1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ዲመርጆግ ያማተረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ

ረቡዕ፣ ግንቦት 3 2014

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዲመርጆግ የነዳጅ ማጠራቀሚያ በትብብር ለመገንባት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል። ሥምምነቱ ገቢራዊ ከሆነ የሚገነባው ማጠራቀሚያ 270 ቶን ነዳጅ የመያዝ አቅም ይኖረዋል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በ1.6 ቢሊዮን ዶላር 550 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማጓጓዣ ቧንቧ ለመገንባት የወጠኑት ዕቅድም አልተሳካም

https://p.dw.com/p/4B9Od
Äthiopien Ethiopian Investment Holdings and Great Horn Investment Holdings in Djibouti
ምስል Ethiopian Investment Holdings/Twitter

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በጅቡቲ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ለመገንባት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል

በአንድ መቶ ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ከአራት ወራት ገደማ በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በጅቡቲ የነዳጅ ማጠራቀሚያ በትብብር ለመገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ባለፈው ሣምንት ተፈራርሟል። ኩባንያው 10 ኪሎ ሜትር በየብስ 20 ኪሎ ሜትር በባሕር በሚሰፋው የዲመርጆግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የነዳጅ ማጣሪያውን በትብብር ለመገንባት የመግባቢያ ሥምምነት የተፈራረመው ግሬት ሆርን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተባለው የጅቡቲ ኩባንያ ጋር ነው።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በመሠረተ-ልማት ላይ ከጅቡቲው ኩባንያ ጋር በትብብር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ዐስታውቋል። በኩባንያው መግለጫ መሠረት ይኸ የትብብር ኢንቨስትመንት በማጓጓዣ እና በሎጂስቲክስ ሥርዓት የሚጀመር ነው። ሁለቱ ኩባንያዎች በጅቡቲ በጥምረት የሚገነቡት ማጣሪያ የሚፈልገው የካፒታል መጠን፣ እያንዳንዳቸው የሚኖራቸው ድርሻም ሆነ ግንባታ የሚካሔድበት ጊዜ ይፋ አልተደረገም። ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ከጅቡቲው ኩባንያ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ ለማግኘት ሳይሳካለት ቀርቷል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት "ስትራቴጂያዊ የኢንቨስትመንት ተቋም" የሆነው ይኸ ኩባንያ "አትራፊ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ማንኛቸውም የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች" የመሠማራት ሥልጣን ተሰጥቶታል። በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ጥር 23 ቀን፣ 2014 ዓ.ም በታተመው ደንብ "በየትኛውም የዓለም ክፍል በስሩ ተቀጥላ ድርጅቶች የሚቋቋሙበትን ሁኔታ" የመወሰን ሥልጣን ሰጥቶታል።

ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን፣ 2014 በጅቡቲ ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ማሞ ምኅረቱ "በዲመርጆግ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በጥምረት ለማልማት [ከግሬት ሆርን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ] ሊቀ-መንበር አቡበከር ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። በዲመርጆግ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ኢንቨስት የምናደርግበትን ሁኔታ እየተመለከትን እንገኛለን" ሲሉ ለጅቡቲ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

Dschibuti Tankwagen
ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ የምትሸምተውን ነዳጅ ሆራይዘን በተባለ ተርሚናል በኩል ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች። በየቀኑ 300 ከባድ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ጭነው ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛሉ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ያቀደው ከሰመረ ኢትዮጵያን ከሆራይዘን ተርሚናል ጥገኝነት ሊያላቅቃት እንደሚችል ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ተስፋ አድርገዋል።ምስል Getty Images/S. Gallup

"ነዳጅ ኢትዮጵያ ከውጪ ከምትሸምታቸው ሸቀጦች ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የማጓጓዣ ወጪን እና ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ፤ ተገቢው ማጠራቀሚያ እና ተገቢው መሠረተ-ልማት ያስፈልጋል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዲመርጆግ የታቀደው "ፕሮጀክት ኹነኛ ሚና" እንደሚጫወት አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያው ኩባንያ በመተባበር የነዳጅ ማጠራቀሚያ ለመገንባት የመግባቢያ ሥምምነት የተፈራረመው ግሬት ሆርን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተባለ ኩባንያ በጅቡቲ ወደቦች እና ከቀረጥ ነፃ ዞን አስተዳደር ሥር የሚገኝ ነው። ኩባንያው የዱራሌሕ እና ታጁራ ወደቦችን ያስተዳድራል። ከአገሪቱ ብሔራዊ የአየር መንገድ ከፍተኛውን ድርሻም በዚሁ ኩባንያ እጅ እንደሚገኝ በድረ-ገጹ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል።  ባለፈው ሐሙስ ከአቶ ማሞ ምኅረቱ ጋር የመግባቢያ ሥምምነቱን የተፈራረሙት የግሬት ሆርን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቡበከር ኦማር ሐዲ ናቸው። ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ መንግሥት ንብረት የሆኑት ሁለቱ ኩባንያዎች በተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት በዲመርጆግ የሚገነባው የነዳጅ ማጠራቀሚያ 270 ቶን ነዳጅ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለጅቡቲ ቴሌቭዥን እንደተናገሩት ሥምምነቱ ነዳጅ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዝበትን መሠረተ-ልማት ጭምር የተመለከተ ነው።

ነዳጅ ማጠራቀሚያ ለምን?

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሥራ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተሉ የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ኩባንያው ሊሰማራ ካቀደባቸው በርካታ የሥራ ዘርፎች በጅቡቲ የነዳጅ ማጠራቀሚያ መገንባት ማስቀደሙን በአዎንታ ተመልክተውታል። ለዚህም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሞያ ኢትዮጵያ የገበያውን የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት በሆራይዘን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ ያላትን ጥገኝነት በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ይኸ የነዳጅ ማጠራቀሚያ 371,000 ሜትር ኪዩብ የመያዝ አቅም፣ ሁለት የመርከቦች መቆሚያ እና ዐሥራ ሁለት ምርቶችን ወደ ከባድ ተሽከርካሪ መጫኛዎች ያሉት ነው። ኢትዮጵያ በዓመት ወደ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ አድርጋ ከዓለም ገበያ የምትሸምተውን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በዋንኛነት ሆራይዘን ጅቡቲ ተርሚናል የተባለው ኩባንያ ንብረት በሆነው በዚህ መሠረተ-ልማት ላይ ጥገኛ ሆናለች። በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ አቅርቦት እና ሽያጭ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ አባይነህ አወል ለአገሪቱ ነዳጅ የመቀበል፣ የማከማቸት እና ወደ ቦቴዎች የመጫን አገልግሎት የሚሰጠው ተርሚናል ከ16 አመታት በፊት የተቋቋመ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"ተርሚናሉ እስካሁን ድረስ የማስፋፊያ ሥራ አልሰራም። በሌላ በኩል የአገራችን የነዳጅ ፍላጎት በየዓመቱ በአማካኝ በዐሥር በመቶ ነው የሚያድገው። የአገራችንን የነዳጅ ፍጆታ ከ2006 ጋር ብታነጻጽረው ከእጥፍ በላይ አድጓል። ስለዚህ ይኸ ተርሚናል ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጠን አልቻለም። በመሆኑም የሆነ ነገር ሲፈጠር የነዳጅ እጥረት ያጋጥማል። ተገቢውን ነዳጅ ማቅረብ አንችልም" ሲሉ አቶ አባይነህ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በጅቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል ብቸኛ መሆኑን የገለጹት አቶ አባይነህ "እኛ በዚህ ተርሚናል ውስጥ ምንም አይነት ድርሻ የለንም። ኢትዮጵያ የባለቤትነት ድርሻ ስለሌላት አገልግሎት የሚሰጠን በኪራይ ነው። ለአገልግሎት የሚከፈለው ክፍያ በውጪ ምንዛሪ ሲሆን ከፍተኛ ነው" ብለዋል።  "ተገቢ ወይም በቂ አገልግሎት ስለማይሰጠን መርከቦች እንደቀረቡ ማራገፍ አይችሉም። ስለዚህ ለመርከብ መቆሚያ ወጪ እያጋለጠን ነው። ሌላው ደግሞ ተርሚናሉ አቅሙ ውስን በመሆኑ በትንንሽ መርከብ ነው ነዳጅ የምናቀርበው። በትልልቅ መርከብ በማምጣት ማግኘት የሚገባን ጥቅም አለ። ያንን ጥቅም አላገኘንም" ሲሉ ጫናውን አብራርተዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ኢትዮጵያ በዚህ አንድ ኩባንያ ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷ ተገቢ እንዳልሆነ ያምናሉ። ኩባንያው አንዳች እንከን ገጥሞት ሥራውን ማከናወን ቢሳነው ለኢትዮጵያ የሚቀርበው ነዳጅ ሊቆም እንደሚችል የሚናገሩት ባለሙያው "ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ የሆኑ ተርሚናሎች ያስፈልጓታል" ሲሉ ይሞግታሉ። ይኸ ግን ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደቦች ጥገኝነት የሚያላቅቃት አይሆንም።

የሆራይዘን ተርሚናል በገጠሙት የአቅም ውስንነቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት አማራጭ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ለመገንባት ማማተር ከያዘ አራት አመታት ገደማ ተቆጥረዋል። አቶ አባይነህ አወል አሁን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተፈራረመው የመግባቢያ ሥምምነት ለፍሬ ከበቃ ለአገሪቱ እፎይታ እንደሚሆን እምነታቸው ነው።

"የራሳችን ተርሚናል መኖሩ ወይም እዚያ መኖሩ ወጪ እንዲቆጥብ ያደርገናል፤ ተገቢ አገልግሎት እንድናገኝ ያስችለናል። አንድ ኩባንያ ብቻ እየሰጠን ያለው አገልግሎት በተወዳዳሪ ዋጋ እንዲሰጠን ያስችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien Abkommen zum Bau einer Pipeline | Yonis Ali Guedi und Samuel Horka
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በ1.6 ቢሊዮን ዶላር 550 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የናፍጣ እና ቤንዚን ማጓጓዣ ቧንቧ ለመገንባት የወጠኑት ዕቅድም አልተሳካም። መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ብላክስቶን የተባለ ግዙፍ የመዋዕለ-ንዋይ ኩባንያ ጭምር የተሳተፈበት ዕቅድ ነዳጅ ለማጓጓዝ ኢትዮጵያን ከከባድ ተሽከርካሪዎች ጥገኝነት የሚያላቅቅ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።ምስል Ethiopian Ministry of mines and petroleum

የውኃ ሽታ የሆኑት ዕቅዶች

ኢትዮጵያ  የነዳጅ ማጣሪያም ሆነ ማጠራቀሚያ ባለቤት ባለመሆኗ የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ከዚህ ቀደም ብቅ ያሉ ውጥኖች የነበሩ ቢሆንም አልሰመሩም። መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ፌርፋክስ አፍሪካ የተባለ ኩባንያ በአዋሽ አካባቢ በ4 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ማቀዱን ከአራት ዓመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር። ስድስት ሚሊዮን ቶን ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ይኖረዋል የተባለው ማጣሪያ ግንባታ በጎርጎሮሳዊው 2019 ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን በተግባር የታየ ነገር የለም።

ፌርፋክስ በኢትዮጵያ ነዳጅ ማጣሪያ ሊገነባ ነው

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በ1.6 ቢሊዮን ዶላር 550 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የናፍጣ እና ቤንዚን ማጓጓዣ ቧንቧ ለመገንባት የወጠኑት ዕቅድም አልተሳካም። መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ብላክስቶን የተባለ ግዙፍ የመዋዕለ-ንዋይ ኩባንያ ጭምር የተሳተፈበት ዕቅድ ነዳጅ ለማጓጓዝ ኢትዮጵያን ከከባድ ተሽከርካሪዎች ጥገኝነት የሚያላቅቅ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተፈቀደለት አንድ መቶ ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ "በጥሬ ገንዘብ እና በአይነት" የተከፈለው 25 ቢሊዮን ብር ነው። በጁቡቲ የተወጠነው ዕቅድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለዚህ ግዙፍ መዋዕለ-ንዋይ የሚሆን አቅም አለወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ከአመሠራረቱ ጀምሮ በቅርብ የሚከታተሉት የኢንቨስትመንት አማካሪ አዲስ በሚቋቋመው ኩባንያ አደረጃጀት ኢትዮጵያ ጥቅሟን የምታስጠብቅበት ተጽዕኖ ሊኖራት እንደሚገባ አቋም አላቸው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩባንያው ከፍ ያለ ድርሻ ሊኖረው ይገባል። ይኸ አቶ ማሞ የሚሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በጅቡቲ በሚቋቋመው አዲስ ኩባንያ ከፍ ያለ ገንዘብ ኢንቨስት እንዲያደርግ እንደሚያስገድደው የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪው ተናግረዋል።

Äthiopien Addis Ababa - Neuer Zug verbindet Hafen und Stadtzentrum
ነዳጅ ከሆርይዘን ተርሚናል ወደ አዋሽ ማጠራቀሚያ በባቡር ለማጓጓዝ ዕቅድ መኖሩን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ የተዘረጋውን የባቡር ማጓጓዣ ከአዋሽ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ማገናኘት የተጀመረ ሲሆን በጅቡቲ በኩል ተመሳሳይ ሥራ ይጠበቃል። ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2021/2022 የበጀት አመት ሁለተኛ መንፈቅ 944 ሚሊዮን ቶን የነዳጅ ውጤቶች ከዓለም ገበያ እንደሸመተች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል። በባንኩ ሰነድ መሠረት አገሪቱ 33.4 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ውጤቶች ለመሸመት ወጪ አድርጋለች። ኢትዮጵያ ለነዳጅ ያወጣችው ወጪ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ 126 በመቶ ገደማ ከፍ ያለ ነው። የአውሮፕላን ነዳጅ፣ የጋዝ፣ መደበኛ ቤንዚን እንዲሁም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሻቀብ ለአገሪቱ ወጪ መጨመር ዋንኛው ምክንያት ነው። አገሪቱ ከዓለም ገበያ የምትሸምተውን ነዳጅ በጅቡቲ በኩል ስታስገባ የምትጠቀምበት የማጓጓዣ መንገድ ሌላው ፈተና ነው።

አቶ አባይነህ አወል "በቀን ከጅቡቲ የሚጫነው ነዳጅ ወደ 300 መኪና ነው። ይኸ ሁሉ መኪና የሚጠቀመውን ነዳጅ ማሰብ ይቻላል። መንገዱ ምን ያህል ይጎዳል? የጥገና ወጪ ይኖራል። የጥገና [ወጪ] ይኖራል። በመኪና ማጓጓዝ ተመራጭ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።  አገሪቱ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመገንባት ያደረገችው ሙከራ ባለመሳካቱ ፊቷን ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ በተዘረጋው የባቡር መንገድ አዙራለች። "ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚያስችሉ የባቡር ፉርጎዎች ተዘጋጅተዋል። የቀረው ነገር ባቡር መስመሩ ከመቀበያ እና ከመጫኛው ጋር የማገናኘት ነው። ማለትም በአሁኑ ወቅት ከሆራይዘን ተርሚናል ጋር መገናኘት አለበት። በእኛ በኩል ደግሞ ማራገፊያ አዋሽ ላይ ትልቅ ተርሚናል ሰርተናል። በአዋሽ ከሚገኘው ተርሚናል ጋር የማገናኘቱ ሥራ እየተሰራ ነው ያለው። በጅቡቲ በኩልም ሥራውን ለመጀመር በሒደት ላይ ነው" በማለት በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ አቅርቦት እና ሽያጭ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ አባይነህ አወል አስረድተዋል።

በጅቡቲ ከሚገኘው ማጠራቀሚያ ነዳጅ በአዋሽ እስከ ተገነባው ተርሚናል በባቡር ማጓጓዝ ከተቻለ በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ እፎይታ የሚፈጥር ይመስላል። አቶ አባይነህ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት 83 ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚጭኑትን ነዳጅ በባቡር አንድ ጉዞ ከጅቡቲ አዋሽ ማድረስ ይቻላል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ