1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲስተም ችግር ተወሰደ የተባለው ገንዘብ፤በፒያሳ የቤቶች ፈረሳ

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2016

የማርያም ልጅ « ባንኩም ሊያፍር ይገባል የራሣቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሠዱ ግለሠቦችን እጅግ በጣም ሊያፍሩ ይገባል የመንገድ ሾላ አደረገው አንዴ የህዝብ ገንዘብ እያወጣ የሚወስደው ሲሉ ሰውና ምግባሩ ደግሞ « በአደራ የተሰጠውን ገንዘብ በአደራ በጥንቃቄ መያዝ የባንኩ ድርሻ ነው ሚስጥራዊ ቁጥሮች ከራሱ ከባንኩ ሰራተኞች በቀር ተጠቃሚ አያቅም»ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4dzqV
Äthiopien | CBE Bank in Addis Abeba
ምስል Eshete Bekele/DW

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲስተም ችግር ተወሰደ የተባለው ገንዘብ፤በፒያሳ የቤቶች ፈረሳ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አርብ ለሊት አጋጠመኝ ባለው የሲስተም ችግር ምክንያት ጤናማ ያልሆነ ያለው የገንዘብ እንቅስቃሴ መካሄዱን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር ያረጋገጠው። ባንኩ ይህን ከማሳወቁ በፊት በዚህ እንቅስቃሴ 2.4 ቢሊዮን ብር እንደተወሰደበት ተዘግቦ ነበር። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ሰኞ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ  ጤናማ ያልሆነ ባሉት የገንዘብ እንቅስቃሴ በእለቱ ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር እንደነበር አስታውቀዋል።ሆኖም በባንኩ የደንበኞች የግል ሒሳብ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል። በዋናነት በዚህ ድርጊት የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደነበሩና ገንዘቡን እየመለሱ መሆኑን ተናግረው ነበር።  ከዚያ በኋላ ባንኩ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱና ወደ ተለያዩ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ ፊታችን ቅዳሜ በፈቃዳቸው ገንዘቡን እንዲመልሱ እያሳሰበ ነው።

በሲስተም ችግር ምክንያት ባንኩ ተወሰደ ባለው ገንዘብና ገንዘቡን መልሱልኝ ሲል በተደጋጋሚ ባቀረበው ማሳሰቢያ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።  በሆነው ያዘኑ፣ ድርጊቱ ያሳሰባቸው ፣ ወደፊት ሊሆን የሚችለው ያስጨነቃቸው፣የተለያዩ ጥርጣሬዎቻቸውን የገለጹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተጠያቂ ያደረጉ ወሰዱ የተባሉትን የኮነኑና በአንጻሩ ወድቆ የተገኘን ባነሱ ምን አጠፉ የሚሉና የመሳሰሉ አስተያየቶች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ተንሸራሽረዋል። የተሳለቁም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። የሰዎችን ክብር የሚነኩ  ዘለፋ ያካተቱና ሚዛናዊነት የሚጎድላቸውን ወደ ጎን ትተን ሌሎቹን ስንመለከት አያሌው ታደሰ አየነው በአጭሩ «ወይ ንግድ ባንክ! ፅድቁ ቀርቶብኝ.» ሲሉ ኤክስ ማኛው የሸገር ልጅ  «እራሳችሁ ሰጥታችሁ መልሱ ማለቱ አይከብድም? ።» ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጠይቀዋል። ጥጋቡ ታደሰ ደግሞ« መጠየቅ ያለበት በመጀመሪያ ሲስተሙን ያበለሻዉ ሰዉ ነዉ እንጂ ገንዘቡን የተቀበለዉ አይደለም እንደ ህጉ ከሆነ  ግን ብሩን የተቀበለዉ ሰዉ በቅን ልቦና ቢመልስ ቅር አያሰኘኝም» ብለዋል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?
 
«በሀገራችን እየሆነ ባለው በጣም እያዘንኩ ነው። እባካችሁ ገንዘቡን ለባንኩ መልሱ መንግሥት ይመጣል ይሄዳል። እኛ ግን አለን። አላዋቂነታችንን ትተን አንድ እንሁን»የሚሉት ደግሞ የሺባከር ባከር ናቸው። ሀበሻ ስታር መልቲ ሚድያ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ሃሳብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሰረቀው የውጭ አገር ዜጋ ገንዘብ አይደለም፤የኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ነው ፡፡ከእምነታችን ከባህላችን የወጣ መጥፎ አስነዋሪ ተግባር ነው። ካለ በኋላ የወሰዳችሁ መልሱ በክብር ሲል ይመክራል። 
ገብረጊዮርጊስ ሀጎስ ደግሞ «የሰው ገንዘብ የወሰደ አሁንም ሌባ ነውና ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል::  ሲሉ አሳስበዋል። « የእምዬን ወደ አብዬ? ለመሆኑ ተማሪዎች ከምሽቱ አምስት ሰዐት በዃላ ወደ ATM ማሽን እንዲሄዱ እና ትራንዛክሽን እንዲያደርጉ መረጃ እንዴት ኖራቸው??» ሰው ብቻ ነኝ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበው ይህ ጥያቄ ያካተተው አስተያየት የባንኩን ሰራተኞች በድርጊቱ የሚያስጠረጥሩ ሁኔታዎች ሳይኖሩ እንዳልቀረ ለመጠቆም ይሞክራል ።
የማርያም ልጅ ደግሞ « ባንኩም ሊያፍር ይገባል የራሣቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሠዱ ግለሠቦችን እጅግ በጣም ሊያፍሩ ይገባል የመንገድ ሾላ አደረገው አንዴ የህዝብ ገንዘብ እያወጣ የሚወስደው ሲሉ ሰውና ምግባሩ ደግሞ « በአደራ የተሰጠውን ገንዘብ በአደራ በጥንቃቄ መያዝ የባንኩ ድርሻ ነው ሚስጥራዊ ቁጥሮች ከራሱ ከባንኩ ሰራተኞች በቀር ተጠቃሚ አያቅም ይልቅ መልሱልኝ ብሎ ክስ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ገንዘብ በማዘረፍ እራሱ ሊጠየቅ ይገባል ሲሉ ጽፈዋል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክምስል Solomon Muchie/DW

ባንኮች የህዝብ እንጂ የአንዱ አካል አይደሉም የተዘረፈው የህዝብ ሃብት እንጂ ከዬትም የመጣ አየደለም በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት ሞም ላቭ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ሰው «ተጎጂው ህዝብ ነው ምክንያቱም ምንም ሳይሰራ ገበያ ላይ የተበተነው ካሽ ገንዘብ ትልቅ የገንዘብ የመገዛት አቅም በዛው ልክ ይቀንሳል ስለዚህ እንደዚህ አይነት መጭበርበር መቃወም እንጂ ደስ ሊለን አይገባም በማለት ምክራቸውን አጠቃለዋል። ፍሪው ነጋሽ ደግሞ « ተማሪው ስሙ በከንቱ እየተነሳ ይመስለኛል። አብዛኛው ማህበረሰብ ክፍል በክስተቱ ውስጥ ተሳትፏል፤ተማሪውን በአጠቃላይ መዝለፉ ተገቢ አይመስለኝም። ሲሉ ገንዘቡን ከወሰዱት መካከል ተማሪዎች ያመዝናሉ መባሉን ነቅፈዋል። እስክንድር ከበደ ደግሞ የባንኩ የቴክኒክ ክፍል ሰራተኞች ላይ ምርመራ ቢካሄድ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ፍቅሩ ሰማ ለነገው መጠንቀቅ ነው ሲሉ ፣ መስፍን ተፈራ ደግሞ «ንግድ ባንክ ሆይ ውስጥህን በመጀመርያ ደረጃ አጥራ ሲሉ ለባንኩ መልዕክታቸውን አስተላለልፈዋል ።
ሰሞኑን ባንኩ ካጋጠመው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሰዱና ያልተገባ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያከናወኑ  ነገር ግን ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችም እስከመጪው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ በመቅረብ ተመላሽ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አበባ ለማድረግ በሚል በተያዘው እቅድ ፒያሳና አካባቢው የሚገኙ እድሜ ጠገብ ቤቶችና የንግድ ተቋማት እየፈረሱ ነው። የቤት ባለቤቶች እና የንግድ ተቋማት ካሳና ምትክ ይሰጣቸዋል ተብሏል። በዚህ የቤቶች ፈረሳ የከተማይቱ ቅርስ የሚባሉና ታሪካዊና ጥንታዊ ቤቶችም ተካተዋል የሚሉ ድርጊቱን በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። በአንድ በኩል የቤቶች ፈረሳው ተገቢ አይደለም በማለት የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ ከተማዋን ለማሳደግና ሳቢ ለማድረግ  እየተወሰደ ነው የሚሉት የዚህ እርምጃ ደጋፊዎችም አልጠፉም ።  በዚህ ጉዳይ ላይ ዶቼቬለ የፌስቡክ ተከታዮቹን አወያይቶ ነበር። ከተሰጡት የተለያዩ አስተያየቶች መካከል የወንዴ ኢትዮጵያ አንዱ ነው። «በአሮጌ እና ባረጀ ነገር ላይ ምንም ትውስታ የለኝም አዲስ ነገርን ለመቀበል እራሳችንን እናዘጋጅ ይላል። ጥላዬ ከበደ « ያሁሉ አለፈ ቀረ በአዲሰ መልክ ውብ ሊያደርጓት ነው መሠለኝ» ሲሉ ተስፋቸውን አካፍለዋል።

በመፍረስ ላይ የሚገኘው የፒያሳ አካባቢ
በመፍረስ ላይ የሚገኘው የፒያሳ አካባቢምስል Solomon Muche/DW

የአዲስ አበባ የፒያሳው የአራዳ ሕንፃ ሱቆች መፍረስ

አዲስ አበባን እንደ ሰሟ አዲስ ለማድረግ ? ወይስ ሌላ ዕቅድ ? የሚሉት ጥያቄዎች በማስቀደም መልእክታቸውን የጀመሩት በለጠ ካሳ ሀብተ ማርያም «እሺ ለቀበሌ ቤት ነዋሪ ሌላ ምትክ ይሰጣል እንበል የንግድ ቤቶች እና በአነሱ ስር ያሉ ለፍቶ አዳሪዎች መበተንስ? በዚህ ላይ ለግል ባለይዞታዎች ካሳ ሳይሆን ማባበያ ነዉ ይሄ ነገር ዜጎችን ወደ ድህነት መምራት አይደል እንዴ? ተወልዶ አድጎባት ታሪኩን ከአዲስአበባ ጋር ያስተሳሰረዉማ ታሪክ አልባ እንዲሆን ተፈርዶበታል ።ዘመናዊነትንና ልማትን ከዜጎች ጋር በመመካከር ቢሰራ ምን ችግር ነበረበት አይ ጊዜ ሲሉ ሃሳባቸውን በቁጭት አጠቃለዋል። የሰው መሆን በቂ አስተያየት ግን ከዚህ ይለያል።  «ምንም ይፍረስ አላማው ማሳመር የበለጠ ለማስዋብ እስከ ሆነ ድረስ ችግር የለም ከተማዋ ከአየር ስትታይ አሮጌው ይበዛል። ማስተካከል ግድ ይላል ሲሉ  አጁ ፈቲ ደግሞ በተቃራኒው ድርጊቱ ያሳስባቸውዋል ።«እኔ የሚያሳስበኝ ሲሉ ሀሳባቸውን የጀመሩት አጁ ፈቲ « እንዴ እኔ ድሃው የት ሊሄድ ነው የሚለው ነው? ስራ የለም ቤት ተወደደ ይሄ ነው እኔን የሚያሳስብኝ ብለዋል።

«አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ከዚያም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል ቀድም ብለው የነበሩትን እድሜ ጠገብ ህንፃዎች ዘመናዊ በሆኑ መልኩ ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው።» የሚሉት የያሬድ ማኅበረሰብ ድምጽ ዘመናዊነታቸውን በጠበቁ የመዝናኛ ቦታዎች ፣ ካፍቴሪያዎች ፣ ፊልም እና ትያትር ቤቶች አዲስ አበባን ለማስዎብ ቀደም ብለው የነበሩ ጠላ ቤቶች ፣ ጠጅ ቤቶች ፣ ሻይ ቤቶች ህዝብ መተላለፊያ መንገድ ላይ ተቀምጦ አላፊ እና አግዳሚውን ሰላም ይነሱ የነበሩ ሙዚቃ ቤቶች እና መሸታ ቤቶች ለልማት መነሳታቸው አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው። በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።
ሳሚ ያለው ካሳ ግን« አዲስ አበባን እንደ ስሟ ማለት ምን ማለት ነው?? አዲስ አበባ እኮ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተለየች ሆና ለማን ልትሆን ነው??? ሃገር የሚለማው እኮ በእኩልነት ነው:: ምግብ ሳይበላ መጠለያ የሌለው: ልብስ እና ጫማ ለሌለው : እራቁቱን ውሎ እራቁቱን ለሚያድረው ኢትዮጵያዊ የአበበች አዲስ አበባ ምኑ ናት?» ሲሉ ጠይቀዋል።በዚህ አጋጣሚ ሳሚ ያለው ካሳ ከዚሁ ጋር አያይዘው አያይዘው ዶቼቬለን የወቀሱበት አስተያያትዎ ከእውነት የራቀና እኛን የማይወክል መሆኑን ልንገልጽልዎት እንወዳለን 
ወደ ሌላ አስተያየት ስናልፍ ሎጎዳ ሄናባ በሚል የፌስቡክ ስም «እድሜ ጠገብ የሆኑ ከተሞችና የመኖሪያ መንደሮች በሰለጠኑ አገራት በእንክብካቤ ተይዘው ከትውልድ ተውልድ ይሸጋገራሉ፣ የቱሪስት የገቢ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ፣ የየዘመናት ታሪክ ማሳያ ሆነው ለምርምርና ትምህርት ይውላሉ፣ ሆኖም በኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣንን የሚይዙ ግለሰቦች የመረጣቸውን ህዝብ ድጋፍ ሳይጠይቁ የህዝብና የአገር ታሪክን እያወደሙ ይገኛሉ፣ በመሆኑም ይህ ተግባር በሕግ ማእቀፍ እልባት ካልተገኘለት ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው፣ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ታሪክ የህዝብ እንጂ የአንድ መንግስት ንብረት አይደለም። የሚል አስተያየት ሰፍሯል።
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ