ከዳዌ ሐረዋ እስከ አጣዬ የዘለቀው ግጭት | ኢትዮጵያ | DW | 07.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከዳዌ ሐረዋ እስከ አጣዬ የዘለቀው ግጭት

ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት በጠፋባቸው በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ መወሰኑን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ። አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራቆሬ በተባሉ ከተሞች በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ በ270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአጣዬ ከተማ ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የጀመረው ግጭት ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል። አንድ የአጣዬ ነዋሪ ከትናንት ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የገቡ ታጣቂዎች ጥቃት ፈፅመዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በከተማዋ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ምክንያት ከቤታቸው ለመውጣት መቸገራቸውን የገለጹት ግለሰብ "ማጀቴ እና አጣዬ ሕዝብ አለቀ። የተላኩትም መከላከያ እና ፌድራሎች ከላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም እያሉ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ "ኦነግ ያደራጃቸው ታጣቂዎች ከመጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የአጣዬ ከተማ አስተዳዳርን ለመውረር በከፈቱት ተኩስ" አራት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ቢሮው በፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው መረጃ "ሕይወታቸው ካለፉት መካከል አንዱ በተባራሪ ጥይት ተመቶ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ የከተማቸውን ሠላም ለማስጠበቅ የተሰማሩ የፀጥታ አባላት ናቸው" ብሏል።

ዶይቼ ቬለ ከአጣዬ ከተማ ፖሊስ እና በአካባቢው ከሚገኙ ሆስፒታሎች በግጭቱ የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎችን ቁጥር ለማጣራት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልሰመረም። አንድ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ በትናንትናው ተኩስ "ብዙ ሰዎች ተገድለዋል" ሲሉ ተናግረዋል።  ዛሬ በከተማዋ ተኩስ ይሰማል የሚሉት የአጣዬ ነዋሪ  "30 ደቂቃ 20 ደቂቃ ያርፍና ከእንደገና ደግሞ ጦርነቱ ይጧጧፋል። እኛ ፈርተን ከቤት አንወጣም። ጤና ጣቢያው ለሕክምና አስቸግሯቸዋል። ጤና ጣቢያው ውስጥ የተመታ ሰው ሞልቷል" ሲሉ አክለዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ በሚያመራው መንገድ ላይ በሚገኙት ካራቆሬ እና ማጀቴ ተመሳሳይ ግጭቶች መከሰታቸውን ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ሐሰን ከጥቂት ቀናት በፊት  ዳዌ ሐረዋ በተባለ አካባቢ በጸጥታ አስከባሪዎች እና በነዋሪዎች መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ቀውሱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዛመቱን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። "የአማራ ልዩ ኃይል በአካባቢው ከሚኖሩ አርሶ አደሮች የኦነግን ባንዲራ ከሱቃቸው ላይ በማንሳት የመቅደድ፤ የጦር መሳሪያ የመፍታት ቀጥሎም የሞተ ሰው አለ በሚል ሕዝብን የማስጨነቅ እና የማሸበር ኹኔታ ነበሩ" የሚሉት አቶ አሕመድ ጉዳዩ በአካባቢው ውጥረት መፍሩን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ባለፈው አርብ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በተፈጠረ ግጭት አራት የጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን ለDW ተናግረው ነበር። ኃላፊው ግጭቱ የተቀሰቀሰው በአካባቢው የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ አሕመድ የትናንትናው ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የአጣዬ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አመራሮች፤ የአገር ሽማግሌዎች እና የሚመለከታቸው ውይይት አድርገው እንደነበር ተናግረዋል።

"ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው" የሚሉት አቶ አሕመድ "ያገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የጸጥታ አካሉ በጋራ ርብርብ መፍታት ያለበት ነው። ይኸንን ለማድረግ መከላከያ እንዲገባ ተደርጓል ሲሉ" አስረድተዋል።

በግጭቱ አሳሳቢነት የሚስማሙት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የድርጅት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሜ ሙሔ "ያገር መከላከያ ሰራዊት ገብቷል። እዚያው በየቦታው ነው ያሉት" ሲሉ ተናግረዋል።  እስካሁን የብሔር ግጭት መልክ የለውም የሚሉት አቶ አሜ "አጣዬ አካባቢ እየተከሰተ ያለው ነገር ወደ ብሔር የመቀየር አዝማሚያ ስላለ ቶሎ መከላከያ ገብቶ እንዲያረጋጋ" መወሰኑን ገልጸዋል።

ከኬሚሴ 15 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው መኮይ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ በአካባቢው ተመሳሳይ ውጥረት አስተውለዋል። መኮይ የሚኖሩት የአይን እማኝ "እዚሕ እኛ ያለንበት አካባቢ ታጣቂዎች እየተንቀሳቀሱ ነው።  ግጭቱ ወደዚህ ይመጣ እንደሆነ እያለ ሕዝቡ ሥጋት ላይ ነው ያለው" ሲሉ እስከ አጣዬ የዘለቀው ግጭት ወደ አካባቢው ይዛመታል የሚል ሥጋት በነዋሪዎች ዘንድ እንደሚታይ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ