1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአማራ ወደ ትግራይና ከትግራይ ወደ አማራ ክልል በመመለስ ላይ ያሉ ተፈናቃዮችና ስጋታቸው

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016

አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ተፈናቃዮቹ ከትግራይ ተመልሰው ወደ አላማጣ መኖሪያቸው የገቡ ቢሆንም ተዋጊ የነበሩና የታጠቁ አካላት አሁንም በየትምህርት ቤቶች ሰፍረዋል ብለዋል፣ በአካባቢው ያለው የመከላከያ ሰራዊት እነኚህ አካላት የከተማዋ ቀደምት ነዋሪ ካልሆኑ እንዲወጡ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንደሰጣቸውም አስተያየት ሰጪው ገልጠዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4ih47
ተፈናቃዮች በዋግኽምራ
ተፈናቃዮች በዋግኽምራ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

ከአማራ ወደ ትግራይና ከትግራይ ወደ አማራ ክልል በመመለስ ላይ ያሉ ተፈናቃዮችና ስጋታቸው

ተፈናቃዮች ከአማራ ወደ ትግራይና ከትግራይ ወደ አማራ ክልል እየተመለሱ እንደሆነ ተመላሾችና ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡ በሁለቱም ክልሎች በኩል በተፈናቃይ ስም የታጠቁ ሰዎችም ተመልሰዋል በሚል ሲከስሱ፣ ከአመራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ታጥቀው የተመለሱ ትጥቅ ሳፈቱ  ከወደትግራይ የመጡት የታጠቁ አካላት ግን ከነትጥቃቸው በመሆናቸው ስጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ከሰሜን ጦርነቱ ጋር በተያያዘ ብዙዎቹ ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ኑሯቸውን ሲመሩ ቆይተዋል፣ ከሁለት ወር በፊት በራያ አላማጣና አጎራባች ወረዳዎች የትግራይ ታጣቂዎች በመጡበት ወቅት ደግሞ በሺዎች የራያ አላማጣ፣ የኦፍላ ወረዳና የሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ነዋሪዎች ወደ ትግራይና አማራ ክልሎች ተፈናቅለዋል፡፡

የተፈናቃዮች አስተያየት

ሰሞኑን ግን ከሁለቱም አቅጣጫዎች ፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል፡፡ አንድ የኮረም ከተማ ነዋሪ መጀመሪያያ ከቆቦ በኋላ ደግሞ ከአላማጣ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም ነዋሪው የበለጠ እንዲቀራረብ ስራ መሰራት እንዳለበት አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡የራያ አላማጣ ተፈናቃዮች መመለስና ውዝግቡ
ሌላ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ተፈናቃዮቹ ከትግራይ ተመልሰው ወደ አላማጣ  መኖሪያቸው የገቡ ቢሆንም ተዋጊ የነበሩና የታጠቁ አካላት አሁንም በየትምህርት ቤቶች ሰፍረዋል ብለዋል፣ በአካባቢው ያለው የመከላከያ ሰራዊት እነኚህ አካላት የከተማዋ ቀደምት ነዋሪ ካልሆኑ እንዲወጡ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንደሰጣቸውም አስተያየት ሰጪው ገልጠዋል፡፡

የባለስልጣናት አስተያየት

ከ2013ቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ስር የሚተዳደረው የኦፍላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ከትናንት ጀምሮ ተፈናቃዮች ወደ ኮረም መምጣት የጀመሩ ሲሆን እስካሁን 3,000 ያህሉ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የደቡባዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ የትግራይ ተወላጅም ሆነ የአማራ ተወላጅ በአካባቢው ይኖር ከነበረ ወደ ቀየው የመመለስ መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ተፈናቃዮች ያለምንም ችግር ኮረም ግብተዋል ነው ያሉት፡፡ሆኖም የኮረም ተወላጅ ያልሆኑ የትግራይ ተወላጆች ከተፋቃዮች ጋር ተቀላቅለው ገብተዋል ሲሉ የኦፍላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሀ ይከስሳሉ፡፡

ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
ተፈናቃዮች በአማራ ክልልምስል Alemenw Mekonnen/DW

የተፈናቃዮቹ ማንነት?

“የአማራ ተወላጆች የነበሩና ወደ ትግራይ ተፈናቅለው የነበሩ እየተመለሱ ነው፣ ከእነርሱ ጋር ሆነው ነዋሪ ልነበሩና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በርካታ ገብተዋል፡፡” ብለዋል፡፡ ሆኖም ከመከላከያ አባላት ጋር በመሆን እየተጣራ እንዲወጡ እያደረጉ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች ብሶት
የደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ግን ስሞታው ሀሰት መሆኑንና በአከባቢው ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ናቸው ወደ ኮረምም ሆነ ወደ አላማጣ እየተመለሱ ያሉት ሲሉ ክሱን ተከላክለዋል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ አላማጣ መመለስ የጀመሩት የትግራ ተፈናቃዮች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዙሮች 16 ሺህ 800 ያክል እንደነበሩ  አቶ ሀፍቱ ጠቁመው ከዚያ በኋላ ግን  ተፈናቃዮቹ በራሳቸው መንገድ እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡
“... ከዚህ በላይ ማገዝ አንችልም አቅም የለንም፣ መንገዱ ሰላም ነው ተፈናቃዩ በራሱ መንገድ ወደ ቀየው መመለስ አለበት” ነው ያሉት፡፡
“አንዳንድ የትግራይ ተፈናቃዮች ትጥቅ ሳይፈቱ  ገብተዋል” የተባለውን ስሞታ በተመለከተም ሰዎቹ የየአካባቢ ነዋሪ በመሆናቸው ከነመሳሪያቸው ቢገቡም የፀጥታ ስራ ተልዕኮ እንደማይሰጣቸው አቶ ሀፍቱ አመልክተዋል፡፡ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ መመለሳቸው

ቆቦ የተሰበሰቡ ተፈናቃዮች ያጋጠማቸው ችግር

ይህ በአንዲህ እንዳለ ዛሬ ከተለያዩ የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች  የተሰባሰቡ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ ከተማ እንደሚመለሱ እቅድ የተያዘ ቢሆንም ተፈናቃዮቹ ዛሬ ከቆቦ ከተማ ጉዞ ጀምረው አላማጣ ከተማ መግቢያ ከደረሱ በኋላ “ባልታወቀ ምክንት” በፀጥታ ኃይሎች ወደ ቆቦ እንዲመለሱ መደረጉን የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባል አቶ መንገሻ ቸሩ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ ከ15 ሺህ በላይ ተፈናቃይ  ዛሬ አላማጣ እንደሚገባ ሲጠበቅ ነበር፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ