1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተባለ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 8 2010

የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ዜጎች "በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ምናልባት ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል" ሲል ሥጋቱን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፦ "የተፈናቀሉ እና ወደ ኬንያ ድንበር የሔዱ ዜጎቻችንን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ" ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/2uWqb
Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ዜጎች ወደ ኬንያ ሊሰደዱ እንደሚችሉ የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር (WFP) ሥጋቱን ገለጸ። የድርጅቱ የኬንያ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ፒተር ስሜርዶን ተፈናቃዮችን በተመለከተ ሲናገሩ፦ «በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ምናልባት ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል ብለን እንጠብቃለን» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወደ ኬንያ የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን «አሁን ቁጥራቸው ከ9, 600 በላይ ናቸው ተብሎ ይገመታል» ያሉት ስሜርዶን አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል። ከትናንት ጀምሮም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እና የዓለም የምግብ መርኃ-ግብርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ለመርዳት ሁኔታውን እያጠኑ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተሰደዱ ዜጎችን ለመመለስ «ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ»መሆኑን ገልጿል። የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ «ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚመለከታቸው ከክልልና ከፌድራል መንግሥት ከአካባቢ አስተዳደር ቡድን ተዋቅሮ ወደ ቦታው ሔዷል። ሕብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ ነው። የተጎዱ ቤተሰቦችን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው። የተፈናቀሉ እና ወደ ኬንያ ድንበር የሔዱ ዜጎቻችንን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር የኬንያ ቢሮ ቃል-አቀባይ በስልክ እንደተናገሩት ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ምግብ እና መጠለያን ጨምሮ በርካታ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። 

«አሁን ቁጥራቸው ከ9, 600 በላይ ናቸው ተብሎ ይገመታል። የተወሰኑት የሕክምና ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ምግብ፣ መጠለያ እና የመጠጥ ውኃም ይፈልጋሉ። አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው። የርዳታ ድርጅቶች አሁን የተፈናቃዮቹን ፍላጎት እያጠኑ ናቸው። የኬንያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እና አጋሮቹ ጋር በመሆን ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ተስማምቷል። መንግሥት ተፈናቃዮቹ የሚሰፍሩበትን ቦታ ማመቻቸት ይኖርበታል። ምክንያቱም በአንድ ቦታ ርዳታ ለመስጠት ይቀላል። ቁጥራቸውን በትክክል ለማወቅ ይቻል ዘንድ ሊመዘገቡም ይገባል።» ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሁኔታውን የሚገመግም አንድ ቡድን በነገው ዕለት ወደ ኬንያዋ ሞያሌ እንደሚልክ አስታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ ኬንያ የተሰደዱት የአገሪቱ ጦር "በስሕተት" ባለው ጥቃት 10 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በገባቸው የደሕንነት ሥጋት ነበር።  

እሸቴ በቀለ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ