1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከደብረብርሀን ደሴ እና ከደሴ ደብረብርሀን የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ

ሰኞ፣ የካቲት 18 2016

የደብረብርሀን ከተማ ነዋሪ በመንገዱ መዘጋት በርካታ ሰዎች በደብረብርሀን አውቶቡስ መናኸሪያ ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።፡“ወደ አዲስ አበባም እንዳይኬድ፣ ተዘግቷል፣ ከጫጫ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባም መሄድ አይቻልም፣ ወደ ጅሩም መጓዝ አይቻልም፣ ዋና መንገዱ ስለተዘጋ ሁሉም ቦታ መሄድ አይቻልም፣የደብረብርሀን መናኸሪያ ዝግ ነው»ብለዋል

https://p.dw.com/p/4ctsl
ደብረ ብርሀን ከተማ
ደብረ ብርሀን ከተማምስል Eshete Bekele/DW

ከደብረብርሀን ደሴና ከደሴ ደብረብርሀን ባለው መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ

ከደብረብርሀን ደሴና ከደሴ ደብረብርሀን ባለው መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናገሩ። የአካባቢው እዝ ጣቢያ (Command Post) በበኩሉ “ፅንፈኛ” ብሎ በጠራቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ በመሆኑ ለህዝቦች ደህንነት ሲባል መንገዱ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን አሳውቋል፡፡ አለምነው መኮንን ከባህርዳር

ካለፈው ነሐሴ 2015 ዓ ም ጀምሮ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጦርነት ክስተቶች በርካቶች ሲገደሉ፣ ሌሎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ንብረታቸውም ወድሟል፡፡ በፀጥታው መደፍረስ ምክንያት የመንገዶች መዘጋጋትና እንደልብ ሸቀጦችን ወደ ገበያ ማድረስ ባለመቻሉም የኑሮ ውድነቱን በእጅጉ እንዳባባሰው ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡

ሰሞኑንም ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ከደብረ ብርሀን ወደ ደሴና፣ ከደሴ ወደ ደብረብርሀን ባሉ መስመሮች መንገድ መዘጋቱን ነው ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ያስረዱት፡፡

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ በአካባቢዎቹ እገታዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ለመንገዶቹ መዘጋት ይህ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ገልፀዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኘው የደሴ ከተማ
በአማራ ክልል የሚገኘው የደሴ ከተማምስል Alemenw Mekonne/DW

አያይዘውም፣ “አዎ ተቋርጧል፣ ከደሴም ወደ ሸዋ ሮቢት አይመጣም፣ ከሸዋሮቢት ወደ ደሴም አይሄድም፣ ከሸዋሮቢት ወደ ደብረብርሀን አይሄድም፣ ከደብረብርሀንም ወደ ሸዋሮቢትም አይሄድም፣ መንግስት ለህዝቡ ደህንነት ሰግቶ መሰለኝ፣ አሁን ካለው የማገት፣ በዛም በዚህም የሚደረገው ነገር መንገዱ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ያነን ለማጥራት ይመስለኛል፣ መንገዱ ባዶ ነው፣ ምንም የመኪና እንቅስቃሴ የለም፡፡” ብለዋል፡፡የተሽከርካሪዎች እና የሾፌሮቻቸው መታገትና መጠቃት እየጨመረ ነዉ

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ፣ ድምፀቸውም እንዲቀየር የፈለጉ የከሚሴ ነዋሪም አልፎ አልፎ በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ውጪ መንገዶች ከየካቲት 16 ጀምሮ ለአገልግሎት ዝግ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የካራ ቆሬ ነዋሪ በበኩላቸው መንግስት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራቸው ታጣቂዎች በቅርቡ “ማርዋጫ”ና “ሰንበቴ ቆሮ” ግድያና ዝርፊያ መፈፀማቸውን አመልክተው በዚህ ምክንት መንገዱ ሳይዘጋ እንደማይቀር ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል፡፡

“... ከሁለት ቀናት በፊት ነው፣ ዛሬ 3ኛ ቀኑ ነው፣ “ሸኔ” ከድሮም ጀምሮ የተንሰራፋበት አአካባቢ ነው ያለው፣ ሰሞኑን ልዩ ስሙ “እንቶሊዎን” ወይም “ማርዋጫ” በሚባል አካባቢ በመኪና ይጓዙ የነበሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ከዚያ በኋላም 108 የሚሆኑ ሰዎችን ከሁለት አውቶቡሶች ላይ አግተው፣ “ሰንበቴ ቆሮ” በምትባል ቦታ ላይ የቃል ኪዳን ቀለበት ሳይቀር የዘረፉበት ሁኔታ አለ፣ ይህን፣ ይህን በመመልከት መሰለኝ የአካባቢው እዝ ጣቢያ (Command Post) መንገዱን ዝግ ያደረገው፣ አሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ”

ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ የምትገኘው የሸዋ ሮቢት ከተማ
ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ የምትገኘው የሸዋ ሮቢት ከተማ ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

 አንድ የደብረብርሀን ከተማ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት  በመንገዱ መዘጋት በርካታ ሰዎች በደብረብርሀን  አውቶቡስ መናኸሪያ ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡“ ወደ አዲስ አበባም እንዳይኬድ፣ ተዘግቷል፣ ከጫጫ (ሰሜን ሸዋ ውስጥ ያለች ከተማ) ጀምሮ ወደ አዲስ አበባም መሄድ አይቻልም፣ ወደ ጅሩም መጓዝ አይቻልም፣ ዋና መንገዱ ስለተዘጋ ሁሉም ቦታ መሄድ አይቻልም፣ ዝግ ነው.፣ ደብረብርሀን መናኸሪያ ዝግ ነው ፣ ሰው ደብረብርሀን ላይ በአጋጣሚ የወጣው ሁሉ ስቃዩን እያየ ነው፡፡” ነው ያሉት፡፡ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ የሰዎች መታገት ያሳደረዉ ስጋት

የማዕከላዊ ሸዋ እዝ ጣቢያ (Command Post) የካቲት 15/2016 ዓ ም “አስቸኳይ ውሳኔ” በሚል ባወጣው መግለጫ  “ፅንፈኛ” ብሎ በጠራቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፣ መግለጫው አያይዞም፣  “...ሰላማዊ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው፣ ከየካትት 16 ቀን/2016 ዓ ም ጀምሮ ከደሴ -ሸዋሮቢት- ደብረብርሀንና፣ ከደብረብርሀን-ሸዋሮቢት- ደሴ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለጊዜው እንዲቆም ተወስኗል” ብሏል፡፡

ከማዕከላዊ ሸዋ እዝ ጣቢያ ተጫማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ