1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከተማና ከተሜነትን ለዓመታት አዋዳ የኖረችው ፒያሳ

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

ከተማ እያደገ፣ እየተዋበ፣ የላቀ እየዘመነ፣ የፍሳሽና እና ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ እየተሳለጠ፣ መንገዶች እየሰፉ መሄዱ የማይቀር ነው። ሰሞነኛው ለልማት በሚል ፒያሳን የማፍረሱ የመንግሥት ርምጃ ብዙ ድንጋጤ፣ ከተለያየ አቅጣጫ አግራሞት፣ ቁጭት፣ ብስጭት፣ ሐዘን እና ለምን የሚሉ ጥያቄዎችንም ከብዙዎች አስነስቷል።

https://p.dw.com/p/4eEcz
የፈረሰችው ፒያሳ
የፈረሰችው ፒያሳ፤ አዲስ አበባ ኢትዮጵያምስል Solomon Muchie/DW

አዎ ፒያሳ የአዲስ አበባ እምብርት ናት፤ ነበረችም

ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስ "የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ" በተባለው መጽሐፋቸው የሥልጣኔ ዘይቤን በተመለከ በዳሰሱበት ክፍል ገጽ 31 ላይ "ሲቪላይዜሽን" የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል ውርስ ትርጋሜው ከተማ ማለት መሆኑን ይጠቅሳሉ። የፍቺው አመጣጥም ከሰው ልጅ አዕምሮ ማመዛዘን መመንጨቱንና የንጽጽሩ ሌላኛው አንጓም ገጠር እንደሆነ ያስገነዝባሉ። "የከተማ ኑሮ ምን ጊዜም በየትም ቦታ ቢሆን ይበልጥ የተደራጀ ነው" የሚሉት ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስ "ትምህርት ቤቱ ፣ ቤተ ክርስትያኑ ፣ ፍርድ ቤቱ፣ ሐኪም ቤቱ ፣ የሙዚቃ እና የቲያትር ቤቱ ሌላም ይህንን የመሳሰሉ የሰው መንፈስ በረጅም ትግል ተጣጥሮ ያስገኛቸው የስልጣኔ ሀብታት የሚገኙት በባላገር ሳይሆን በከተማ ነው" ይሉና የሥልጣኔ ዘይቤ ከከተማ ዘይቤ ጋር የተያያዘው በዚህ ምክንያት መሆኑንም ያስረዳሉ። 

አዎ ፒያሳ የአዲስ አበባ እምብርት ናት፤ ነበረችም

በጣልያንኛ ቋንቋ ስያሜ የምትጠራው ይህች የከተማ ውስጥ ከተማ በሲኒማ ቤቶች፣ በወርቅ ቤቶች ፣ በኬክ ቤቶች ፣ በሆቴሎች፣ በምሽት መዝናኛ ቤቶች ፣ በሙዚቃ ቤቶች የተሞላች አልፎም ለድርሰትና የፈጠራ ሥራዎች መወለድ የሀሳብ ማማጫ ሆኖ ኖራለች። ኖራም ነበር።
ፒያሳ በ 1903 ዓ.ም በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኖራ ግንብ የተሠራው የራስ መኮንን ድልድይ መገኛም ናት። ሥልጣኔዎች እና ከወዲህ ወዲያ የሰው፣ የተሽከርካሪ መሻገሪያ ድልድዮች ተመጋጋቢ ውርሶች ናቸው። 
የአሁኑ የሀገር ፍቅር ትያትር ስያሜው ሀገር ፍቅር ማሕበር በሚል ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር መዘጋጀቱን ተከትሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማንቃትና በአንድነት እንዲቆም ለማድረግ የተቋቋመ እዚው መሀል አዲስ አበባ ፒያሳ ውስጥ ነው። የሀገሪቱ አንቱ የተባሉ የኪነ ጥበብ ሰዎችም ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩበት የጥበብ አውድማ ነው። ይህ የፒያሳ ውለታ መሆኑ ነው።

በፒያሳ ምን ጎድሎ? ምንስ ታጥቶ?

አራት ኪሎ የአርበኞች ሃውልት ፊህ ለፊት የነበረ ሕንፃ
አራት ኪሎ የአርበኞች ሃውልት ፊህ ለፊት የነበረ ሕንፃምስል Solomon Muchie/DW

ፒያሳና ዙሪያ ገባው ፣ ጠቅላውም አራዳ፣ ዋና ዋና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቋማት ተከትመውበታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፣ መታሰቢያቸው ሆኖ የቆመው  ሃውልት፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፓርቲ ጽ/ቤቶች፣ የሀገሪቱ እድሜ ጠገብና ቀዳሚ ትምህርት ቤቶች ፣ የመጀመርያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ፣ባለትዳሮች፣ ፍቅረኞሞች ታሪካቸውን ያሳረፉባቸው ኬክና ባቅላ ቤት ቢፈለጉ መገኛው ከፒያሳ ነበር። ይህ ዛሬ ታሪክ ሆኗል።

ጣይቱ ሆቴል በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዘመናዊ ሆቴል ነው። በእርግጥ አሁን እድሳት ላይ ይገኛል። ከዚህ ሆቴል አጠገብ ብዙ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ቡና ቤቶች ይገኛሉ። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሃውልት እና አደባባይ የብዙ ሰዎች የቀጠሮ ማሰሪያ ነበር። በጥቅሉ ፒያሳ የተሟላ የከተማ ሕይወት መሠረት፣ መገለጫም ነበረች። ጣት ላይ ቃል ኪዳን ያተሙ የትዳር ቀለበዮቶች ፣ እጅ ላይ የታሰሩ ሰዓቶች፣ መዘነጫ መነጽሮች ፣ አልባሳቶች እንዲያው በጥቅሉ የዘመናዊነት ምልክቶች ሁሉ በዚያ ፒያሳ ውስጥ ነበሩ። ፒያሳ አሁን ግን ፈርሳለች። 
እንዲህ የምናጫውታቸው ሙዚቃዎች ፣ ከሙሃሙድ ሙዚቃ ቤት፣ ከአያሌው ሙዚቃ ቤት ፣ ከአሊ ታንጎ ሙዚቃ ቤት በገናና ባንዶች ተቀምረው ለገበያ የሚውሉበትም ነበር ፒያሳ።

ከተሞች እና ልማት የሚቀይራቸው ገጽታቸው

ከተማ እያደገ፣ እየተዋበ፣ የላቀ እየዘመነ፣ የፍሳሽና እና ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ እየተሳለጠ፣ መንገዶች እየሰፉ መሄዱ የማይቀር ነው። ሰሞነኛው ለልማት በሚል ብዙ ድንጋጤ፣ ከተለያየ አቅጣጫ አግራሞት፣ ቁጭት፣ ብስጭት፣ ሀዘን እና ለምን የሚሉ ጥያቄዎችንም ከብዙዎች አስነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ታማኝ" ከተባሉ ከፍተኛ  ግብር ከፋዮች ጋር አድርገውት በነበረው ምክክር 
"አዲስ አበባ ላይ ትልቁ ድህነትና ችግር ያለው መሃከል ላይ ነው። መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ የሚባለው ነው። ዋናውን ችግር ደፍረን ካፈረስነው በ5 ዓመት ከተማው ምን እንደሚመስል ታዩታላችሁ" በማለት የሥራውን ዓላማ "ካልፈረሰ ሌላ አማራጭ የለም" በማለት የከተሞችን የሁል ጊዜ ለውጥ መኖር ተገቢነትን አስረድተዋል።

በዚህ ስፍራ ውስጥ ታሪካዊ ኬክ ቤቶች ፣ ወርቅ ቤቶች፣ ልብስ መሸጫ ቤቶች ፣ ቡና ቤቶች ይገኙበት ነበር
ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ሲኒማ አምፒየር ወርቅ ቤቶች የነበሩበት ስፍራምስል Solomon Muchie/DW

"የማልማት ሥራ ሂደቱ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በመንግሥት ብሎም አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የተለያዩ አካላት የተያዙና የተከራዩ ንብረቶችን የነካ ሊሆን ቢችልም ይህ ለረዥም ጊዜ ፋይዳ ትልም ይዞ የተነሳ ሥራ ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል ብሎም ለሰፊው ሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ ነው" ሲሉም ትናንት ጽፈዋል።

እናት የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ ግን የተለየ ምልከታ እንዳለው ገልጿል ። "ፒያሳን ጨምሮ በሌሎች ሥፍራዎችም ነባር ሕንፃዎችን ወደ ፍርስራሽነት የመቀየርና በአዲስ የመተካት ፕሮጀክት እንደ ማዕበል ሆኖ የከተማችን ገላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እንዳልነበሩ እያደረገ ቅርሶቻችንን እየበላ የብዙዎችን ሕይወት በማናወጥ ላይ ይገኛል" የሚለው ይህ የፖለቲካ ድርጅት "ልማት የማይጠላ፣ የሚበረታታ እና የሚደገፍ ተግባር ቢሆንም ፈረሳው በዚሁ ከቀጠለ የአዲስ አበባን መነሻ አሻራ ለማየት የምንቸገር ይሆናል" በማለት ድርጊቱን ኮንናኗል። 
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የተሠራበት አራዳ ሕንፃ ሥር በነበሩ ሶቆች ውስጥ ሱቃቸውን ለሠላሳ ዓመት ያህል የሠሩበት እናት እሳቸውን ጨምሮ እዚያ ቦታ ላይ የተነሱት እዚያው ፒያሳ ሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ጀርባ የመሥሪያ ቦታ ሊሰጣቸው መሆኑን ነግረውናል። የፒያሳው ሱቃቸው መፍረስ ግን ግንኙነታቸውንም በጥሶታል።

የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር "በልማት ምክንያት ሲኖሩ ከነበሩበት ጎስቋላ መንደር የተነሱ ነዋሪዎችን በተመለከተ" "የማልማት ሥራዎቹ ሳይጀመሩ አስቀድሞ ከነዋሪዎቹ ጋር የምክክር ስራ ተደርጋል፣ በመንግሥት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች ጽዱ እና ለመኖር ምቹ የሆኑ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፣ የንግድና የመሥሪያ ቦታ ለነበራቸው ነዋሪዎች በተገቢ ቦታ የተሻለ የንግድ ቦታ ተሰጥቷል፣ የግል ይዞታ ለነበራቸው ነዋሪዎች ካሳ እና ምትክ ቦታ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን በራሳቸው በኩል ያሉ መስፈርቶች አጠናቅቀው ለሚመጡ ነዋሪዎች በሚመጡበት ጊዜ የሚስተናገዱ ይሆናል።" ሲል አስታውቋል። እዚው መሃል ፒያሳ ያነጋገርነው የላዳ ታክሲ ሾፌር ግን የሚለው ሌላ ነው።

ሀገር ፍቅት ቲያትር አካባቢ
ሀገር ፍቅት ቲያትር አካባቢምስል Solomon Muchie/DW

የፓርቲ፣ የኢሰመኮ እና የሥነ ሕንፃ ጥበብ ባለሞያ አስተያየቶች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቤቶቻቸው የፈረሰባቸው ሰዎችን አስመልክቶ ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ "ሕገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ እርምጃ ሕጋዊ ሂደትን መከተል እና እርምጃው ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል" ማለቱ ይታወሳል።

እናት ፓርቲ "ከመቶ ዓመት በላይ ባስቆጠረ ጊዜ የጎለበተው ማኅበረሰባዊ መስተጋብራችን በተያዘው አካሄድ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ታሪክ አልባ አዲስ አበባን ታቅፈን እንዳንቀር የትኛውም አይነት ፕሮጀክት ከስሜት ይልቅ በስሌት መጀመርና መከናወን አለበት" ያለው ከቀናት በፊት ነው።

የሥነ ሕንፃ ጥበብ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ መኮንንን በዚህ ጉዳይ የልማት ሥራዎች ከተሞች ውስጥ እንዴት ትናንትን ከዛሬና ከነጋ ሊያጣጥሙ ይገባል  ብለን ከዚህ በፊት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

ከራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብሎ የነበረ ግዙፍ ሕንፃ
ከራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብሎ የነበረ ግዙፍ ሕንፃምስል Solomon Muchie/DW

"ልማት ማለት አንድን ቦታ ለማህበረሰብ አገልግሎት እንዲመች አድርጎ ማዘጋጀት ነው እንጂ ረጃጅም ሕንፃ ወይም ደግሞ በዘመናዊ ቁሳቁስ የተገነባ አዳዲስ ሕንፃ መገንባት ላይሆን ይችላል። እሱ ፍላጎቱም ካለ ለዚህ ተለይተው የሚመረጡ ቦታዎች አሉ። እንደዚህ ያሉ የቅርስ ቦታዎች ፣ ኪነ ሕንፃዎች የአንድ ማህበረሰብ ትውስታ አካል ናቸው።"

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕብረ ሰብ መስተጋብር እና ጉድኝት በጉልህ ይታይባቸው የነበሩ ጥንታዊ ከተሞች ቅርሳቸው ዛሬ ድረስ ህያው ሆኖ መዳሰሱን ሐርር እና ጎንደርን በመጥቀስ ማሳየት ይቻላል። የኢትዮጵያ በሉዓላዊነት፣ የአፍሪካ በፖለቲካ ትርጉም መዲና የምትባለው አዲስ አበባ በውስጧ ከተሜነት እና የከተማ መልክ ይገኝበት የነበረው ፒያሳ ላይ ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ