተባሉ ጉዳዮችን በተመለተ ሲናገርም ለጦርነቱ መዋቅራዊ መንስኤ የነበሩ ችግሮች ተደራሽ መደረግ እንደሚኖርባቸው  ወጣቱ ያስረዳል። «የኢትዮጵያ ሕገመንግስት መከለስ ያለበት የአፓርታይድ አረመኔያዊ ሥርዓት ነው፤  ካለበለዚያ ብዙ ብጥብጥ ይጠበቃል። ዴሞክራሲና እኩልነት ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው። ይህ ከተደረገ ተስፋ ሰጪ የወደፊት ተስፋ የምናገኝ ይመስለኛል።  » በማለት ሀሳቡን ይቋጫል።
  
ሀሊማ ሰኢድ ከአፋር ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዩጵያውያን እና ትውልደ ኢትዩጵያውያን ጋር ትሰራለች።   «በሰላም ውይይቱ ላይ ብሩህ ተስፋ አለኝ» የአፋር ህዝብ ሰላም ይፈልጋል የሰዎች ስቃይ እንዲያቆም እንፈልጋለን ።ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንዲሁም ህይወታቸውን እንደገና እንዲጀምሩ እንፈልጋለን »። ትላለች። ህወኃት ስምምነቱን ወደ ጎን ሊተው እንደሚችል የጠቆመችው ሀሊማ «የኢትዮጵያ መንግስት ግን የሰላም ስምምነቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደሚተገብረው  እርግጠኛ ነኝ። » ትላለች።

ሀሊማ ሰኢድ
ሀሊማ ሰኢድ ከአፋር ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዩጵያውያን እና ትውልደ ኢትዩጵያውያን ጋር ትሰራለች። ምስል Privat
ሮቤል አለሙ
ሮቤል አለሙ: በአማራ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ተደጋጋሚ ጥቃት በማውገዝ በቶሮንቶ መስከረም 2014 ዓም በተካሄደው ሰልፍ ላይምስል Privat

አንድ መሆኑ ይሻለናል 
ሀሊማ  "መንግስት በተፋላሚ ወገኖች መካከል እርቅ መፍጠር ይችላል። ዋናው ችግር በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች ናቸው” የሚል ዕምነት አላት። አንዳንድ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚተላለፉ ፀብ ጫሪ መልእክቶች ኢትዮጵያ ያሉ ሰዎችን ለጥል እንደሚያነሳሱ የምትገልፀው ሀሊማ  በሀገሪቱ ላይ ያለውን ሰው ዲያስፖራው ለራሱ አጀንዳ  ከመጠቀም ይልቅ ይህንን ትቶ ሰላምን ማበረታታት እንዳለበት አፅኖት ሰጥታ ትናገራለች። 

የአፋር ወጣቶች ማህበር እና የአሜሪካ አፋር ዲያስፖራ ተቃውሞ
የአፋር ወጣቶች ማህበር እና የአሜሪካ አፋር ዲያስፖራ ህዳር 2014 ዓም በዋሽንግተን ዲሲ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደግምስል privat

“አሁን ሀገሪቱን መልሶ መገንባት ላይ ማተኮር አለብን። ከአፋር ወጣቶች ማህበር እና ከአሜሪካ አፋር ዲያስፖራ ጋር በህወሓት የፈረሱ ትምህርት ቤቶች እና መስጊዶችን እየገነባን እንገኛለን። መጻሕፍትን፣ እርሳሶችን፣ ወረቀትን፣ አልባሳትን፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን እና ሌሎችንም እየሰበሰብን ነው። በግጭቱ የተጎዱ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ርዳታ ይሻሉ።

ሃሊማ በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ ለተደራደሩት አካላት የምታስተላልፈውም መልዕክት አላት። “ለዚህ ስምምነት ኃላፊነት ላላቸው አካላት የማስተላልፈው መልዕክት ፤  በአፋር ፣በአማራ ክልልም ይሁን በትግራይ የተገደሉትን ንጹሃን ሰዎች አስቧቸው ። ወደፊት እንድንራመድ አንድ መሆኑ ይሻለናል። ስለሆነም ሀገራችን ኢትዮጵያን እንድናለማ  ሁሉም ሰው የሰላም ስምምነቱን ቢያከብር የተሻለ ነው። 

 

ይኩኖ ቦጋለ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

Äthiopien | Kämpfer der Fano-Miliz in Lalibela in der nördlichen Amhara-Region
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW
ዋናዉን ገፅ ተመልከት